የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ የውሃ ሀብት የተጋረጠበት አደጋ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 26 2015
የኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ የበርካታ ሐይቆችና ወንዞች መገኛ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ እነኝህ የውኃ ሀብቶች ግን አሁን ላይ የህልውና ሥጋት እንዳሳደረባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ በሀዋሳ ከተማ በተካሄደው የሥምጥ ሸለቆ ንዑስ ተፋሰስ የውሃ አያያዝ ፣ አስተዳደርና አጠቃቀም ዙሪያ ባተኮረው አውደ ጥናት ላይ የቀረቡት የምርምር ውጤቶችም ይህንኑ የባለሙያዎችን ምልከታ የሚረጋግጡ ናቸው ፡፡
ከአውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች አንዱ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ታዬ አለማየሁ ላለፉት ሃያ ዓመታት በውሃ ዘርፍ አጠቃቀም ዙሪያ የተለያዩ ምርምሮችን ሲያካሂዱ መቆየታቸውን ይናገራሉ ፡፡ አሁን ላይ ሐይቆቹን በውኃ ፍሰት በሚመግቡ አብዛኞቹ ወንዞች ላይ ባልተናበበ መልኩ እየተከናወነ የሚገኘው የመስኖ እርሻ አጠቃቀም በሐይቆቹ ቀጣይነት ላይ ሥጋት መደቀኑን ዶክተር ታዬ ጠቅሰዋል ። ለዚህም ከስምጥ ሸለቆ ሐይቆች አንዱ የሆነውን የደንበል ወይንም የዝዋይ ሐይቅን በአብነት አንስተዋል ፡፡
ቀድሞ የነበረው ሥጋት ከአየር ንብረት መለዋወጥ ጋር የተያያዘ እንደነበር የሚናገሩት ዶክተር ታዬ “ አሁን ላይ ግን ከውኃ ፍሰት መመናመን የተነሳ ወንዞች ሐይቅ መድረስ አለመቻላቸው አዲስ ሥጋት እየሆነ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ዘንድሮ ከተር እና ቦሻ የተባሉት ወንዞች ወደ ደንበል ወይም ዝዋይ ሐይቅ ለመድረስ የተቸገሩበትን ሁኔታን አይተናል ፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በሀይቆቹ ተፋሰሶች ላይ በጥናት ላይ ያልተመሠረተና የተፈጥሮ ሀብት አጠባበቅን መሠረት ያላደረጉ የእርሻ ሥራዎች መስፋፋታቸው ነው ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም እነዚህ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እርሻዎች በዘፈቀደ የሚጠቀሙት የፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭትም የሀይቆቹን ሥነ ሕይወትና የከርሰ ምድር ውሃን አደጋ ላይ እየጣሉ ይገኛሉ “ ብለዋል ፡፡
በሀዋሳው አውደ ጥናት ላይ በዶክተር ታዬ ዓለማየሁ የቀረበውን ሀሳብ የሚያጠናክር ገለጻ ያደረጉት ሌላኛዋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውሃ አካላት ተመራማሪ ዶክተር አደይ ንጋቱ ናቸው ፡፡ አሁን በሐይቆቹ ላይ የሚታዩት ሥጋቶች ካልተቀረፉ በሚቀጥሉት ሃያ እና ሠላሳ ዓመታት ውስጥ በውሃ አካላቱ ላይ በአይን ሊታዩ የሚችሉ ጉዳቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ የሚናገሩት ዶክተር አደይ ለዚህም በዋናነት ሁለት ምክንያቶች እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል፡፡ የመጀመሪያው የውሃ ሀብቶቹ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚገኙ መሆናቸው በራሱ ከመልክዐ ምድራዊ አቀማመጥ ጋር የተያያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከማኅበረሰቡ ያልተገባ አጠቃቀም ጋር የተገናኘ መሆኑን ተመራማሪዋ አብራርተዋል ፡፡
የውኃ አካላት ተመራማሪዎች በሥምጥ ሸለቆ የሚገኙ የውሃ ሀብቶችን ለመታደግ መፍትሄ ነው ያሉትንም ምክር ሀሳብ ጠቁመዋል ፡፡ የውሃ ዘርፍ ተመራማሪው ዶክተር ታዬ አለማየሁ ሀብቱን በዘላቂነት ለመጠበቅ ከትንሽ የተፋሰስ ደረጃ ውሃን ማዕከል ያደረገ የተቀናጀ ስትራቴጂ መንደፍ ይገባል ይላሉ ፡፡ ይህም ማኅበረሰቡ የእርሻ መሬቶችን የት ፣ እንዴትና በምን ያህል የውሃ መጠን መጠቀም እንዳለበት በጥናት ላይ የተመሠረተና ወጥ የሆነ የሀብት አጠቃቀም ለመፍጠር እንደሚያስችል ነው ዶክተር ታዬ የገለጹት ፡፡
ሌላኛዋ የዘርፉ ተመራማሪ ዶክተር አደይ ንጋቱ በበኩላቸው ለሰፋፊ እርሻዎች የወንዝም ሆነ የሐይቅ ውሃን የሚጠቀሙ አካላት ለተጠቀሙበት በጥናት ላይ የተመሠረተ ክፍያ ቢኖር ሀብቱን ለመጠበቅና ለመንከባከብ እንደ አንድ መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸው ይናገራሉ ፡፡ ሰው በተፈጥሮ በነጻ ለሚያገኘው ነገር ግድ አይሰጠውም ይልቁንም ያባክነዋል የሚሉት ዶክተር አደይ ለውሃው ክፍያ ቢኖር ግን ሀብቱን በቁጠባና በጥሩ አያያዝ የመጠቀም ሁኔታ እንደሚኖር ተናግረዋል ፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ