1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃይሌ የለንደን ኦሎምፒክ ምዕራፍ ተዘጋ

ሰኞ፣ ግንቦት 20 2004

ሃይሌ ገ/ሥላሴ በመጨው የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ ለመሳተፍ የነበረው ተሥፋ ትናንት በኔዘርላንድ-ሄንገሎ ማጣሪያ ውድድር ፍሬ ሳይሰጥ ቀርቷል።

ምስል AP

ሃይሌ ገ/ሥላሴ በመጨው የለንደን ኦሎምፒክ ጨዋታ ለመሳተፍ የነበረው ተሥፋ ትናንት በኔዘርላንድ-ሄንገሎ ማጣሪያ ውድድር ፍሬ ሳይሰጥ ቀርቷል። ቀደም ሲል በማራቶን ለተሳትፎ ለመብቃት ያደረገው ጥረት ያልተሳካለት ሃይሌ በትናንቱ የአሥር ሺህ ሜትር ሩጫ በሰባተኝነት ተወስኖ ነው የቀረው። እርግጥ ሃይሌ ያሰበው አይሁንለት እንጂ የፈጀው ጊዜ አንድ ከ 36 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆነ አትሌት እስካሁን ካስመዘገበው ሁሉ የፈጠነ ነበር። ይህም ክብረ-ወሰን ጥቂትም ቢሆን የክብረ-ወሰኑን ንጉስ ሊያጽናና ይገባል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሺን ይህን ታላቅ የስፖርት ሰው የውድድር ተሳትፎው ቢቀር እንኳ በይፋ ወኪልነት ወደ ለንደኑ ኦሎምፒክ ቢልከው በጣሙን የሚገባው ነው። በዓለምአቀፉ የስፖርት መድረክ በተጎናጸፋቸው በርካታ ድሎቹ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲነሣ ሲያስደርግ በበጎ አምባሳደርነት አገሩን በመወከል ያደረገው ታላቅ አስተዋጽኦው ጨርሶ መረሳት የሌለበት ነገር ነው።

ወደ ትናንቱ ውድድር መለስ እንበልና በሩጫው ታሪኩ በቀለ፣ ሊሊሣ ደሲሣና ስለሺ ስሂኔ ከአንድ እስከ ሶሥት በመከታተል ቀደምቱ ሲሆኑ በተለይም አሸናፊው ታሪኩ ደስታውን በታላቅ ስሜት ነበር የገለጸው።

ምስል picture-alliance/dpa

በለንደኑ ኦሎምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩት ስፖርተኞች እስከ ሰኔ 30 ቀን በሙሉ የሚመረጡ ሲሆን በተለይም ወጣቶቹ አትሌቶች ለነሃይሌ ጥሩ ተተኪ እንደሚሆኑ ተሥፋ እናደርጋለን። የሄንገሎውን ሩጫ በአካባቢው ሃገራት የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውንም በቅርብ ሲከታተሉ በሃይሌ መሸነፍ ቢያዝኑም ድሉ የኢትዮጵያውን በመሆኑ መካሳቸውን ነው በደስታ የገለጹት።

ሩጫውን በተመለከተ ውድድሩን በስፍራው ተገኝታ የተከታተለችውን ወኪላችንን ሃይማኖት ጥሩነህን ዛሬ በስልክ አነጋግሬ ነበር።

በተቀረ ትናንት ራባት ላይ ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ ውድድርም የኢትዮጵያ አትሌቶች አንዳንድ ጥሩ ውጤቶች ማስመዝገቡ ሆኖላቸው ነበር። የዘንድሮው የኢስታምቡል የአዳራሽ ውስጥ የዓለም ሻምፒዮና የ 800 ሜትር አሸናፊ መሐመድ አማን በሞሮኮም ድሉን ደግሞታል። በ 3 ሺህ ሜትር መሰናክል በወንዶች ጋሪ ሮባ ሲያሸንፍ በሴቶችም ሕይወት አያሌው ቀደምቷ ሆናለች።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW