የህወሓት መሪ የኢትዮጵያ መንግሥትን ወቀሱ
ማክሰኞ፣ መስከረም 13 2018
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲነት ያገደዉ የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ለፓርቲያቸዉ ዕውቅና መንፈግ የፕሪቶሪያ-ደቡብ አፍሪቃ ዉስጥ የተደረገዉን ሥምምነት በቀጥታ መጣስ ነዉ አሉ።ዶክተር ደብረ ፅዮን ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግስት የሰላም ስምምነቱን እየጣሰ ነው በማለት ወቅሰዋልም።ህወሓት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች ህዝባዊ የተባሉ ስብሰባዎች እያደረገ ነዉ።
ህወሓት "የብሔራዊ አንድነት ዘመቻ" በሚል በተለያዩ የትግራይ አካባቢ ከአባላቱ እና ሌሎች አካላት ጋር እያደረጋቸው ያሉ ስብሰባዎች በዚህ ሳምንትም ቀጥለዋል። ህወሓት እንደሚለው "ህዝባችን እንደ ህዝብ ከቶ ገጥሞት ባለ አደጋ ዙርያ እየመከረ ነው" የሚል ሲሆን በእነዚህ መድረኮችን ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የፈረመው ስምምነት እንዲያከብር እና እንዲፈፅም፥ ከዚህ በተጨማሪ ከጦርነት አዋጅ እንዲቆጠብ ጥሪ እየተደረገ ነው ሲል አስታውቋል።
የህወሓት ስብሰባዎች
በእነዚህ ህወሓት እያደረጋቸው ያሉ ተከታታይ ስብሰባዎች የፖርቲው አባላት፣ የወጣቶች፣ ሴቶች እና ሌሎች አደረጃጀቶች፣ የቀድሞ ተዋጊዎች፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ ምሁራን እና ሌሎች እየተሳተፉ መሆኑ ተገልጿል። በመቐለ በተደረገ መድረክ የተናገሩት የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት እየጣሰ ነው በማለት የከሰሱ ሲሆን፥ በጦርነቱ ወቅት የነበሩ አንዳንድ ክልከላዎች አሁንም ትግራይ ላይ መቀጠላቸው ተናግረዋል። ለዚህም ነዳጅ ጨምሮ ሸቀጦች እንዳይገቡ ማድረግ፣ የውጭ ሀገር ዜጎች ወደ ትግራይ እንዳይጓዙ መከልከል እና ሌሎች ማሳያ ብለው አንስተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት የፈረመው ህወሓት ሆኖ ሳለ፥ የፌደራሉ መንግስት ህወሓትን እውቅና መንሳቱ በግልፅ ስምምነቱ የማፍረስ እርምጃ ሲሉ ከሰዋል።
የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን "ስምምነቱ ህወሓት ነው የፈረመው። እንደምታስታውሱት ህወሓትንም አላውቅም ብሏል። ሕጋውነት የለውም፣ ተሰርዟል ብሏል። ይህ ምን ማለት ነው ? የተፈራረምከው አካል አላውቅም ካልክ ውሉም የለም ማለት ነው በሌላ አገላለፅ። የኢትዮጵያ መንግስት የፕሪቶርያ ስምምነት ለማደናቀፍ ያላደረገው ነገር የለም። ህወሓትን አላውቅም ማለት በቀጥታ የሰላም ስምምነቱ የለም ማለት ነው" ብለዋል።
ከሰላም ስምምነቱ በኃላ የህወሓት ሕጋዊ ከመመለስ ጋር በተያያዘ ፓርቲው ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ የቆየ ሲሆን ባለፈው ዓመት መሰረዙ ማስታወቁ ይታወሳል።
ህወሓት የማፍረስ እንቅስቃሴ
ይሁንና ህወሓት ፖለቲካዊ ውይይት እንዲደረግለኢትዮጵያ መንግስት እና የፕሪቶርያ ውል አፈራራሚ ለሆነው አፍሪካ ሕብረት ጥሪ ሲያቀርብ ቆይቷል። ዶክተር ደብረፅዮን በተጨማሪም በውስጥና በውጭ ሐይሎች ህወሓት የማፍረስ ተግባራት ሲከወኑ መቆየታቸው ያነሱ ሲሆን ይህ እንቅስቃሴ ከሽፏል ሲሉም ገልፀዋል። ደብረፅዮን "ህወሓትን የማፍረስ ተግባር ከሽፏል። መጀመርያ ላይ በውስጥ መቆጣጠር ነበረ አላማው፥ በኃላ ላይ ግን ወደ ማፍረስ ተሸጋግሮ ነበር። ሁለት ህወሓት እየተባለም ይገለፅ ነበረ። ህወሓት አንድ ነው። ህወሓት ማፍረስ ሌላ የትግራይ ህዝብ የማጥፋት ስራ አካል ነው። የከዱት ሄደው የራሳቸው ሌላ ፓርቲ መመስረታቸው ግን የኛ ፓርቲ ድኖ እና ተስተካክሎ እንዲቀጥል ዕድል የሚከፍት ነው። አሁን ገጥሞን ያለ አደጋም ፓርቲያችን ይዘን ነው የምንወጣው። ህወሓት የፕሪቶርያ ውል ፈራሚ ነው፣ ከህዝቡ ጋር ሆኖም እየታገለ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የህወሓት ክፍፍል
ከህወሓት የተለዩ ከፍተኛ አመራሮች እና አባላት ብያንስ ሁለት ፓርቲዎች በቅርብ ግዚያት ያቋቋሙ ሲሆን በሌላ በኩል ወደ ትጥቅ ትግል የገቡም አሉ። ህወሓት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ በሚዘነዝራቸው ክሶች ዙርያ ምላሽ እንዲሰጡን በቅርቡ ጥያቄ አቅርበንላቸው የነበሩ የኢትዮጵያ የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ከበደ ደሲሳ፥ በፕሪቶሪያ ውል አፈፃፀም እንዲሁም ከህወሓት ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ዙርያ በከፍተኛ ባለስልጣናት ጭምር በተደጋጋሚ ማብራሪያ መሰጠቱ በመግለፅ ተጨማሪ ነገር ለመናገር እንደማይሹ ገልፀውልናል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ