1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥሪ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3 2016

የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮቹ ቁርዓን እና መጽሃፍ ቅዱስ በመያዝ ወደ ተፋላሚዎቹ በመሄድ ለእርቅ ቁርጠኛ እንዲሆኑ እስከ መማጸን የሚዘልቅ ውጥን ይዘናል ይላሉ፡፡

Äthiopien | Religiöse Führer der Region Oromia rufen zum Frieden auf
ምስል Seyoum Getu/DW

የሃይማኖት አባቶች የሰላም ጥሪ

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል እና በመላው አገሪቱ በወንድማማቾች መካከል የሚደረግ ግጭትና አለመግባባት ምዕራፉ ተዘግቶ ወደ ሰላም መሸጋገር እንዲቻል ሲሉ የሃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከሰባት የእምነት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች ትናንት ዓርብ ከሰዓቱን እስከ አመሻሽ አዲስ አበባ ውስጥ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ የሰላም አስፈላጊነት ላይ ከመከሩ በኋላ ነው።
ቦራቲ አርት ፕሮሞሽን የመስከረም ወር የተለያዩ በዓላትን ምክኒያት በማድረግ ከአሜሪካ ህዝብ ተራድኦ ድርጅት (USAID) ጋር በመተባበር በሰላም አስፈላጊነት እና ሰላም ማምጫ መንገዶች ላይ የተለያዩ የህብረተሰብ አካላትን ሲያወያይ ቆይቷል፡፡ በመስከረም ወር ላይ የተከበሩ የመስቀል እና የኢሬቻ በዓላትንም ምክኒያት በማድረግ ከወጣቶች፣ አባገዳዎች እና የተለያዩ የህብረተሰብ አካላትን አወያይቶ ማህበረሰቡን ከፈተነው የግጭት አዙሪት መውጫ መንገድ ላይ ምክክር ተደርጓል፡፡ 
የዚህ መርሃ ግብር የመጨረሻ በሆነውም በትናንቱ ከሃይማኖት አባቶች ጋር በተደረገው ውይይት ላይም በኦሮሚያ ሃማኖት ተቋማት ጉባኤ ስር የተካተቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ እስልማና ሃይማኖት፣ የወንጌላውያን አብያተክርስቲያናትን ጨምሮ ከሰባት የእምነት ተቋማት የተውጣጡ የሃይማኖት ተወካዮች የታደሙበት የፓናል ውይይት ተካሂዶ ነበር፡፡ 
የዚህ መርሃ ግብር ውጥን ላይ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የፕሮግራሙ አስተባባሪ የቦራቲ አርት ፕሮሞሽን ስራ አስከያጅ ወጣት ብሩክ ግርማ በተለይ የሃይማኖት ተቋማት ዘላቂ ሰላም በማስፈን ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው ይላሉ፡፡ በመሆኑም ከእምነት ተቋማቱ ተወካዮች ጋር የሚካሄደው ውይይት ከንግግር ባለፈ ገቢራዊ እንዲሆኑም እምነቱ አለ ብሏል፡፡
መጋቢ ሃይማኖት ቆሞስ አባ ገብረማሪያም ገብረመደህን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን  ወክለው ነው በዚህ የውይይት መድረክ የተሳተፉት፡፡ “ያለሰላም የሰው ልጅ የህይወት ዋስትናው የጨለመ ነው፡፡ በመሆኑም የዛሬ መርሃግብር በትልቁ ነገር ላይ የተደረገ በመሆኑ መልካም ውይይት አድርገናል” ሲሉም የውይይቱን ወሳኝነት አስረድቷል፡፡
ዑስታዝ ጀማል መሃምድ አሊዪ ደግሞ የእስልምና ሃይማኖትን ወክለው በሰላም ውይይት መድረኩ ከታደሙ ናቸው፡፡ “ከኦሮሚያ ሰባት የእምነት ተቋማት ተሰባስበን በሰላም ጉዳይ ስንወያይ ጥሪያችንን የምናቀርበው ሰላሙ እንደ አገር እንዲመጣ ነው፡፡ ይህን የምንለው በአንድ አገር ውስጥ የሆነ ቦታ አለመረጋጋት እያለ ሌላ ቦታ ሰላም ይኖራል ብሎ ማሰብ ከባድ ስለሚሆን ነው” ብለዋል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹ ከአዳራሽ ውይይት ባለፈ ወደ የተፋላሚ ሃይላቱ ሄደው እርቅ እንዲወርድ ስለመጠየቅ ያስባሉ፡፡ ዑስታዝ ጀማል የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮቹ ቁርዓን  እና መጽሃፍ ቅዱስ በመያዝ ወደ ተፋላሚዎቹ በመሄድ ለእርቅ ቁርጠኛ እንዲሆኑ እስከ መማጸን የሚዘልቅ ውጥን ይዘናል ይላሉ፡፡ መጋቢ ሃይማኖት ቆሞስ አባ ገብረማሪያም በበኩላቸው የአንድ አከባቢ ሰላም እጦት ሌላውን የሚረብሽ እንደመሆኑ በሁሉም ቦታ ሰላም ይሰፈን ዘንድ አለመግባባቱ በመግባባት እስኪተካ እርቅ የማውረድ ጥረቱ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የሀሳቡ አመንጪ እና የእርቅ ሂደቱ አስተባባሪው ወጣት ብሩክ ግርማ በበኩሉ የተጀመረው ጥረት ተፈላጊው ሰላም  እስኪወርድ የሚቀጥል ነው ይላል፡፡ “ከመሰረቱ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ሃሳቦችን የሚያራምዱ አካላት ቁጭ ብለው የሚወያዩበት ጊዜ ያስፈልጋል፡፡ ያም ሆኖ እርቁ እስኪመጣ እኛ ጥረታችንን እንቀጥላለን፡፡”
በኦሮሚያ ክልል ለአምስት ኣመመታት ያልተቋጨውንአለመግባባት በሰላም ለመፍታት ባለፈው ዓመት ሚያዚያ ወር ላይ መንግስት እና መንግስትን የሚፋለመው ``የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት`` ተወካዮች በታንዛንያ አድርገውት የነበረው የእርቅ ጥረት ያለፍሬ መቋጨቱ ይታወሳል፡፡
ስዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር


Y

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW