1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህዳሴ ግድብ ድርድር ክሽፈት፣ የግብፅ «ዛቻ»

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 10 2016

የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ እንዳሉት ግብፅ ከእንግዲሕ እንደማትደራደር አስታዉቃለች። ድርድሩ ከከሸፈ በኋላ ግብፅ ያወጣችዉን መግለጫ የኢትዮጵያዉ ዋና ተደራዳሪ «ዛቻ መሰል፣ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ» ብለዉታል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ «በቅርቡ ይጠናቀቃል» ተባለ
የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ በከፊልምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የሕዳሴ ግድብ ድርድር ከሸፈ- የኢትዮጵያና ግብፅ ይወቃቀሳሉ

This browser does not support the audio element.

 ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ በምታስገነባዉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግዙፍ ግድብ ሰበብ ከግብፅና ሱዳን ጋር የገጠመችዉን ዉዝግብ ለማስወገድ አዲስ አበባ ዉስጥ የተደረገዉ አራተኛዉ ዙር የሶስትዮሽ ድርድር ያለዉጤት አበቃ። የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ እንዳሉት ግብፅ ከእንግዲሕ እንደማትደራደር አስታዉቃለች። ድርድሩ ከከሸፈ በኋላ ግብፅ ያወጣችዉን  መግለጫ የኢትዮጵያዉ ዋና ተደራዳሪ «ዛቻ መሰል፣ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ» ብለዉታል።ኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብያለችዉን የኃይል ማመንጫ መገንባት የጀመረችዉ በ2003 ነዉ።ግንባታዉ ሲጀመር በአምስት ዓመት ይጠነቀቃል የተባለዉ ግድብ ዘንድሮም በ13 ዓመቱ አልተጠናቀቀም።ግድቡ በሙሉ አቅሙ መስራት ሲጀምር 6 ሺሕሜጋዋት ኤሌክትሪክ ያመነጫል ይባላል። 

ድርድሩ ለምን ያለ ስምምነት ተቋጬ? 

ኢትዮጵያ ፣ ሱዳን እና ግብጽ አዲስ አበባ ውስጥ ባደረጉት አራትኛ ዙር የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር 16 አንቀጾች ካሉት የመደራደሪያ ሰነድ የውኃ ክፍፍልን በሚመለከተው ስድስተኛው አንቀጽ ላይ ስምምነት ባለመደረሱ ያለ ውጤት ስለመበተኑ የኢትዮጵያ የግድቡ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለ ዛሬ በሰጠት አጭር መግለጫ ተናግረዋል። 

ዉኃ ከሚፈስበት የሕዳሴ ግድብ አንዱምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

"ኢትዮጵያ የወንዙን ውኃ በፍትሕ እና በእኩልነት የመጠቀም ፣ አብሮ የማደግና ቀጣናዊ ትስስር መፍጠር በሚያስችል መልኩ የመጠቀም ፍላጎትና አቋሟን ብታራምድም ፣ ከግብጽ በኩል "በድርድር እና በስምምነት ሥር የማይሆን እና ዘላቂ መፍትሔ የማያመጣ ፣ ሀገሮቻችንን ችግር ውስጥ የሚከት ዓይነት ስምምነት እንዲፈረም ያለ ጥብቅ ፍላጎት በመኖሩ ችግሩ ሊፈታ አልቻለም" ሲሉ ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ የተደረገው  የሚኒስትሮች ድርድር ያልተሳካበትን ምክንያት ገልፀዋል። አምባሳደር ስለሺ "ከመደራደር ውጪ ሌላ አማራጭ የለም" የሚለው አሁንም በቀጣይም የኢትዮጵያ አቋም መሆኑን አብራርተዋል። 

"ፍትሕን እና እኩልነትን መሰረት አድርገን እንጠቀም ነው ያልንው" ያሉት ዋና ተደራዳሪው ሆኖም ግብጽ ቀደም ብሎ አለኝ በምትለው የውኃ ድርሻ መሰረት ኢትዮጵያ የውኃ ድርሻ የምትለውን ፈርማ እንድትሰጣት አቋም በመያዛቸው ድትድሩ ያለ ውጤት ለመጠናቀቁ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የየሀገራቱ የውኃ ድርሻ በግልጽ ያልተቀመጠ ሆኖ ሳለ ግብጽ የውኃ ድርሻየ በሕግ ፀንቶ ይሰጠኝ በሚለው መከራከሪያ በመጽናቷ ድርድሩ ላይ ችግር መፍጠሩንም ኃላፊው ገልፀዋል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ድርቅ በሚከሰትበት ወቅት ወደ ታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት የምንለቀው የውኃ መጠን የኢትዮጵያን የወደፊት የመልማት እድል በሚገድብ መልኩ እንዳይሆን በሚል አቋሟን ስለማራመዷም አብራርተዋል።

"አጠቃላይ የድርድሩ ይዘት ቀደም ብሎ በተቀረጹት የመደራደሪያ መርሆች መሰረት ሀገራቱ የየራሳቸውን አቋም እና ፍላጎት የሚያንፀባርቁበት ሆኖ ብዙ መሻሻሎች የታየበት ሆኖ ቀጥሎ ነበር።" በዚህም በተወሰኑት ላይ መግባባት ላይ ስለመደረሱ ፣ ከነበረበት ላይ መሻሻል ማሳየቱን እና በተወሰኑት ላይ ደግሞ ልዩነት መኖሩን ጠቅሰዋል። እስከ 6ኛው የመደራደሪያ አንቀጽ ጥሩ ተጉዘን በዚህኛው ላይ ግን ከፍተኛ ልዩነት ነበር ያሉት አምባሳደር ስለሺ የድርቅ ሁኔታን የሚመለከተው እና የውኃ ክፍፍልን የሚመለከተው ይህ አንቀጽ ላይ መግባባት ላይ መድረስ አለመቻሉን ዘርዝረዋል።

የግብጽ መግለጫ "ዛቻ" ያለበት ነው

ግብጽ የድርድሩን በስምምነት አለመቋጨት ተከትሎ ትናንት ባወጣችው መግልጫ በአዲስ አበባ ውስጥ የተካሄደው ድርድር ውጤት አልባ ሆኖ የመጠናቀቁ ምክንያት ኢትዮጵያ መፍትሔ የተባሉና በግብጽ በኩል የቀረቡ መፍትሔዎችን ውድቅ በማድረጓ መሆኑን በመዘርዘር ከሳለች። 

አምባሳደር ስለሺ በቀለ በግብጽ መግለጫ "ዛቻ የመሰለ" ነገር መኖሩን ጠቅሰው ችግሩ ከድርድር ውጪ በሌላ አማራጭ የማይፈታ መሆኑን ገልፀዋል። የአፍሪካ ሕብረት በቀጣይ ጉዳዩን ወደፊት የሚያስኬደው ሊሆን ይችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

"የአፍሪካ ሕብረት ጉዳዩን የያዘው በመሆኑ ይህንንም አይነት ድርድር ሙሉ እውቅና ያለው እና ድጋፍ የሚሰጥበት ነው። እንደ አስፈላጊነቱ የአፍሪካ ሕብረትም በቀጣይ ጉዳዩን ወደፊት የሚያስኬደው ሊሆን ይችላል" ሲሉ ያብራሩት ዋና ተደራዳሩው ይህ "አንዱ አማራጭ ነው። ወይም ደግሞ ሦስታችንም ሀገሮች አንድ ላይ ሆነን እንደጀመርነው ድርድሩን ጫፍ ማድረስ ያስፈልጋል" ብለዋል።

ይህንን ለማሳካትም ኢትዮጵያ ፍላጎትና አቋሟን ለጎረቤት ሀገራት እና ለሌሎች በማስረዳት ዲፕሎማሲያዊ ጥረቷን እንደምትቀጥል አብራርተዋል። "ግድቡ ከ 94 በመቶ በላይ የመጠናቀቅ ደረጃ ላይ ደርሷል" ሲሉም ዋና ተደራዳሪው አምባሳደር ስለሺ በቀለ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አምባሳደር ስለሺ በቀለምስል Solomon Muchie/DW

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ "ግብጽ አራተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ ድርድር መጠናቀቅ አስመልክታ ያወጣችው መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት እና የአፍሪካ ሕብረት ቻርተሮችን የጣሰ እንዲሁም የኢትዮጵያ አቋም ተዛብቶ የቀረበበት" መሆኑን ገልጿል። ሚኒስቴሩ ግብጽ አሁንም በውኃው አጠቃቀም ዙሪያ የቅኝ ግዛት ዘመንን ኢትዮጵያን ያገለለ ስምምነት የምታራምድ መሆኑን በመግለጽ ኢ ፍትሓዊ መሆኑን ገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

እሸቴ በቀለ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW