ህንድ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሁለት መንኮራኩሮችን ወደ ህዋ ልካለች
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 1 2015እስያዊቷ ሀገር ህንድ ሰሙኑን ወደ ጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ የጠፈር መንኮራኩር በመላክ በተሳካ ሁኔታ አሳርፋለች። ቻንድራያን-3 በመባል በሚጠራው በዚህ ተልዕኮ ስኬታማ የሆነችው ህንድ፤ከሳምንት በኋላ ደግሞ ያለፈው ቅዳሜ ለሌላ የጠፈር ተልዕኮ ሌላ መንኮራኩር ወደ ፀሀይ ልካለች።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዝግጅት በሰሞኑ የህንድ የህዋ ሳይንስ ተልዕኮዎች ላይ ያተኩራል።
ያለፈው ረቡዕ በጎርጎሪያኑ ነሀሴ 23 ቀን 2023 ዓ/ም እስያዊቷ ሀገር ህንድ በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ የጠፈር መንኮራኩር አሳርፋለች። ቻንድራያን-3 በመባል የሚጠራው ይህ ተልዕኮ ለህንድ የጠፈር ምርምር ድርጅት በእንግሊዝኛው ምህፃሩ (ISRO) ትልቅ ስኬት ሲሆን፤ ሀገሪቱም በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ ላይ የጠፈር መንኮራኩር በማስቀመጥ የመጀመሪያዋ ሀገርእንድትሆን አድርጓታል።ህንድ ከዚህ ቀደም በጨረቃ ላይ ለማረፍ ያደረገችው ሙከራ በጎርጎሪያኑ 2019 ዓ/ም ባይሳካም ሰሞኑን ግን የሀገሪቱ ሳይንቲስቶች እና ባለስልጣናት የጠፈር መንኮራኩሯ ስታርፍ በጭብጨባ ደስታቸውን ገልፀዋል።
ተልዕኮው የተጀመረው ከስድስት ሳምንታት በፊት ሲሆን ህንዳውያን በቴሌቭዥን ስክሪኖች ላይ ተጣብቀው በጉጉት ትዕይንቱን ተከታትለው ደስታቸውን ገልፀዋል።
ለ BRICS የመሪዎች ጉባኤ ጆሃንስበርግ ደቡብ አፍሪቃ ሆነው ትዕይንቱን በቀጥታ የተከታተሉት የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ «ይህ የአዲሲቷ ህንድ የድል ዕምባ ነው»ሲሉ ተደምጠዋል ። የቻንድሪያ-3 ተልዕኮ ስኬትም «የህንድ ብቻ አይለም» ብለዋል።
«የህንድ የተሳካ የጨረቃ ተልዕኮ፤ የህንድ ብቻ አይደለም።ይህ ዓመት የህንድ ጥልቅ አመራር ውጤት የታየበት ነው። የእኛ አንድ ጥበብ፣ አንድ ቤተሰብ ፣አንድ የወደፊት ዕጣ አካሄድ በዓለም ዙሪያ እያስተጋባ ነው።»በማለት ገልፀዋል።
የህንድ የጠፈር ተልዕኮ የተሳካው የሩስያ ሉናር-25 የተባለው የጠፈር መንኮራኩር ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ በጨረቃ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ላይ ከተከሰከሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው። ከዚህ አንፃር የህንድ የጠፈር ምርምር ድርጅት /ISRO/ ሊቀመንበር ኤስ. ሶማናት የቻንድራያን-3 ተልዕኮ የአዲስ ወሳኝ ምዕራፍ መጀመሪያ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለ ስድስት ጎማው ፣ሰው አልቫው እና በፀሀይ ሃይል የሚሰራው ይህ የህንድ መንኮራኩር ከዚህ ቀደም ብዙ ምርምር ያልተካሄደበትን የጨረቃን ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ በማሰስ ምስሎችን እና ሳይንሳዊ መረጃዎችን በሁለት ሳምንታት ውስጥ ያመጣል ተብሎ ይጠበቃል።ይህ ተልዕኮ ህንድን ከአሜሪካ፣ ከቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት እና ከቻይና ቀጥላ ጨረቃ ላይ መንኮራኩር ያሳረፈች አራተኛዋ ሀገር አድርጓታል።ታሪካዊው የጨረቃ ጉዞ
በኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ እና ቴክኖሎጅ የአስትሮ ፊዚክስ ከፍተኛ ተመራማሪ እና የዓለም አቀፉ የአስትሮኖሚ ህብረት ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ሰለሞን በላይ እንደሚሉት የሰሞኑ የህንድ የጨረቃ ተልዕኮ መሳካት ተጨማሪ ጥናቶችን ለማካሄድ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።
«ከዚህ በፊት «ላውንች» ከተደረጉት ረጅም ጊዜ ነው የወሰደው። 40 ቀን ያህል ወስዷል ወደ ጨረቃ ለመድረስ፤ ነገር ግን ውጤታማ ሆኗል።ውጤታማ መሆኑም አንደኛ በቅርብ ጊዜ በቤተ ሙከራ የምርምር ስራዎችን ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል።አልፋ ፓርቲክልን፣ኤክስሬይን ስፔክትሮ ሜትርን እና በተለይ በረዶ ላይ ያለው ውሃ ሙሉ በሙሉ ለመገንዘብ እና ለመጠጥ ይውላል ወይ የሚለውን ለማወቅ ጥልቅ ምርምር ለማድረግ ይጠቅማል።በአጠቃላይ በሳይንሱ አዳዲስ ግኝቶችን ለማግኘት እና ምርምር ለማድረግ እጅግ ትልቅ ጠቀሜታ አለው። ።»በማለት አብራርተዋል።
ምንም እንኳ አሜሪካ፣የድሮዋ ሶቬት ህብረት እና ቻይና በዘርፉ የተወሰነ ምርምር ቢያደርጉም ዶክተር ሰለሞን እንደሚሉት ፤ጥልቅ የህዋ ሳይንስ ምርምር /Deep Space/ ገና ያልተነካ እና ብዙ ጥናት እና ምርምር የሚጠይቅ ነው።ከዚህ አንፃር ከህንድ በተጨማሪ ሌሎች ሀገሮችም በዘርፉ ቢሳተፉ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል።ከዚህ ባሻገር የህንድ የጠፈር ምርምር ጅማሬ ሳይንሱ የጥቂት ሀገራት ብቻ እንዳይሆን አድርጓል ይላሉ።
«ሌላው የህዋ ሳይንስ የጥቂት ሀገራት ብቻ ሳይሆን የሌሎችም እንደሆነ ትልቅ ትምህርት ሰጪ ነው ብዬ አስባለሁ።የዚህ የህዋ ፉክክሩ በተወሰኑ ሀገራት ላይ ብቻ ጥገኛ እንዳይሆን አድርጓታል።ይህ ነው ሀብት ክፍፍል ማለት።ህዋ ላይ ትልቅ ሀብት ስላለ ፍትሃዊ የሆነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ብዙ ጊዜ በዙ ጊዜ አዳጊ ሀገራት የሚያነሱት ይህንን ነው። አንደኛ ጨረቃ በተፈጥሮ የተለያዩ አካላት አሏት ያንን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማወቅም አንድ ነገር ነው።ከዚያ ተነስቶ ደግሞ መሬትን በጥልቅ ለማወቅ ያስችላል።»ካሉ በኋላ፤
«ሌላው እና ትልቁ ነገር ከመሬት የበለጠ በተለያዩ ፕላኔቶች ላይ ጨረቃን ጨምሮ ትልቅ የሆነ የማዕድን «ዲፖዚት» አለ።በተለይ «ሬር ኧርዝ ሜታል» የሚባሉ አሉ።»ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ አጠቃላይ ሶላር ሲስተምን ለማጥናት እንደሚጠቅም ገልፀዋል።ጨረቃ ዋና የምርምር ማዕከል በመሆኗ ደግሞ ወደ ጨረቃ የሚደረገው ጉዞ ህዋን ከተወሰኑ አካላት በማውጣት መልኩን እየቀየረ መሆኑን ተናግረዋል።
የጨረቃ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ወደፊት ለሚደረጉ ቀጣይ የህዋ ሳይንስ ምርምሮች የኦክሲጅን፣ ነዳጅ እና የውሃ ምንጭ ሊሆን ይችላል ተብሎ ይታሰባል።በመሆኑም የቻንድራያን -3 የሁለት ሳምንት ቆይታ በጨረቃ ላይ ያለውን የማዕድን ስብጥር ለመለየት አሰሳ ማድረግ ላይ ያተኩራል።በተጨማሪም ተልዕኮው በጨረቃ ደቡባዊ ንፍቀ ክበብ በረዶ መኖሩን በማረጋገጥ ለወደፊቱ የጠፈር ምርምር የመጠጥ ውሃ ለማቅረብ ያለመ መሆኑንም የህንድ የጠፈር ምርምር ገልጿል።
በአጠቃላይ ጨረቃ ፣ሌሎች ፕላኔቶች እና አስትሮይዶችን በመሳሰሉ የአፅናፈ ዓለም ክፍሎች በጋዝ፣ በውሃ እና በተለያዩ ማዕድናት፣ የበለፀጉ ናቸው።በመሆኑም ይህንን ጠቃሚ ሀብት ለመቆጣጠር ሀገራት በህዋ ላይ ምርምር የማድረግ ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ምንም እንኳ እስካሁን ዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ ፣ ቻይና እና የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ብቻ በጨረቃ ወለል ላይ ቁጥጥር የሚደረግበት ማረፊያ ያላቸው ቢሆንም፤እስራኤል እና ጃፓንን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ጨረቃ ላይ የምርምር ጣቢያ የማቋቋም ዓላማ አላቸው።የሌሎች የጠፈር ኤጀንሲዎችም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ ነው።
ያም ሆኖ በዘርፉ አንዳንድ ስምምነቶች ቢኖሩም ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን በተመለከተ እስካሁን ህግ ባለመኖሩ፤ ቀድመው ቦታውን የያዙ ሀገራት ሀብቱን መቆጣጠር እንዲችሉ ያደርጋል።
ይህም በህዋ ሳይንስ ምርምር ያደጉ ሀገራትን የበለጠ የሚያበለፅግ ድሃ ሀገራትን ደግሞ የሀብቱ ተጠቃሚ ባለመሆናቸው የበለጠ ድሃ የሚያደርግ ነው የሚል ስጋት አሳድሯል።
ከዚህ አኳያ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አዳጊ ሀገራት በዘርፉ ያላቸውን ሚና በሚመለከት ሁለት አማራጭ አላቸው ይላሉ ዶክተር ሰለሞን።አንደኛው ግን በእጃቸው አይደለም።
«ታዳጊ ሀገራት ሁለት አማራጭ አላቸው።አንደኛው አማራጭ ህዋ ላይ የቀደመ ነው ቅድሚያ የሚሰጠው/first come first serve/ነው።የቀደመ ሁሉ ቦታውን ይይዛል ሀብቱን ይይዛል።»ካሉ በኋላ፤ፍትሃዊነትን ለማስፈን በተባበሩት መንግስታት ህግ እንዲወጣ ግፊት ማድረግ አንዱ የታዳጊ ሀገራት አማራጭ መሆኑን ጠቅሰዋል።ነገር ግን ቀላል አለመሆኑን ገልፀዋል።«ዋናው እና በእጃቸው ያለው ልክ እንደ ህንድ እና ሌሎች ሀገራት ሁሉ በጀት መድቦ ወደ ህዋ መላክ እና ቦታውን ቀድሞ መያዝ ይህ ነው በእጃቸው ያለው።ሪሶርስን በአግባቡ ከተጠቀሙ ይቻላል።»በማለት አብራርተዋል።በአፍሪቃ የህዋ ሳይንስ ተቋም ሰለመገንባት የመከረው አውደ ጥናት
ህንድ በቻንድራያን-3 ተልዕኮ መንኮራኩሯን ስኬታማ በሆነ መንገድ ጨረቃ ላይ ካሳረፈች ከሳምንት በኋላ ያለፈው ቅዳሜ በጎርጎሪያኑ መስከረም 2 ቀን 2023 ዓ/ም ደግሞ ለሌላ የጠፈር ተልዕኮ ሌላ መንኮራኩር ወደ ፀሀይ ልካለች። አድቲያ-ኤል-1 /Aditya L-1 /የተባለችው ይህች መንኮራኩር ተልዕኮዋ አራት ወራት የሚወስድ ሲሆን፤ የፀሐይን ውጫዊ ክፍል ለመመልከት እና ባህሪዋን ለማጥናት የሚያስችል ሳይንሳዊ መሳሪያዎችን የተሸከመች መሆኗ ተገልጿል።
በዚህ ሁኔታ ህንድ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በህዋ ሳይንስ ምርምር ላይ አሻራዋን ለማሳረፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ነው።ሁለተኛውን የህዋ ሳይንስ ተልዕኮ ተከትሎ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር በሰጡት መግለጫም፤ ስለ አጽናፈ ሰማይ የተሻለ ግንዛቤን ለማዳበር በሀገሪቱ ያላሰለሰ ሳይንሳዊ ጥረት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። እንደ ዶክተር ሰለሞን ይህ የህንድ የህዋ ሳይንስ ግስጋሴ በሀገሪቱ በእውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚን ላማሳደግ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።የህዋ ሳይንስ በኢትዮጵያ
በመሆኑም አዳጊ ሀገራት ከህንድ ርምጃ ሊማሩ ይገባል ብለዋል። የህዋ ሳይንስ ምርምር ቅንጦት ሳይሆን ፤የወደፊቱን የሰውልጆች ሁለንተናዊ እድገት የሚወስን በመሆኑ ሀገራት በተቀናጄ ሁኔታ በጀት በመመደብ እና ተቌማትን በማደራጄት በዘርፉ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ ዶክተር ሰለሞን አሳስበዋል።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ