የቀጠለው የሃድያ ዞን መምህራን አቤቱታ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 29 2016በሃድያ ዞን የምሥራቅ ባድዋቾ ፣ የምዕራብ ባድዋቾ እና የዱና ወረዳ የመንግሥት ሠራተኞች “ የሦስት ወራት የደሞዝ ከፍያ አልተፈጸመልንም “ በሚል ከያዝነው የጥቅምት ወር መግቢያ አንስቶ ሥራ አንዳቆሙ ይገኛሉ ፡፡ የሠራተኞቹን ሥራ ማቆም ተከትሎ ትምህርት እና ህክምናን ጨምሮ የወረዳዎቹ መስተዳድር ጽህፈት ቤቶች መደበኛ አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በተለይም መምህራን ሥራ በማቆማቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ተነጥለው ቤታቸው ለመዋል መገደዳቸውን ነው ነዋሪዎች ለዶቼ ቬለ የገለጹት ፡፡
የትምህርት ቤቶች መዘጋት
ወልቂጤን ጨምሮ በጉራጌ ዞን ከተሞች የሥራ ማቆም አድማየሦስት ልጆች አባትና የሾኔ ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን የገለጹት አቶ አብረሃም ሞሎሮ ” በከተማው ከመምህራን የደሞዝ ጥያቄ ጋር በተያያዘ ትምህርት በመዘጋቱ ልጆቼ ቤት ለመዋል ተገደዋል ፡፡ ልጆጃችንን የግል ትምህርት ቤት ለማስተማር የሚያስችል ገቢ የሌለን ነዋሪዎች በችግር ውስጥ ነው ያለነው ፡፡ መቼ የሚለውን ባናውቅም ልጆቻችንን ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበትን ቀን እየጠበቁ ይገኛሉ “ ብለዋል ፡፡
በወረዳዎቹ የደሞዝ አለመከፈል በጤና ተቋማት አገልግሎት ላይም የራሱን ተፅኖ ማሳደሩ ይነገራል ፡፡ ተመሳሳይ የደሞዝ ይከፈለን ጥያቄ ያቀረቡ የጤና ባለሙያዎች ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ሥራ አቁመው ነው የሰነበቱት ፡፡ አሁን ላይ ህብረሰተቡ እያጋጠመው ያለውን ችግር በመረዳት ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ ከጥያቄያቸው ጎን ለጎን ለድንገተኛ ታካሚዎች ብቻ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አንድ የሾኔ ሆስፒታል ሀኪም ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡
ምላሽ ያጣው የሠራተኞቹ ጥያቄ
የወረዳዎቹ መንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጥያቄው ተፈጻሚ እንዲሆንላቸው ለወረዳቸው ፣ ለሃድያ ዞን መስተዳድር ፣ ለማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እና ለፌደራል እምባ ጠባቂ ተቋም አቤቱታቸውን ማቅረባቸውን የምስራቅ ባድዋቾ ወረዳ የመምህራን ማህበር አስታውቋል ፡፡ ነግር ግን እስከ አሁን ምላሽ እንዳላገኙ ነው የማህበሩ ሊቀመንበር መንግሥቱ ገዶሬ የገለጹት ፡፡
ዶቼ ቬለ የሠራተኞቹ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ከወረዳ እስከ ክልል የሚገኙ ባለሥልጣናትን ለማነጋገር ከባለፈው ሰኞ ጀምሮ ጥረት ቢያደርግም ምላሽ የሚሰጥ አካል ባለማገኘቱ የክልሉን አስተያየት በዚህ ዘገባ ማካተት አልተቻለም ፡፡
በአርባምንጭ መምህራን አድማ መቱ ያም ሆኖ ከሦስቱ ወረዳዎች አንዱ የሆነውን የዱና ወረዳ መምህራንን አቤቱታ መቀበላቸውን ያረጋገጡት በፌደራል የህዝብ እምባ ጠባቂ ተቋም የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የምርመራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አበራ ንጉሴ ተቋማቸው ጥያቄው በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲያገኝ በተጠሪ ተቋማት ላይ ምርምራ መጀመሩን ተናግረዋል ፡፡
በሃድያ ዞን በምሥራቅ ባድዋቾ ፣ በምዕራብ ባድዋቾ እና በዱና ወረዳ በማገልገል ላይ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከባለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የደሞዝ በወቅቱ አለመከፈል ችግር እያጋጠማቸው እንደሚገኝ ይታወቃል ፡፡ የቀድሞው የደቡብ ክልል የወረዳዎቹን በጀት በዋስትና በሚሲያዝ በብድር የወሰደውን የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ባለመክፈሉና በጀቱም ለዕዳ ክፍያ መዋሉ አሁን ለተፈጠረው ችግር ምክንያት መሆኑን የወረዳዎቹ ባለስልጣናት ከዚህ ቀደም ለዶቼ ቬለ ገልጸው ነበር ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ