የህወሓት ሊቀ-መንበር በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ሥምምነት ላይ በአፋጣኝ ውይይት እንዲደረግ ጠየቁ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2017
የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የአፍሪካ ሕብረት ፓነል በአፋጣኝ ተሰብስቦ ሊወያይ እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸው ተገለፀ። ዶክተር ደብረፅዮን በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምነቱ ተከታታይ ኮሚቴ ተወካይ ጋር ዛሬ ተገናኝተው መነጋገራቸው ፓርቲው አስታውቋል። በሌላ በኩል በጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ አዲስ የአስተዳደሩ አወቃቀር ማፅደቁ ተገልጿል።
በሳምንቱ መጨረሻ መግለጫ ያሰራጨው በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስቱ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እየጣሰ፣ የትግራይ ህዝብን ወደጎን እየገፋ፣ በተናጠል አዋጆች፣ ደንቦች እና መመርያዎች እያወጣ ይገኛል ሲል ወቅሷል። ህወሓት ይህ አካሄድ ተስተካክሎ እና የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ተከብሮ 'ሁለታችን የውሉ ፈራሚ አካላት በፖለቲካዊ ንግግር እና መግባባት' ልንሰራ ይገባል ሲልም ገልጿል።
የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በሁለት ዓመቱ የስልጣን ጊዜ ምን አሳካ?
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ወቅታዊ አጀንዳዎች ዙርያ አቋሙ የገለፀው በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት በትግራይ በተፈጠረ ፖለቲካዊ ልዩነት ምክንያት ከትግራይ ውጭ መሄድ ይሁን ከሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግል ውጭ ሌላ መንገድ መከተል ለትግራይ ህዝብ የማይመጥን ተግባር በመሆኑ፥ ብሄራዊ የትግራይ ጥቅሞች በሚመለከቱ ጉዳዮች መግባባት ለመፍጠር እና ከሁሉም አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ዝግጁ መሆኑ ህወሓት በመግለጫው ጨምሮ አንስቷል።
በትግራይ የተፈጠረው ፖለቲካዊ መካረር ተከትሎ በርካቶች ከትግራይ መውጣት ጨምሮ የተለየ የራሳቸው ፖለቲካዊ ዓላማ ማስፈፀሚያ መንገድ የሚከተሉበት ሁኔታ እየተተስተዋለ ሲሆን፥ ለዚህ መፍትሔ ማበጀት ደግሞ ከአዲሱ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር እንደሚጠበቅ በበርካቶች ይነገራል። በቅርቡ ፕሬዝደንት ሆነው የተሾሙት ጀነራል ታደሰ ወረደ በተለይም በትግራይ ልሂቃን መካከል እየታየ ያለው ክፍፍል እና የተራራቀ አቋም ማጥበብ ዋና አጀንዳቸው እንደሚያደርጉት ሲገልፁ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል።
ጀነራል ታደሰ የትግራይ የፖለቲካ ባህል በመደማመጥ፣ መቻቻል እና መከባበር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እንደሚሰራም በቅርቡ በተደረገ የካቢኔ ስብሰባ ገልፀዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ በቅርቡ ስልጣን በተረከቡት ጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ካቢኔ አዲስ የመንግስት ተቋማት አወቃቀር አፅድቋል።
ከአዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ነዋሪዎች ምን ይጠብቃሉ?
በአዲስ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር አወቃቀር ላይ የፕሪቶርያ ውል፣ የተፈናቃዮች ጉዳይ እንዲሁም የቀድሞ ተዋጊዎች ወደሰላማዊ ህይወት የመመለስ ሂደት የሚከታተሉ ተቋማት እንደሚካተቱ ተነግሯል። በተደረገው ማሻሻያ መሰረት ከዚህ በፊት የነበሩ ካቢኔ ሴክሬታሪያት የተባሉ አደረጃጀቶች መቅረታቸው እና አንድ ምክትል ፕሬዝደንት ብቻ እንደሚኖር እንዲሁም ውሱን የካቢኔ አባላት ለውጥ እንደሚኖርም ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት ዛሬ ባሰራጨው መግለጫ፥ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምንቱ ክትትል፣ ማረጋገጥ እና ማስከበር ተልእኮ ኮሚቴ ሐላፊ ሆነው ከተመደቡት ሜጀር ጀነራል ሳማድ አላዴ ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው አመልክቷል። ህወሓት እንዳለው ሜጀር ጀነራሉ በአፍሪካ ሕብረት እስካሁን ድረስ ስራ ላይ የቆዩት ሜጀር ጀነራል ስቴቨን ራዲናን ተክተው የተሾሙ መሆኑ ገልጿል።
በዚህ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ስምምነቱ አፈፃፀም ክትትል ኮሚቴ እና የህወሓት ውይይት፥ በፕሪቶርያው ስምምነት መሰረት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ውጭ የሆኑ ሐይሎች አሁንም ከትግራይ ባለመውጣታቸው የተፈናቀለ ህዝብ ወደቀዬው መመለስ አለመቻሉ የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል መግለፃቸው ተነግሯል።
ወደየቀያቸዉ የተመለሱ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የገጠማቸዉ ፈተና
ዶክተር ደብረፅዮን ጨምረውም በውሉ መሰረት እስካሁን ከፌደራል መንግስት ጋር ፖለቲካዊ ንግግር አለመጀመሩ፣ የተሰረዘ የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት አለመመለሱ እና ሌሎች ጉዳዮች ለአፍሪካ ሕብረቱ ተወካይ መግለፃቸው እና በአጠቃላይ የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ያለበት ሁኔታ አሳሳቢ በመሆኑ የአፍሪካ ሕብረት ፓነል በአፋጣኝ ተሰብስቦ ሊወያይ እንደሚገባ ጥሪ ማቅረባቸውም ተመላክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የህወሓት ከፍተኛ አመራር ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ዛሬ በፌደራል መንግስት ሹመት የተሰጣቸው ሲሆን፥ ፕሮፌሰሩ በትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስቴር ዴኤታ ሁነው እንዲሰሩ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ መሾማቸው ተገልጿል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻም በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ አቶ ጌታቸው ረዳን የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር