1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህገ-ወጥ አዘዋዋሪ ሰለቦች መብት ጉዳይ

ሰኞ፣ ሐምሌ 24 2015

በሰው የመነገድ ወንጀል ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ የተሟላ ድጋፍ እና ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ። በሰው መነገድ ወንጀል ተሳታፊዎች ማታለል ደርሶባቸው ከሀገር ከወጡ በኋላ ተጎጂ ዜጎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት ለብዝበዛና ለሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተጋለጡ መገንዘቡን አመልክቷል።

Äthiopien Menschenrechtskommission
ምስል Solomon Muche/DW

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መግለጫ

This browser does not support the audio element.

 

በሰው የመነገድ ወንጀል ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ የተሟላ ድጋፍ እና ጥበቃ ሊደረግላቸው  ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጠየቀ። ኮሚሽኑ በሶማሌ ክልል ቶጎ ውጫሌ አካባቢ በሚገኝ የፍልሰተኞች ምላሽ መስጫ ማዕከል በሰው መነገድ ወንጀል ተሳታፊዎች ማታለል ደርሶባቸው ከሀገር ከወጡ በኋላ ተጎጂ ዜጎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለሥነ - ልቦና ቀውስ፣ ለገንዘብ ብዝበዛ እና ለሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተጋለጡ መገንዘቡን አመልክቷል።

በተመሳሳይ በደቡብ ክልል ባደረገው ክትትል ሕፃናት ለዚህ ወንጀል በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ መሆናቸውን፣ በዚህም ምክንያት ለአካል ጉዳት፣ ለሥነ-ልቦና ቀውስ፣ ለጾታዊ ጥቃቶች እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚጋለጡ ከተጎጂ ሕፃናት እና ቤተሰቦቻቸው መረዳቱን ኮሚሽኑ ገልጿል።

በሰው መነገድ፣ ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ወደ ውጭ ለሥራ መላክ ዜጎችን ለወንጀል ተጋላጭ እያደረጋቸው የመሆኑ አሳሳቢነት የገለፀው ፍትሕ ሚኒስቴር ችግሩን ለመፍታት የሚረዳ ያለውን ረቂቅ ሥልት - ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ "ግለሰቦችን ለብዝበዛ በማስገደድ፣ በመጥለፍ፣ በማታለል ወይም በኃይል በመመልመል፣ በማጓጓዝ፣ በማሸጋገር፣ በመቀበል፣ ወይም ማስጠለል የሚል ፍቺ በተሰጠው እና በሰዎች በተለይም በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚደርሰውን በሰው የመነገድ ወንጀል ለመከላከል፣ ለመግታትና ለመቅጣት የወጣውን የፓሌርሞ ፕሮቶኮል ፈራሚ ነች ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሰው የመነገድ ወንጀል ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያስከትል እና የተጎጂዎችን ነጻነት እና ክብር የሚገፍ ነው ብሏል። የወንጀል ፈጻሚዎቹ ዋና ዓላማም ሰዎችን በግዳጅ ሥራ ማሠራት፣ በልመና፣ በወሲባዊ ብዝበዛ፣ በሰውነት አካል ክፍል ስርቆት፣ በእገታ ክፍያ ወይም ቤዛ እና በሌሎች ድርጊቶች ገንዘብ ማግኘት መሆኑን አመልክቷል።

ኮሚሽኑ በሰው የመነገድ ወንጀል ፈጻሚዎች ተታለው ከሀገር ከወጡ በኋላ ተጎጂዎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ ለሥነ-ልቦና ቀውስ፣ እና ለገንዘብ ብዝበዛ እና ለሌሎች የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እንደሚጋለጡ ለመገንዘብ መቻሉን በመግለጽ መንግሥትም ሆነ ድርጊቱን በመግታት ዙሪያ የሚሠሩ አካላት የተናበበ ሥራ እንዲያከናውኑ ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለወንጀሉ ተጎጂዎች የሚደረገው ድጋፍ እና ጥበቃ በተደራጀ እና በተቀናጀ መልኩ ሊተገበር ይገባል ያለው ኮሚሽኑ በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የማቆያ ቤቶችን በመገንባት፣ ተደራሽ ማኅበራዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና የጤና አገልግሎት በማመቻቸት፣ እንዲሁም የወንጀሉ ሰለባዎች ለደረሰባቸው ጉዳት በሚገባ የሚካሱበት የተሟላ አሠራር እንዲኖርም ጠይቋል።

በኢትዮጵያ የወንጀሉ አሳሳቢነት ደረጃ ምን እንደሚመስልም ወይዘሮ ራኬብን ጠይቀናል። ኢትዮጵያ በሰው የመነገድ እና ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርን የሚከለክል አዋጅ አጽድቃለች። ይህ ችግር ዜጎችን ላላሰቡት ወንጀል ተጋላጭ እያደረጋቸው መሆኑን ያስታወቀው ፍትሕ ሚኒስቴር ዘላቂ መፍትሔ ያመጣል ያለውን ረቂቅ ሥልት - ስትራቴጂ ማዘጋጀቱን አስታውቋል። ከሰሞኑም በጉዳዩ ላይ ምክክር አድርጎበታል።

ሰለሞን ሙጬ

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW