የልጅነት ልምሻ ክትባት በአማራ ክልል
ዓርብ፣ መስከረም 30 2018
በአማራ ክልል ሁለት ዞኖች የታየውን የልጅነት ልምሻ (ፖሊዮ) ክስተት ተከትሎ ክልሉ ከ3 ሚሊዮን 500ሺህ በላይ ለሚሆኑ ህፃናት የፖሊዮ ክትባት መሰጠት መጀመሩን የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ተቋም አስታወቀ፡፡ ተቋሙ ባለፈው ዓመት ከ4 ሚሊዮን በላይ ህፃናት የፖሊዮ ክትባት መስጠቱን አመልክቷል፡፡ የአማራ ክልል ህብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ በጽ/ቤታቸው በሰጡት መግለጫ በአማራ ክልል በጎንደር ከተማ አስተዳደርና በደቡብ ጎንደር ዞን አንዳቤት ወረዳ ሁለት ህፃናት በልጅነት ልምሻ ቫይረስ መጠቃታቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ አንድም ሠው በልጅነት ልምሻ ቫይረስ ከተጠቃ እንደወረርሽኝ ይቆጠራል ያሉት አቶ በላይ፣ ሁለቱን አካባቢዎች በሚያዋስኑ በአራት ከተማ አስተዳደሮችና በአራት ዞኖች ከዛሬ መስከረም 30/2018 ጀምሮ ለተከታታይ 4 ቀናት የፖሊዮ መከላከያ ክትባት መሰጠት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ በሽታው በታየባቸው ጎንደር ከተማ አስተዳደርና ደቡብ ጎንደር ዞን አዋሳኝ የደቡብ ጎንደር ዞን ወረዳዎች፣ በሰሜን ጎጃም ዞን፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን፣ በማዕከላዊ ጎንደር ዞን፣ በደብረታቦር ከተማ አስተዳደር፣ በደብረማርቆስ ከተማ አስተዳደር፣ በባህር ዳር ከተማ አስተዳደርና በጎንደር ከተማ አስተዳደር ክትባቱ እየተሰጠ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አመልክተዋል፡፡
ክትባቱ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ህፃናት ይሰጣል
ከዚህ በፊት አብዛኛውን ጊዜ የልጅነት ልምሻ ክትባት የሚወስዱ እድሜያቸው ከ5 ዓመት በታች እንደነበር ያስታወሱት አቶ በላይ፣ አሁን የልጅነት ልምሻ ቫይረስ የተገኘባቸው ህፃናት ከተጠቅሰው እድሜ በላይ ሆነው በመገኘታቸው፣ ክትባቱ ከ10 ዓመት በታች ለሆኑ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሁሉም ህፃናት በተጠቀሱት ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች እንደሚሰጥ ገልጠዋል፡፡ በዚህ የክትባት ዘመቻ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ የጤና ቡድኖችና የጤና ባለሙያዎች ክትባቱን ለመስጠት መሰማራታቸውንም አመልክተዋል፡፡
በዘመቻው ከ26ሺህ በላይ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ
በዘመቻው፣ “ ...ከ8ሺህ 830 በላይ የጤና ቡድኖች፣ ከ3ሺህ 220 በላይ የየዘመቻው አስተባባሪዎችና አጠቃላይ ከ26ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች በዘመቻው የሳተፋሉ፡፡” በለዋል አቶ በላይ፡፡ በሌሎች የክልሉ ዞኖች ክትባቱ ለምን አይሰጥም ተብሎ ከጋዜጠኖች ለቀረበው ጥያቄ በተቋሙ የበሽታዎችና የጤና ሁኔታዎች ቅኝትና ምላሽ አስተባባሪ ወ/ሮ ፅጌረዳ አምሳሉ በሌሎቹ አካባቢዎች በተደረገ ቅኝት የልጅነት ልምሻ ስጋት ባለመኖሩ በሌሎቹ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የክትባት ዘመቻው አላስፈለገም ነው ያሉት፡፡ በ2017 ዓ ም በአማራ ክልል በሁለት ዙር በተደረገ የልጅነት ልምሻክትባት ለመከተብ ከታቀደው የህፃናት ቁጠር መካከል 99 ከመቶ መከተባቸውን አቶ በላይ ገልጠዋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ በመጀመሪያው ዙር ከ3 ሚሊዮን 800ሺህ ህፃናት በላይ ህፃናት ይልጅነት ልምሻ መከላከያ ክትባት ሲወስዱ በሁለተኛው ዙር ደግሞ 4 ሚሊዮን ህፃናት እንደተከተቡ ነው ያስረዱት፡፡
ለክትባቱ መሳካት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ተጠይቋል
ክተባቱ በትምህርት ቤቶችና ቤት ለቤት በመሆኑ ወላጆች፣ የሐይማኖት አባቶችና ሌሎችም አካላት ለክትባቱ መሳካት የራሳቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል፡፡ ዛሬ ክትባቱ በባህር ዳር ሲጀመር የተለያዩ የሐይማኖት አባቶች ወላጆች ህፃናቱን እንዲያስከትቡ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ በስንስርዓቱ ላይ የተገኙት የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጤና መምሪያ ኃላፊ ዓለም አሰፋ በከተማዋ 144ሺህ ህፃናት ክትባቱን ይወስዳሉ፡፡ ይልጅነት ልምሻ እግርና እጅን በማዛል ለከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚዳርግ በቫይረስ አማካኝነት የሚከሰት የጤና እክል ነው፡፡ አንድ አገር ከልጅነት ልምሻ ነፃ ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምስክር ወረቀት የሚሰጠው ለ3 ተከታታይ ዓመታት የተመዘገበ የፖሊኦ ተጠቂ ከሌለበት እንደሆንም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ የልጅነት ልምሻ በዓይነ ምድር በተበከለ ምግብና ውሀ ከሠው ወደ ሠው የሚተላለፍ በሽታ መሆኑን ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡
ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ