የልጃቸውን ገዳይ ከእስር ያስፈቱት የሀዋሳው የሀገር ሽማግሌ
ሐሙስ፣ መስከረም 19 2015
የዛሬው የባህል መድረክ ዝግጅት ላለፉት 20 ዓመታት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ቢሮ ከፍተው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለ ልዩነት በነፃ የሽምግልና እና የእርቅ አገልግሎት የሚሰጡ የሀገር ሽማግሌን እንግዳ አድርጓል።
በሰው ልጆች መስተጋብር ውስጥ ግጭት እና አለመግባባት የሚያጋጥም ጉዳይ ነው።ይህንን አለመግባባትን በኃይል ለመፍታት መሞከር ዘላቂ መፍትሄ ሲያመጣ አይታይም። በመሆኑም ግጭት እና አለመግባባትን ለመፍታት ሰላማዊ ሥርዓት መኖሩ ለሰው ልጆች አስፈላጊ ነው። ከነዚህ መካከል ባህላዊ የግጭት አፈታት የሽምግልና ዘዴ አንዱ ነው።በዛሬው የባህል መድረክ ዝግጅት በሽምግልና ስራ በርካታ አመታትን ካስቆጠሩ አንድ የሀገር ሽማግሌ ጋር ቆይታ አድርጓል መልካም ቆይታ።
የ86 ዓመቱ አዛውንት አቶ ማቲዎስ ደስታ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው። ትውልድ እና እድገታቸው በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ሲሆን ትዳር መስርተው ልጆች ወልደው የሳሙት ግን አሁን በሚኖሩበት ሀዋሳ ከተማ ነው።አቶ ማቲወስ ስለልጆቻቸው ሲናገሩ «በልጅ ተባርኪያለሁ ደርዘን ሙሉ ናቸው» ማለት ይቀናቸዋል። ቀደም ሲል የብረታ ብረት ስራ ይሰሩ የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን የግንባታ ስራ ፈቃድ በማውጣት ላለፉት ለሰላሳ ዓመታት በቤት እና በሕንጻ ግንባታ ስራ ላይ በመሰማራት ነው ቤተሰባቸውን ሲያስተዳድሩ የቆዩት። በሐዋሳ ከተማ እና በተለያዩ ቦታዎች በርከት ያሉ ግንባታዎችን አከናውነው በሙያው ጥሩ ስም አግኝተዋል።ልጆቻቸውም በእግራቸው ተተክተው በዚሁ ሙያ እየሰሩ ይገኛሉ። በዚህ የተነሳ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ የሚያውቃቸው «ኮንትራክተር» በሚለው ስማቸው ነው።
የሀዋሳ ከተማ አቶ ማቲዎስን የሚያከብራቸው በጥሩ የግንባታ ስራቸው ብቻ አይደለም።በከተማው አንቱ የተባሉ ስመጥር አስታራቂ ሽማግሌም ናቸው።ላለፉት 20 ዓመታት በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ቢሮ ከፍተው ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለ ልዩነት በነፃ የሽምግልናና የእርቅ አገልግሎት ይሰጣሉ።
አቶ ማቲወስ ይህንን የሽምግልና እና የእርቅ አገልግሎት የሚሰጡት በተጋጩት ወገኖች ስምምነት ሲኖር እና ሽምግልናውን ከፈለጉ ብቻ መሆኑንም ገልፀዋል።ለዚህ ሥራዬ ደመወዝ የማገኘው ከሰማይ ነው የሚሉት አቶ ማቲዎስ ፤ በዚህ ሁኔታ ላለፉት 20 ዓመታት ባለትዳሮችን ጨምሮ በርካታ ባለጋራዎችን በእርቅ እና በይቅርታ ወደ ሰላም መልሰዋል።
አቶ ማቲዎስ ሌሎችን ማስታረቅ እና ማሸማገል ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም አርአያ ሆነው አንድ አስገራሚ ነገር ፈፅመዋል። ነገሩ እንዲህ ነው ።በ1998 ዓመተ ምህረት አንድ ምሽት ከስራ ውለው ወደ ቤት ሲገቡ ከ12ቱ የአብራካቸው ክፋይ ልጆቻቸው መካከል አራተኛ የሆነው እስራኤል ማቲወስ መሞቱ ተነገራቸው።የሞቱን መንስኤ ሲያጣሩ ደግሞ በስለት ተወግቶ በሰው እጅ መገደሉን ሰሙ።
ከጊዜ በኋላ የልጃቸው ገዳይ በሰራው ወንጀል አስር ተፈርዶበት ወደ ማረሚያ ቤት ወረደ።
አቶ ማቲዎስ ግን በልጃቸው ሞት አምርረው ቢያዝኑም ሀዘንና ቂም ይዘው መቀመጥን ግን አልፈለጉም።የልጃቸውን ገዳይ ማረሚያ ቤት ድረስ ሄደው በመጠየቅ በሞተው ልጄ ምትክ አንተ ልጄ ነህ በማለት ይቅር ለእግዚያብሔር ማለታቸውን ይገልፃሉ። ይቅርታ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የልጃቸውን ገዳይ እግሩንም አጥበዋል።
ከዚያም ዶክመንት አዘጋጅተው ጉዳዩ ወደ ይቅርታ ቦርድ እንዲሄድ አድርገው የልጃቸው ገዳይ መፈታቱን ገልፀዋል።’ይቅርታ ማድረጋቸውን የሰሙት የገዳይ ወገኖች ውለታ ለመመለስ ምን እናድርግልዎት የሚል ጥያቄ የጠየቋቸው ቢሆንም እሳቸው ግን ምንም አይነት ካሳ አለመቀበላቸውን ይናገራሉ።ለመሆኑ የልጀዎን ገዳይ ከይቅርታው በኋላ አግኝተውት ያውቃሉ ወይ? ያነሳንላቸው ጥያቄ ነበር።ከዚህ በኋላ ከገዳዩም ይሁን ከቤተሰቦቹ ጋር ተገናኝተው እንደማያውቁ ገልፀው።«ተመልሶ አልመጣም አንገናኝም ምክንያቱም እግር ያጠበው የሆነ ነገር ሊያደርግ ነው ብሎ ፈርቶኝ ይሆናል እኔ አላውቅም። ስለዚህ አልተገናኜንም።» ካሉ በኋላ «እሱንም እግዚአብሄር ይጠብቀው»በማለት ጥሩ ተመኝተውለታል።አቶ ማቲዎስ አያይዘውም «ይቅርታ ሰላምን ይሰጣል። ይቅር ካላችሁ ይቅር አትባሉም ይላል የእግዚአብሄር ቃል።ስለዚህ እኔ ይቅር ካልኩ እግዚአብሄር እኔን ይቅር ይላል» በማለት ገልፀዋል ።
የአቶ ማቲወስ ሁለተኛ ልጅ ቡሩክ ማቲዎስ የሟቹ የእስራኤል ማቲዎስ የሁለት ጊዜ ታላቅ ነው።እርሱ እንደሚለው በወቅቱ በታናሽ ወንድሙ ሞት ሀዘን እና ቁጭት አድሮበት የነበረ ቢሆንም፤ አባቱ የወንድሙን ገዳይ ይቅር ማለታቸው ግን በቤተሰቡ ቂም እና በቀል እንዳይቀጥል በማድረጉ ቅሬታ አልፈጠረበትም።
ብሩክ አይይዞም አባቴ ለሌሎች ሰዎች የሚያደርገው ሰላም የማውረድ እና እርቅ የመፍጠር ስራ መላ ቤተሰቡን ጭምር የሚያስደስት እና የይቅርታ ልብ እንዲኖረን አድርጓል ሲልም ይገልፃል ።
በሐዋሳ ከተማ በመልካም ተግባራቸው የሚታወቁት የ86 ዓመቱ አዛውንት አቶ ማቲዎስ ደስታ የትዳር አጋራቸውን በሞት አጥተዋል። እርጅናና ህመምም ተጫጭኖኛል ይላሉ። ይሁን እንጅ የተጣላ እና የተጋጨ ሰው ካለ አሁንም ቢሆን አንተም ተው አንቺም ተይ ከማለት፣ ሰዎችን ከማስታረቅ እና ከማሸማገል እንዲሁም ወርደው እግር ከማጠብ አሁንም አልቦዘኑም። በመኖሪያ ቤታቸው የሚገኘው የእርቅ ቢሯቸውም ሽምግል እና እርቅ ለሚፈልጉ ሁሉ አሁንም ክፍት ነው።
ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ታምራት ዲንሳ
ፀሀይ ጫኔ