1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የልዩ ኦዲት ምርመራ ሲሠራ ችግር እየገጠመው መሆኑን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 17 2017

ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ፣ ዛሬ የዓመቱን የምርመራ ውጤቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ጉድለት የተገኘባቸው ተቋማት አመራሮች በፓርላማው አለመገኘት እና ተቋማቱ በሚፈጽሟቸው ጥፋቶች ተጠያቂ አለመደረጋቸው ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል።

መስሪያ ቤታቸዉ ከዚሕ ቀደም በምርመራ የደረሰበትና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበት የ20 ቢሊዮን ብር ጉድለት እስካሁን አልተመለሰም።አጥፊዎቹም አልተጠየቁም
ወይዘሮ መሠረት ዳምጤ።የኢትዮጵያ የፌደራል ዋና ኦዲተር።ዋና ኦዲተሯ ዛሬ እንዳሉት ባልደረቦቻቸዉ ምርመራ በሚያደርጉበት ወቅት ማስፈራራትና እስራት ይደርስባቸዋል።ምስል፦ Solomon Mucheu/DW

የልዩ ኦዲት ምርመራ ሲሠራ ችግር እየገጠመው መሆኑን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ

This browser does not support the audio element.

ከመደበኛ የገንዘብ እና የክዋኔ ኦዲት የሚለየውን የልዩ ኦዲት ሥራ ሲያከናውን ኦዲት ወይም የሒሳብ እና የሥራ ምርመራ ከሚደረገው ተቋም ብቻ ሳይሆን ከተቆጣጣሪ ተቋማት ጭምር ችግር እየገጠማቸው መሆኑን የፌደራል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ተናገሩ።ዋና ኦዲተሯ  ተቋማቸው ልዩ ምርመራ እንዲያደርግ ተጠይቆ ሲያበቃ ምርመራው በጊዜ አልቀረበም በሚል መርማሪዎች ላይ እሥር መፈፀሙን ለዚህ በማሳያነት ገልፀዋል።

የበጀት ሒሳብ ምርመራው ከዓመት ዓመት መሻሻልየታየበት መሆኑን የተናገሩት ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ፣ ዛሬ የዓመቱን የምርመራ ውጤቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ጉድለት የተገኘባቸው ተቋማት አመራሮች በፓርላማው አለመገኘት እና ተቋማቱ በሚፈጽሟቸው ጥፋቶች ተጠያቂ አለመደረጋቸው ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል።የፌዴራል ዋና ኦዲተር የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የ2016 በጀት ዓመት የሒሳብ ምርመራ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ በ2015 እና ከዚያ በፊት ጉድለት ያገኘበት እና እንዲመለስ የጠየቀው 20 ቢሊዮን ብር ቢኖርም ሦስት ቢሊዮን ያልሞላ ብር ብቻ ተመላሽ መደረጉን አስታውቀዋል።

 

በ24 መሥሪያ ቤቶች፣ በ9 የገቢዎች እና በ3 የጉምሩክ ቅ/ጽ/ቤቶች 51 ሚሊዮን ብር መመሪያን ሳይከተል ክፍያ መፈፀሙ፣ በ16 የፌዴራል መ/ቤቶችና በ1 የጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሥራ ላይ ለሌሉ እና ከሥራ ለተሰናበቱ ሠራተኞች 408,462 ብር ክፍያ መፈፀሙም ተጋልጧል።የምክር ቤት አባላት ይህንን የመሰሉ የመንግሥት ሀብትና በጀት ብክነቶች በየ ዓመቱ ተደጋግመው እንደሚቀርቡ በመግለጽ ተጨባጭ እርምጃ ለምን እንደማይወሰድ ጠይቀዋል። ይህም ብቻ ሳይሆን ጉድለት የተገኘባቸው ኦዲት ተደራጊ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎቻቸው በፓርላማው ተገኝተው ጉዳዩን አለማድመጣቸው "ለምን"? የሚል ጥያቄን አስነስቷል።

 

በጀት በየዓመቱ ለአሥፈፃሚ ተቋማትየሚያፀድቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብክነት በሚፈጽሙ ተቋማት እና አመራሮች ላይ እርምጃ እንዲወስድ በማሳሰቢያ ጭምር ተጠይቋል። ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ተቋማቸው የሒሳብ እና የሥራ ክንውን ምርመራ አድርጎ ጉድለቶችን ለምክር ቤቱ ከማቅረብ በዘለለ "ሌላ ሥልጣን የሌለው" መሆኑን ደጋግመው ገልፀዋል።ከመደበኛ ኦዲት የተለየውን ልዩ የኦዲት ምርመራ የሚያደርገው ይሄው ተቋም በዚህም የሰዎችን ስም ጭምር ጠቅሶ እርምት እንዲወስዱ ለፍትሕ እና የፀጥታ ተቋማት ውጤቱን የሚያቀርብበት ነው። እንደ ዋና ኦዲተሯ አገላለጽ ሥራው በመርማሪዎች ላይ "የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር የሚጠይቅ ነው" 

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚገኝበት ሕንፃ።ምክር ቤቱ ዛሬ የ2016 የዋና ኦዲተር ዘገባ አድምጧልምስል፦ Solomon Muchie/DW

ዋና ኦዲተር መሠረት ዳምጤ ይህ ስራቸው መርማሪዎችን ለእሥር፣ ምርመራ የሚደረግባቸው የግል ተቋማት ደግሞ "ሽጉጥ ይዘው" ጭምር ወደ መሥሪያ ቤታቸው መሄድ ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል።21 ቢሊዮን ብር ክፍያ የተፈፀመባቸው በ11 ተቋማት ውስጥ ያሉ የ131 ፕሮጀክቶች የግንባታ ሥራ ከ1ወር እስከ 11 ዓመት ድረስ መጓተታቸው በምርመራው ውጤት ተመላክቷል።

3.6 ቢሊዮን ብር ያልተሰበሰበ ቀረጥና ታክስ መኖሩ በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል። በሌላ በኩል የክፍያ መመሪያና ተመን ሳይኖር ክፍያ መፈፀም፣ የመንግሥትን የግዥ አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ ያልተከተለ ግዢ መፈፀም መኖሩ ለምክር ቤቱ ተገልጿል።

ሶሎሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW