1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችኢትዮጵያ

የሆሮ ጉዱሩ አሙሩ ወረዳ ጥቃት ተጎጂዎች ስጋት

ሥዩም ጌቱ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 27 2018

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በአገምሳ ከተማ እና ዙሪያው ባሉ ቀበሌዎች ላይ ሰኔ 23 የተፈጸመ የታጣቂዎች ጥቃት በነዋሪው ላይ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል። ልጃቸው የተገደለባቸው አባት ጥቃት በተፈጸመበት ቀን የቤት እንስሳትን ጨምሮ የንብረት ዘረፋ መፈጸሙን ተናግረዋል።

የተተኮሰ ጥይት ቀልህ
በኦሮሚያ ክልል ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በአገምሳ ከተማ እና ዙሪያው ባሉ ቀበሌዎች ላይ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. የተፈጸመ የታጣቂዎች ጥቃት በነዋሪው ላይ ትልቅ ስጋት ፈጥሯል። ምስል፦ Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የሆሮ ጉዱሩ አሙሩ ወረዳ ጥቃት ተጎጂዎች ስጋት

This browser does not support the audio element.

በላይ የተባሉ የሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ ነዋሪ አንዱን ልጃቸውን ያሳጣቸውን የማክሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2018 ኣ.ም. ጥቃቱን ህልም የሚመስል አስደንጋጭ ክስተት ሲሉ ገልጸውታል፡፡ “እኔ ልጄ ነው የተጎዳብኝ፤ ስሙ ሰለሞን በላይ ይባላል፡፡ የተገደለብኝ ልጄ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበር፡፡ እሱ አራተኛ ልጄ ነው፡፡ ነቀምት ትምህርት ላይ ቆይቶ ተመርቆም የራሱን ስራ ፈጥሮ ነበር የምኖረው፡፡ ህይወቱን ለማትረፍ ብርቱ ጥረት ብናደርግም በአምቦላንስ እጦት ለተሻለ ህክምና ወደሻምቡ ሆስፒታል ስናደርሰው ደሙ ፈሶ በማለቁ ህይወቱን ማትረፍ አልተቻለንም” ብለዋል፡፡

የተጎጂው ማህበረሰብ እሮሮ

ስለ ማክሰኞው ጥቃት አስተያየታቸውን ያከሉት የጥቃቱ ተጎጂ ብዙውን ሰው ባዶ እጁን ያስቀረ ነው ሲሉም አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡ “ከማለዳው 11፡30 ነበር ማናችንም ከእልቅልፋችን እንኳን ሳንነቃ በተኩስ እሩምታ የነጋልን፡፡ የሚተኮሰው ብሬንና ስናይፐር ነው፡፡ ስንነሳ አንድም የጋማ ከብት በበረት አልነበረም፡፡ ተዘርፈው ተነድተው ማለት ነው፡፡ ሱቅ ተሰብሮ ከፍተኛ ሀብት ተዘርፏል፡፡ ከ400 በላይ የሚገመት የጋማ ከብት ነው የተነዳው፡፡ እኔ ደግሞ ልጄን ነው ያጣሁ” ሲሉ በጥቃቱ የደረሰው ጉዳት ጥልቅ አንድምታ ያለው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ሌላው አስተያየት ሰጪ የአገምሳ ከተማ ነዋሪ በፊናቸው፤ “የአሁኑ ጥቃት ለብዙ ሰው ከአራት አምስት አመታት ግድም በፊት ተፈትሮ የነበረውን ቁስል የነካ ነው፡፡ ብዙ ህይወት ነው የተመሰቃቀለው በዚህ፤ ሶስት አመታት ከዚህ በፊት ከደረሰው አደጋ በማገገም ላይ የነበሩ ሰዎች በሙሉ የሰው ህይወት እና የንብረታቸው ጉዳት ከባድ አደጋን ያስከተለ ነው፡፡ እስካሁን ሶስት ሺህ ግድም የቤት እንስሳት መዘረፋቸው ነው የሚነገረው፡፡ 13 ሰዎች ህይወተቻው አልፏል፡፡ እስካሁን በሻምቡ ሆስፒታል የመኖር አለመኖሩ እጠፈንታቸው ገና ያልተረጋገጠና በዚሁ አገምሳ ጤና ጣቢያ ቀለል ያሉ ጉዳቶችን እስካሁን እየተመላለሱ እየታከሙ ያሉም ብዙ ናቸው” ሲሉም አስተያየታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

ቀጣዩ የማህበረሰቡ ስጋት

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በቀጣይም በፊታቸው የተደቀነው አደጋ እና ስጋት የዋዛ አይሆንም፡፡ ይህም ስጋት የሚመነጨው በተደጋጋሚነት ካጠቃቸው ጥቀቃትና ከማያቧራው የአከባቢው አለመረጋጋት ዳፋ ውጤት እንደሆነ ያስገነዝባሉ፡፡ “ህዝቡ ጭንቀት ውስጥ ነው ያለው፡፡ አሁን ከትናንት ወዲያ በ25 ሓሙስ እለትም ተኩስ ከፍተው በቂ የመንግስት የጸጥታ ኃይል በዚህ ስላለ ነው ወደ ኋላ የተመለሱት፡፡ በቂ የመንግስት ፀጥታ ኃይል ከዚህ ከተማ ዞር ባለ ቁጥር ህብረተሰቡ ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብቶ ነው የሚመጣውን የሚጠባበቀው” ብለዋል፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ በማክሰኞው የታጣቂዎች ጥቃት ከተዘረፉ የጋማ ከብቶችም ሆኑ ንብረቶች እስካሁን የተመለሰ አንድም ነገር የለም፡፡ ማህበረሰቡም ጉልበተኞች ባሏቸው የታጠቁ አካላት የተዘረፉትን ንብረቶቻቸውን እንዳጡ ከመቀመጥ ሌላ አማራጭ እንዳላገኙ በማስረዳት፤ “ትልቅ ስጋት ውስጥ ነን አሁን፡፡ በዚህ በኪረሙ ወረዳ ሀሮ እና ሌላው ርገቴ በሚባሉ በሁለት አቅጣጫዎች ትልቅ ስጋት ተደቅኖብናል፡፡ እንደ ህብረተሰቡ እራሳችንን ከአደጋው ለመጠበቅ በቻልነው መጠን እየጣርን ነው”  ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ ባለፈው ማክሰኞ በአሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ እና አከባቢው ላይ ደርሷል ስላለውና በቀጣይም አሉብን ስላሉት የፀጥታ ስጋትን በማስመልከት ዶይቼ ቬለ ለአገምሳ ከተማ አስተዳዳሪ ለአቶ ተስፋዬ ደውሎላቸው አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ለአሙሩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አምሳሉ እና ለሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ሚሬሳ ፊጤም የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ በመደወል ምላሻቸውን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት እስካሁን አልተሳካም፡፡

ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2018 ዓ.ም “የፋኖ ታጣቂዎች ናቸው” የተባሉ ኢትዮጵያ መንግስትን የሚወጉ የታጣቂዎች ቡድን በአገምሳ ከተማ አደረሱ በተባለው ጥቃት ቢያንስ የ13 ሰዎች ህይወት ማለፉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡  

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW