1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዶክተር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ ልዩ መብት ተነሳ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 26 2015

በባለቤታቸው ስም ባላ ሦስት ወለል ቤት በ10 ሚሊዮን ብር አብረዋቸው በሰሩ ተቋራጮች በተሰጠ ገንዘብ መገዛቱ ፣ ሌሎች ሀብትና ንብረቶችም እንደተገኙባቸው ተጠቅሶ የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብት በአብላጫ ድምፅ ተነስቷል። ክሱን ያስተባበሉት ዶክተር ጫላ እጃቸውን ከተቃውሞ ይልቅ ለድምፅ ተአቅቦ ማንሳታቸው ግርምት ፈጥራል።

Äthiopien, Addis Abeba | Äthiopisches Parlament
ምስል Solomon Muchie/DW

የዶክተር ጫላ ዋታ ያለመከሰስ ልዩ መብት ተነሳ

This browser does not support the audio element.


የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ያረጋገጠው ነው የተባለውና በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ዶክተር ጫላ ዋታ ፈጽመውታል የተባለው የሙስና ወንጀል በምክር ቤቱ አደገኛ ልምድ መሆኑ እና ለሌሎች መማሪያ መዋል አለበት የሚል እምነት ተወስዶበታል።በመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል የተባሉት እኒሁ የምክር ቤት አባል የመንግሥት የግዢ ሕግ ከሚፈቅደው አሰራር ውጪ ከመሥራት ባለፈ ገቢ ማስገኛ በሚል ያልተገባ አማካሪ ድርጅት በማቋቋም ፣ በስማቸው ሕገ ወጥ ንግድ ፈቃድ በማውጣት ፣ ከሥልጣናቸው ውጪ ቀጥታ ግዢ በመፈፀም በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል የሚል ምርመራ ተደርጎባቸዋል።የሕግ ከለላ የማንሳት ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ማስረጃዎችን ጭምር መመርመሩንና ለድርጊቱ መፈፀም በቂ አመላካች ማስረጃ ማግኘቱን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ እጸገነት መንግሥቱ አብራርተዋል። ተጠርጣሪው የምክር ቤት አባል ዶክተር ጫላ ዋታ የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል። ከእሳቸው ጋር ተመሳጥሮ ሰራ የተባለው የግል ድርጅት ተብሎ የቀረበው የዩኒቨርሲቲው መሆኑን ፣ ክፍተቶች አሉ ከተባለም በሕግ ሊታይ ይችላል የሚልና መጣራት የሚችል ጉዳይ  መሆኑን ገልፀዋል።ቀጥታ ግዢ መፈፀሙን ያመኑት እኚሁ ልዩ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው ግለሰብ ወቅቱ የኮሮኖ ተኅዋሲ ፈጥሮት በነበረው ጫና ምክንያት በቅንነት የተፈፀመ መሆኑን ገልፀዋል።

እሳቸው ይህንን ቢሉም በባለቤታቸው ስም ባላ ሦስት ወለል ቤት በ10 ሚሊዮን ብር አብረዋቸው በሰሩ ተቋራጮች በተሰጠ ገንዘብ መገዛቱ ፣ ሌሎች ሀብትና ንብረቶችም እንደተገኙባቸው ተጠቅሶ የምክር ቤት አባሉ ያለመከሰስ መብት በአብላጫ ድምፅ ተነስቷል። ይህ ውሳኔ ሲወሰን በምክር ቤቱ ተገኝተው የቀረበባቸውን ክስ ያስተባበሉት ዶክተር ጫላ የአፈ ጉባኤውን ድምፅ የመሰጠት ሂደት ተከትሎ እጃቸውን ከተቃውሞ ይልቅ ለድምፅ ተአቅቦ ማንሳታቸው ግርምት ፈጥራል።በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በፈቃዳቸው ሥራ መልቀቃቸው በተገለፀው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ቦታ በዳኞች አስተዳደር ጉባኤ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ተንተርሰው ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይዘሮ ሌሊሴ ደሳለኝን በፕሬዝዳንትነት ፣ ወይዘሮ ዛኻራ ዑመርን በምክትል ፕሬዝዳንትነት እንዲሾሙ አቅርበው ምክር ቤቱ ሹመቱን በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል።የፌዴራል ከፍተኛም ሆነ ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች መሪዎች በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቁ የሚለው ጉዳይ መደጋገሙ ግን ከምክር ቤት አባላት ጥያቄ አስነስቷል።
"ይህ ጉዳይ ከዳኝነት ነፃነት ጋር የሚያያዝ ነገር የለውም ወይ ? ምናልባት አሥፈፃሚው አካል በዳኞች ነፃነት ውስጥ ጣልቃ እየገባ ሊሆን አይችልም ወይ"? ፍርድ ቤቶች የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በፖሊስ እየተጣሱ መሆኑም በአስረጂነት ቀርቧል። ዋና ዐፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ለዚህ አጭር ምላሽ ሰጥተዋል። "ሥራ መልቀቅ መብት ነው። በሕግም የተፈቀደ ነው"። የሚል ። ከወራት በፊት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ባተመሳሳይ በገዛ ፈቃዳቸው ሥራ መልቀቃቸው ተገልጾ በምትካቸው ሌሎች ሰዎች መሾማቸው ይታወሳል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW