1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሕግ እና ፍትሕኢትዮጵያ

የኖላዊት እገታና ግድያ፤የኤሌክትሪክ ዋጋ ጭማሪ፤ከአፍሪቃ ወጣቶች 60 በመቶው መሰደድ መፈለጋቸው

ዓርብ፣ ጳጉሜን 1 2016

«በኢትዮጵያ ምድር የሚከበር፤የሚፈራ፤ዋስትና የሚሰጥ የሕግ ተቋም አለን? እውነት ኢትዮጵያ ወስጥ ተጠያቂነት አለ? የሕግ አስፈጻሚ የሚጠየቅብት አሰራርስ አለን? ሕግ ተርጓሚውስ ለሕዝበ ምን ያህል ታማኝነት አለዉ? የሚሰጠው ውሳኔ በህዝብ ዘንድ ተማዓኒነት ኖሮት ያውቃል?ማን ይመዝነዉስ?» የሚሉ ጥያቄዎችን አከታትለው ያቀረቡት ብርሀን እጅጉ ሰማኝ

Äthiopien Stadt Gonder
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

የኖላዊት እገታና ግድያ፤የኤሌክትሪክ ዋጋ ጭማሪ፤ከአፍሪቃ ወጣቶች 60 በመቶው መሰደድ መፈለጋቸው

This browser does not support the audio element.

የህጻን ኖላዊት እገታና ግድያ

በሁለት ዓመትዋ ህጻን ኖላዊት ዘገየ ላይ ባለፈው ሳምንት በጎንደር ከተማ የተፈጸመው እገታና ግድያ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እጅግ አነጋጋሪ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።  አጋቾቿ ኖላዊትን ለመልቀቅ አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሰጣቸው ጠይቀው ወላጆቿ ያሰባሰቡትን 200 ሺህ ብር ለመቀበል ከተስማሙ በኋላ ገንዘቡን ቢወስዱትም በሰረቋት በሦስተኛው ቀን ገድለው ጥለዋት መሰወራቸው ነው የተገለጸው።  በዚህ ዘግናን ወንጀል ላይ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተሰጡ አስተያየቶች ውስጥ አንዱ «የጎንደር ከተማ አስካሁን ባለን መረጃ መሰረት መንግስት የሚያስተዳድረው፣ የመንግስት መከላከያ ኃይል ያለበትና በተደጋጋሚ ጎንደር ከተማ ሰላም እንደሆነች መንግስት እየገለፀ ፣ ይህን የመሰለ አስከፊ ወንጀል ሲፈፀም ማየትና መስማት፣ መንግስት ምን ያህል የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ እንዳልቻለ ያሳያል፤በማለት መንግሥትን በመውቀስ የሚጀምረው አበበ ተሰማ ወሮታ በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት ነው።በአስተያየቱ «፣በአማራ ክልል ጦርነት፣  ንፁሃን ይታገታሉ፤ንፁሃን ይገደላሉ፤ ለዚህ ደግሞ በተለይ የመንግስት የፀጥታ መዋቅር የሚያስተዳድራቸው  ከተሞችና መዋቅሮች ውስጥ የሚደርሱ ግፎች በገለልተኛ አካል መመርመር ይኖርባቸዋል፤በማለት መፍትኄም አቅርበዋል። 


« በኢትዮጵያ ምድር የሚከበር፤የሚፈራ፤ዋስትና የሚሰጥ የሕግ ተቋም አለን? እውነት ኢትዮጵያ ወስጥ ተጠያቂነት አለ? ሕግን ያላከበረ፤ ያላስከበረ የሕግ አስፈጻሚ የሚጠየቅብት አሰራርስ አለን? ሕግ ተርጓሚውስ ለሕዝበ ምን ያህል ታማኝነት አለዉ? የሚሰጠው ውሳኔ በህዝብ ዘንድ ተማዓኒነት ኖሮት ያውቃል?፡፡ማን ይመዝነዉስ?» የሚሉ ጥያቄዎችን አከታትለው ያቀረቡት ብርሀን እጅጉ  ሰማኝ ፣የኢትዮጵያ አምላክ ፍርዱ ሳይዘገይ ይድረስልን ፡፡እውነት በሃሰት፤ ሃሰት በእውነት ተሸፋፍኗልና ለእኛም እውነታዉን ይግለጽለን  ሲሉ ተምጽነዋል።
ንጉሱ አይናለም በአጭሩ « በጣም ያሳዝናል፣ ኦ እግዚኦ ክፋቶች ጭካኔዎች መለያየቶች በዙ! ምህረትህን አውርድ!»በማለት ፈጣሪን ጠይቀዋል ። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት የታሪፍ ጭማሪ በአዲስ ዓመት
ወለገን ተክሌ  «ግን አይዘገንናቸውም ገዳዮቹ አሁን ያንን ገንዘብ ሊበሉት ነው የእውነት ይበላላቸዋል ? ምን አይነት ስብዕና የተላበሱ ሰዎች ቢሆኑ ነው አቤት ጭካኔ! እግዚአብሔር መዓቱን ያውርድባቸው ሲሉ ረግመዋቸዋል።


እገታና ግድያውን በመቃወም በቁጣ ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከመንግሥት የፀጥታ ኃይል ጋር ተጋጭተው የፀጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃ ፣ 4 ሰዎች መገደላቸውንና ሌሎች መቁሰላቸውን የህፃን ኖላዊት የቅርብ ዘመድ ለዶቼ ቬሌ ተናግረዋል። በጎንደሩ እገታና ግድያ «የመንግሥት ፀጥታ ኃይላት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም» ሲል ከትናንት በስተያ የገለጸው የአማራ ክልል መንግሥት በህጻኗ እገታና ግድያ የተጠረጠሩ 14 የፀጥታ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል። «እንዲህ ነው እራስን ዘወር ብሎ ማየት ሁሌም ቢሆን ችግሩ ካልተፈታ እና ካልታወቀ የችግሩ ፈጣሪ አብሮን አለ ማለት ነው ። ማለት ሰርቆ እንደማፋለግ! ማለት ካለ በኋላ፤ ግን ዛሬ ማን ከእንቅልፋችሁ ቀስቅሷችሁ ነው? የሚለው አባ ዘቫጋዲያስ በሚል የፌስቡክ ስም የተሰጠ አስተያየት ነው። አማራ አጥናፉ ደግሞ ስጋት አላቸው።« ምን ዋጋ እለው!  በተለያየ ጥቅማጥቅም ፣ድጋሚ ይፈታሉ» ሲሉ ጥጣሪያቸውንም አክለውበታል። 

 

ከአፍሪቃዊ ወጣት 60 በመቶው መሰደድ ይፈልጋል 

ሜሊያ በተባለችው የስፓኝ ባህረ ሰላጤ በሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ የተኮለኮሉ የአፍሪቃ ስደተኞች ምስል dpa


60 በመቶ ወጣት አፍሪቃዊ መሰደድን የሚፈልግ መሆኑን በዚህ ሳምንት ይፋ የሆነ አንድ ጥናት አስታውቋል። መቀመጫውን  ጆሐንስበርግ-ደቡብ አፍሪቃ ያደረገዉ አንድ ተቋም በዚህ ጉዳይ ላይ  ከኢትዮጵያ እስከ ደቡብ አፍሪቃ በሚገኙ ሐገራት የሚኖሩ ዕድሜያቸዉ ከ18 እስከ 24 ዓመት የሚደርስ 5 ሺሕ 600 ወጣቶችን በአካል አነጋግሯል ። ወጣቶቹም በየሐገራቸዉ መንግስታት ላይ ያላቸዉ እምነት በጣም አነስተኛ መሆኑን ጠቁሟል። በጥናቱ ዉጤት መሠረት በየሐገሩ የተስፋፋዉ ሙስናና ብልሹ አሠራር የወጣቶቹን የወደፊት ተስፋ አጨልመዋል ከተባሉ ምክንያቶች ዋነኛዎቹ ናቸው። በዚሕም ምክንያት ወጣቶቹ ሲሆን ወደ ሰሜን አሜሪካ፣ ካልሆነ ብሪታንያ፣ፈረንሳይና ጀርመንን ወደ መሳሰሉ የምዕራብ አዉሮጳ ሐገራት መሰደድ ነው የሚፈልጉት። 
ዶቼቬለ በፌስቡክ ባቀረበው በዚህ መረጃ ላይ አስተያየቱን የሰጠው ሀፍቶም ኢትዮጵያዊ የተባለ የፌስቡክ ተከታይ «አረ ምን 60% ብቻ 100% በሉት ይችን አፍሪካ ለመሪዎች ትተን ሁላችን በተሰደድን ነበር ፣ክፍት መንገድ ቢገኝ።»ብሏል። ጌች የአፄዎቹ በአጭሩ «በተለይ ኢትዮጵያ» በማለት ሀሳባቸውን አስፍረዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ15 ሚሊየን ብር በላይ መዝብረዋል በሚል የተጠረጠሩ በቁጥጥር ሥር እየዋሉ ነው
ብዙአየሁ አየልኝ አዳነ «እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ቢጠይቁ ዘጠና በመቶ ተሰዳጅ ነን ።ለምን የምንወጣበትን መንገድ አትፈልጉልንም? የሚል ጥያቄ በማከል ተሳልቀዋል። ሰጠኝ አዲሴ ደግሞ ምክንያቱን ደርድረዋል።  «መሮናል አሞናል ቸግሮናል »ሲሉ ። ሳሚ ጌቱ የጥናት ውጤቱን «መራር እውነታ» ሲሉት ዮናትን አማረ አጎናፍር  «ከ60% በላይ ነው። ተስፋ የሚጣልበት አህጉር አይደለም ምክንያቱም የአፍሪካ መሪዎች ሁሉም በሚባል ደረጃ ለህዝባቸው ከፍተኛ ንቀት ያላቸው፣ በሙስና የተበላሹ ፣ ተላላኪዎች ፣ የራሳቸውን ጥቅም በማሳደድ ማሰቢያቸው የጠበበ ፣ ህዝብ ድምፁን እንዳያሰማ የሚያፍኑ ፣ የሚገሉ ፣ ለትንሽ ግርግር መሣሪያ የሚጠቀሙ ፣ በአስተሳሰብ 21ኛውን ክፍለዘመን የማይመጥኑ ፤ የሚለውን ወቀሳቸውን ካዘነቡ በኋላ  ታዲያ ምን ተስፋ አድርገን ፣አገር አለን ብለን እንቀመጥ? ባለችን እድሜ የተሻለ ነገር እንፈልጋለን።» በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል። 


ሀብቶም ኤርጊቾ ደግሞ እንደ VIP ዓይነት ሕይወት  የሚመሩት ፖለቲከኞች ፣የሚሰሩት ለኅብረተሰቡ ሳይሆን ለራሳቸውና ለቤተሰቦቻቸው እድገት  ነው። በሙስና የባለገ ባለሥልጣን እድገት ይሰጠዋል። እናም የመንግሥት ሠራተኞች ከአገር የመውጣት እድል ቢያገኙ በነዚህ ሙሰኛ መሪዎች ምክንያት አንዳቸውም ሀገራቸው አይቀመጡም ብለዋል። « ቅጥር፣እድገት ፣ዝውውር ፣የትምሕርት እድል፣የመኖሪያ ቤት እጣ፣ ሹመት ኧረ የሚገኝ ነገር ሁሉም በዕውቀት ሳይሆን በዘመድ፣ በቤተሰብ፣ በጎሳ ሆኖ በትምህርት ቤት ውሎ ውጤት ሰቅሎ ፣ተሸላሚ የነበረው፣ ሥራ ፍለጋ አራትና አምስት ዓመት በሚንከረተትባትና ፣በጠመዝማዛ መንገድ ባልተማረበትና ባልለፋበት ማዕረግ የሚጠራው ተንዳላቆ በሚኖርባት በሀገራችን ኢትዮጵያ ፣የጥናቱ ውጤት 100% እንደሚሆን አልጠራጠርም።»ያሉት ደግሞ መ/ር አሸናፊ ናቸው። 

ምዕራብ ወለጋ ዞን የሚገኝ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶምስል Negassa Desalegn/DW

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የዋጋ ጭማሪ 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመጪው 2017 ዓ.ም አንስቶ በየሦስት ወሩ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ከዚህ በፊት በሰዓት 50 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች ይከፍሉት ከነበረው 27 ሳንቲም በአዲሱ ተመን 35 ሳንቲም ይከፍላሉ ተብሏል።  ጭማሪው አነስተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረገ ፤ እና የመክፈል አቅማቸዉን ከግምት ያስገባ ነዉ ተብሏል። ከአዲሱ አመት ከመስከረም አንድ ቀን ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ስለተባለዉ ስለ አዲሱ የዋጋ ጭማሪ ዶቼቬለ አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የተለያዩ አስተያየቶቻቸውን አካፍለዋል።  የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አግልግሎት የታሪፍ ጭማሪ በአዲስ ዓመት
ሀብቴ አደራጀው አስናቀው «የመብራት ኃይል የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት ፣ ዋጋ ጭማሪ ሆነ ማለት ነው?ሲሉ ፤ሀና አበበ  «በአጠቃላይ መንግስት እንኳን ደስ ያለችው እያለ የሚሰራው ነገር ህዝቡን ያማረረ ፣ኑሮ ከአቅሙ በላይ እንዲሆን እንጂ የሚሰራው ለዜጎቹ ምንም ያደረገው ማሻሻያ የለም።»ካሉ በኋላ
«ሰው በልቶ ማደር እያቃተው በላይ በላይ ይጨመራል ፣በአጠቃላይ  ለመንግስት እና ለሚኒስትሮቹ ምቾት ካልሆነ በቀር ለዜጎች አንድም ጥሩ ነገር አልሰራም»በማለት ሀሳባቸውን ደምድመዋል።
ታሪኩ ፀጋዬ ደግሞ  «የህዳሴው ግድብ ለታሪፍ ጭማሪ ምክንያት ነው ወይስ እሱም በዶላር ጭማሪ ሰበብ ይሆን? በሃገራችን  ዋጋ ይጨምራል እንጂ አይቀንስም ማለት ነው??» ሲሉ ጠይቀዋል።
ደረጀ ተስፋዬ «በመጀመርያ ደረጃ መብራቱን በአግባቡ መቼ አሰራጩ እና ነው ዋጋ የሚጨምሩት !!!! »ሲሉ ያሬድ ታደሰ «እኛ እንዲያውም ብልጭ ድርግም አያለ ሁለት ሶስት ቀን ስለማይመጣ ከከፈልነው ላይ መልስ ይሰጡናል ብለን ነበር።» በማለት ተሳልቀዋል።


ኂሩት መለሰ

እሸቴ በቀለ 


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW