1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሊቨርፑል እና የፖርቹጋል ተጫዋች የነበረው ዲዬጎ ዮታ እና ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ቀብር ተፈጸመ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 28 2017

የሊቨርፑል እና የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ቁልፍ ተጨዋች የነበረው ዲዬጎ ዮታ እና የወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ። በመኪና አደጋ ባለፈው ሐሙስ ሕይወታቸውን ያጡት ወንድማማቾች ሥርዓተ-ቀብር የተፈጸመው በፖርቹጋል ምሥራቃዊ ፖርቶ በምትገኘው ጎንዶማር የተባለች ከተማ ውስጥ ነው።

ዲዬጎ ዮታ እና ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ሥርዓተ ቀብር
በመኪና አደጋ ባለፈው ሐሙስ ሕይወታቸውን ያጡት ወንድማማቾች ሥርዓተ-ቀብር የተፈጸመው በፖርቹጋል ምሥራቃዊ ፖርቶ በምትገኘው ጎንዶማር የተባለች ከተማ ውስጥ ነው።ምስል፦ Manu Fernandez/AP Photo/picture alliance

የሊቨርፑል እና የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ቁልፍ ተጨዋች የነበረው ዲዬጎ ዮታ እና ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ። በመኪና አደጋ ባለፈው ሐሙስ ሕይወታቸውን ያጡት ወንድማማቾች ሥርዓተ-ቀብር የተፈጸመው በፖርቹጋል ምሥራቃዊ ፖርቶ በምትገኘው ጎንዶማር የተባለች ከተማ ውስጥ ነው።

የሊቨርፑል አጥቂ የነበረው ዲዬጎ ዮታ እና በፖርቹጋል ሁለተኛ ሊግ ፓናፊል ለተባለ ክለብ ይጫወት የነበረው ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ሥርዓተ ቀብር ቤተሰቦቻቸው፣ አድናቂዎቻቸው እንዲሁም የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን እና እንግሊዙ ሊቨርፑል እግር ኳስ ቡድን አባላት ተገኝተዋል።

የፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን አባላት የሆኑት ሩበን ዲያዝ፣ በርናርዶ ሲልቫ እና ሩበን ኔቬዝ በሥርዓተ-ቀብሩ ላይ ከተገኙ መካከል ናቸው። የሊቨርፑል ተጨዋቾች የሆኑት ቨርጂል ቫን ዳይክ፣ አንዲሮብርትሰን እና የቡድኑ አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ተገኝተዋል።

ዮታ እና ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ ሕይወታቸውን ያጡት ባለፈው ሐሙስ ዕኩለ ለሊት በስፔን ዛሞራ ግዛት የሚጓዙበት ላምቦርጊኒ ቅንጡ ተሽከርካሪ ከመንገድ ወጥቶ በእሳት በጋየበት አደጋ እንደሆነ ሬውተርስ ዘግቧል። ፖሊስ የላቦርጊኒው ጎማ ፈንድቷል የሚል ጥርጣሬ እንዳለው ይፋ አድርጓል።

ዮታ በአደጋው ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ከረዥም ጊዜ የፍቅር ጓደኛው ጋር ትዳር በመሠረተ በ11ኛው ቀን ነው። ጥንዶቹ አብረው በቆዩባቸው ጊዜያት ሦስት ልጆች አፍርተዋል።

ከጎሮጎሮሳዊው 2020 ጀምሮ ለሊቨርፑል 182 ጨዋታዎች የተሰለፈው ዲዬጎ ዮታ 65 ግቦች ከመረብ አሳርፏል። ከቡድኑ ጋር የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እና የኤፍኤ ካፕ ዋንጫዎችን አሸንፏል። ዮታ ሊቨርፑልን ከመቀላቀሉ በፊት ለአትሌቲኮ ማድሪድ፣ ፖርቶ፣ ለእንግሊዙ ዎልቭስ ተጫውቷል።

ከፖርቹጋል ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት የአውሮፓ የሀገራት ዋንጫ (Nations League) አሸናፊ ነበር።

ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላሕ የዲዮጎ ዮታን ሞት “ለመቀበል አስቸጋሪ” እንደሚሆን ገልጿል። ምስል፦ Attila Kisenedek/AFP

የ28 ዓመቱ እግር ኳስ ተጨዋች ሞት ለፖርቹጋላውያን፣ የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ አጋሮቹ እና የስፖርት አፍቃሪያን ከፍተኛ ድንጋጤ እና ሐዘን የፈጠረ ነው። ሊቨርፑል የዮታን ሞት “ከክለቡ የሚሻገር አሳዛኝ አደጋ” ብሎታል።

የሊቨርፑል ደጋፊዎች ከአንፊልድ ስታዲየም ውጪ በመሰብሰብ ሐዘናቸውን ገልጸዋል። ግብጻዊው ሞሐመድ ሳላሕ የዲዮጎ ዮታን ሞት “ለመቀበል አስቸጋሪ” እንደሚሆን ገልጿል። 

የዲዬጎ እና የወንድሙን አሳዛኝ ሞት በመስማታቸው ልባቸው እንደተሰበረ የገለጹት የቀድሞው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርመናዊው የርገን ክሎፕ ዮታ ድንቅ ተጫዋች ብቻ ሳይሆን “ጥሩ ጓደኛ፣ አፍቃሪ እና ተንከባካቢ ባል እና አባት” እንደነበር መስክረዋል።

ሐዘኑን ለመግለጽ ትክክለኛ ቃላት ለማግኘት መቸገሩን የገለጸው የሊቨርፑል እግር ኳስ ክለብ አጋሩ ጎዲ ጋብኮ ከዮታ ጋር መጫወት እንደሚያስደስተው እንደ ሰው እንደሚያደንቀው በኢንስታግራም ጽፏል።

“አሁን ቅርቡ በብሔራዊ ቡድኑ አብረን ነበርን። ትዳር የመሠረትከው አሁን ነበር” ያለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ የዮታ ሞት “ትርጉም አይሰጥም” ሲል በስሜታዊ ቃላት ሐዘኑን ገልጿል። የ40 ዓመቱ ሮናልዶ እንደ ብዙ የስፖርት በተለይም የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ለዮታ ቤተሰቦች፣ ለባለቤቱ እና ለልጆቹ መጽናናትን ተመኝቷል።

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW