የልጅነት ልምሻ ማለትም ፖሊዮን ከዓለም የማጥፋት ጥረት
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 13 2016
የልጅነት ልምሻ ማለትም ፖሊዮ በዛሬው ዕለት በመላው ዓለም ሲታሰብ መሪ ቃሉ በሽታውን ለማጥፋት የተደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት እና ልጆችን ከዚህ በሽታ ለመከላከል የክትባትን አስፈላጊነት ማጉላት ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በርካታ ሃገራት የልጅነት ልምሻን ከምድራቸው ማጥፋት ተሳክቶላቸዋል። ፖሊዮን ከመላው ዓለም ለማጥፋት የሚደረገው ጥረት ከየት ተነስቶ የት ደረሰ?
የልጅነት ልምሻ ማለትም ፖሊዮን የማጥፋቱ ጥረት
ግብፅ ውስጥ የተገኘው አንድ እግሩ ልምሾ የሆነ ሰውን የሚያሳይ ጥንታዊ የድንጋይ ላይ ሥዕል የልጅነት ልምሻ ማለትም ፖሊዮ ከክርስቶስ ልደት በፊትም እንደነበር አመላካች ተደርጎ ተወስዷል። ሥዕሉ ከ1580 እስከ 1350 ዓመተ ዓለም ባሉት ጊዜያት የተሣለ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው መረጃው የሚያመለክተውና በዚህም ፖሊዮ እጅግ ብዙ ሺህ ዘመናትን ተሻግሮ የመጣ በሽታ ለመሆኑ ማመላከቻ ተደርጓል። ለረጅም ዓመታት መፍትሄ ባለመገኘቱ ከባድ የማኅበረሰብ የጤና ችግር ሆኖ የኖረው። የልጅነት ልምሻ በተለይ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢንዱስትሪ ባደጉት ሃገራት ሳይቀር በርካታ ሺህ ሕጻናትን ሽባ በማድረጉ ምክንያት እጅግ የሚፈራ ተላላፊ በሽታ ሆኖ ቆይቷል። ሆኖም በጎርጎሪዮሳዊው 1950 ዓም እና 1960ዎቹ ላይ የተገኘው መከላከያ ክትባት የፖሊዮ ተሐዋሲን መቆጣጠር ብሎም ከእነዚህ ሃገራት ይኽን የጤና ችግር ለማጥፋት ማስቻሉ ለታሪክ ተመዝግቧል። በወቅቱ ቀድሞ በኢንዱስትሪው ያደገው ዓለም ከፖሊዮ ጋር ሲታገል በአዳጊ ሃገራት የልጅነት ልምሻ እንደዋና የጤና ችግር ተደርጎ አልታየም ነበር። ክትባቱ ውጤቱን ካስመዘገበ ከ10 ዓመታት በኋላ በአዳጊ ሃገራት የተካሄደ ቅኝት ሽባነትን የሚያስከትለው ይኽ በሽታ እዚህም መንሰራፋቱ ተደረሰበት። ከዚህ በኋላ ነው በ1970 እና 80ዎቹ ዓመታት አዳጊ ሃገራት ፖሊዮን እንዲከላከሉ ለመርዳት በሃገራት የበሽታ መከላከያ መርሃግብር ውስጥ ክትባቱ ለሕጻናት መሰጠት ካለባቸው የመከላከያ ክትባቶች ውስጥ እንዲካተት የተደረገው። በጎርጎሪዮሳዊው 1985 ዓም የልጅነት ልምሻን የሚከላከለው ክትባት ለልጆች የመስጠት ዓለም አቀፍ ጥረት ሲጀመር በወቅቱ በየቀኑ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ልጆች ለሽባነት ይዳረጉ ነበር። በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አማካኝነት የክትባት ዘመቻው ተጠናክሮ ከዚያ ወዲህ ከ2,5 ቢሊየን በላይ ለሚሆኑ ልጆች ክትባቱን ማዳረስ ተችሏል። በዚህ ጥረትም የሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ ሃገራት በ1991 በተነሳሳው ፓን አሜሪካኒዝም እና ጤናን የመጠበቅ ቁርጠኝነት ከፖሊዮ ስጋት ነጻ ሲሆኑ፤ በ2002 መላው አውሮጳ ከዚህ የጤና ችግር መላቀቅ መቻሉን የዓለም የጤና ድርጅት መዝግቧል። የእስያ ሃገራት አብዛኞቹ ከልጅነት ልምሻ ስጋት ነጻ መሆናቸው ቢነገርም፤ አሁንም አፍጋኒስታን እና ፓኪስታን ውስጥ የጤና ችግሩ መኖሩ በተላላፊነቱ ምክንያት ስጋት እንደሆነ ነው። የአፍሪቃ ሃገራትም አብዛኞቹ ባካሄዱትና በቀጠለው የመከላከያ ክትባት ዘመቻ በጎርጎሪዮሳዊው 2020 ላይ ከሁሉም የፖሊዮ አይነት ስጋት መላቀቃቸው ይፋ ሆኗል።
የዘመቻ ክትባት በፓኪስታን
ከእስያ ሃገራት በተለይ ሕንድ ከፖሊዮ ስጋት ነጻ መሆኗ ከተነገረ 12 ዓመታት ተቆጠረ። የዓለም የጤና ድርጅት ሕንድ ውስጥ የመጨረሻው የፖሊዮ ታማሚ መረጃ የተመዘገበው በጎርጎሪዮሳዊው 2011 ጥር 13 ቀን መሆኑን አመልክቷል። የተገኘውን ስኬት ዘላቂ ለማድረግም በየዓመቱ ለበርካታ ሚሊየን ሕጻናት ክትባቱ እየተሰጠ ነው። ከሁለት ዓመት በፊትም ሕንድ ለ159 ሚሊየን ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት መስጠቷ ተመዝግቧል። ምንም እንኳን ሕንድ በጥረቷ ብትቀጥልም ጎረቤቷ ፓኪስታን እና አፍጋኒስታን ዛሬም ከልጅነት ልምሻ ስጋት አለመላቀቃቸው የስኬቱን አስተማማኝነት ጥያቄ ውስጥ ከቶታል። ለበርካታ ዓመታት በዘለቀው ጸጥታ ችግር ምክንያት አፍጋኒስታን ውስጥ የጤና ባለሙያዎች እንደልብ ተንቀሳቅሰው መከላከያ ክትባቱን ማዳረስ አለመቻላቸው በእንቅፋትነት ይጠቀሳል። ፓኪስታን ውስጥ ደግሞ በተለይ ልጆቻቸው ክትባት እንዲወስዱ የማይፈልጉ ወላጆች ሕጻናቱን ለአካል ጉዳት እየዳረጉ መሆኑ እያነጋገረ ነው። የዓለም ትኩረት ያረፈበት ሁኔታው ያሳሰበው የፓኪስታን መንግሥት ባለሥልጣናት ታዲያ ዜጎች ሕጻናትን እንዲያስከትቡ ለማስገደድ ዘዴም የሕግ እርምጃም መውሰድ ጀምረዋል። የጤና መኮንን የሆኑት ዶክተር ኤሳን ገሃኒ ክትባቱ ለልጆች እንዲዳረስ የተጀመረውን ስልት ሲናገሩ፤ «በአካባቢው ፈቃደኝነት ከሌለ፤ በተለይ ልጆቻቸው እንዳይከተቡ የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ፤ የቅኝት ቡድናችንን በመጀመሪያ እናሰማራለን፤ ልጁን ለመከተብ እምቢተኞቹን ማሳመን ካልተሳካላቸው፤ የሕግ አካላትን እርዳታ እንጠይቃለን፤ ጉዳዩም ለፖሊስ ይነገራል፤ ምክንያቱም ይኽ ብሔራዊ ጉዳይ ነው፤ የመከላከያ ክትባቱን ለመስጠት ከጤና ዘርፉ ጋር የማይተባበር ካለ ሕግ ደግሞ የበኩሉን እርምጃ ይወስዳል።» ነው ያሉት። እሳቸው እንደሚሉት ከሆነም ፓኪስታን ከራሷ አልፎ ከጎረቤት አፍጋኒስታንም ይኽ ተላላፊ በሽታ ሊመጣባት መቻሉ ለእነሱ አሳሳቢ ሆኗል።
በአሁኑ ጊዜም የክትባቱ ዘመቻ በተለይ ልጆቻቸውን አናስከትም በማለት በሚታወቁት አካባቢዎች ላይ በማተኮር እየተካሄደ መሆኑንም ነው ያመለከቱት። ባለፈው ወር በአንድ የፓኪስታን ክፍለ ሀገር ባለሥልጣናቱ ፖሊዮን ለማጥፋት ለበርካታ አስርት ዓመታት የሚደረገው ጥረት ውጤት እንዲያስገኝ በሚል በቀየሱት አነጋጋሪ አዲስ ስልት ሕጻናት ልጆቻቸውን አናስከትብም የሚሉ ወላጆች በእስራት እንዲቀጡ ለመወሰን መገደዳቸው ተሰምቷል። ሲንዲህ የተባለው ክፍለ ግዛት አስተዳደር በወሰነው መሠረትም ልጁን የፖሊዮም ሆነ ሌሎች ለሕጻናት የሚሰጡ ክትባቶችን የማያስከትብ ወላጅ እስከ አንድ ወር ለማሰር መመሪያ አውጥቷል። የጤና ባለሙያዋ አሪባ ጃሜል በምትራበት አካባቢ አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ማስከተብ እንደማይፈልጉ ነው የምትናገረው።
ፑንጃም ግዛት የሚኖሩት አብዱል ቃድር ካን በፖሊዮ ምክንያት ለሽባነት የተዳረገ ልጅ አባት ናቸው። በእኔ ልጅ የደረሰው እንዳያጋጥማቸው ልጆቻቸውን ቢያስከትቡ ይበጃል በሚል ሰዎች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ ይመክራሉ። ፓኪስታን ከሳምንታት በፊት በጀመረችው በዚህ የክትባት ዘመቻ 44 ሚሊየን ሕጻናት የፖሊዮ መከላከያ እንዲያገኙ ለማድረግ አቅዳለች። ባለፉት አምስት ቀናት ብቻ 350 ሺህ የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት በመሄድ የፖሊዮን ጨምሮ ሌሎች ክትባቶችን መስጠት ተሳክቶላቸዋል።
የመከላከያ ክትባቱ ያስገኛቸው ለውጦች
የፖሊዮ ወረርሽኝ ቅኝትን በተመለከተ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር አጋማሽ አዲስ አበባ ላይ የተካሄደው ጉባኤ የቀጠለው የልጅነት ልምሻን መከላከያ የክትባት ዘመቻ እና የሚደረገው ክትትል ሁለተኛውን አይነት ፖሊዮ ምን ያህል ስኬታማ በሆነ መልኩ አስቀድሞ በማወቅ ለመከላከል ይረዳል የሚለውን ገምግሟል። በዚህም ጉድለት የታየበትን በመለየት በሽታውን የመከላከሉ ጥረት ተጠናክሮ የሚቀጥልበትን መንገድ መወያየቱን በኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ጽሕፈት ቤት አመልክቷል።
ፖሊዮ ተላላፊ በሽታ ሲሆን በተለይም ከሰው ወደ ሰው በተበከለ ውኃ እና በአይነ ምድር ቅንጣቶች አማካኝነት የሚዛመት መሆኑን የዓለም የጤና ድርጅት ያመለክታል። ከዚህ በተጨማሪም በተያዙ ሰዎች ሲስሉ እና ሲያነጥሱ በሚፈናጠቅ ፍሳሽ ምክንያትም ሊተላለፍ እንደሚችል የጤና ባለሙያዎች ያሳስባሉ። በሽታው በተለይ ከንጽሕና አጠባበቅ ጋር የተገናኘ እንደመሆኑ ድህነቱ በከፋባቸው አካባቢዎች ተንሰራፍቶ መቆየቱ ነው የታየው። በፖሊዮ የተያዘ ሰው በአብዛኛው ምንም የሚታይበት ምልክት የለም። አንዳንዶች ለጥቂት ቀናት የጉንፋን መሰል ምልክቶች እንደ ትኩሳት እና የጉሮሮ ህመም ሊያጋጥማቸው ይችላል፤ አንዳንዶች ደግሞ ህመማቸው ጠንከር ሊል ይችላል።
ከ20ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ አንስቶ በመላው ዓለም የተካሄደው የተጠናከረ የክትባት ዘመቻ በአሁኑ ወቅት 99 በመቶ የሚሆነውን የልጅነት ልምሻ ማለትም ፖሊዮ ስጋት መቀነሱ ዓለም አቀፍ የፖሊዮ ማጥፋት ዘመቻ ተነሳሽነት ይፋ አድርጓል። የበሽታው አምጪ ተሐዋሲ የመዛመት ፍጥነት እና የተለያየ አይነት መኖሩ ግን አሁንም ፖሊዮ ስጋትነቱ አብቅቷል ለማለት አያስደፍርም። ለዚህም ነው ዕድሜያቸው እስከ አምስት ዓመት የሆኑ ሕጻናት የመከላከያ ክትባቱን መውሰድ እንዳለባቸው የሚመከረው።
ሸዋዬ ለገሠ
ነጋሽ መሐመድ