1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 29 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ ሐምሌ 29 2016

የፓሪስ ኦሎምፒክ ቀጥሏል ። በዐሥር ሺህ ሜትር የወንዶች ፉክክር የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ኢትዮጵያ በሴቶቹ አምስት ሺህ እና ስምንት መቶ ሜትር ፉክክር ምሽቱን ተጨማሪ ሜዳሊያ ትጠብቃለች ። ኖቫክ ጄኮቪች በሜዳ ቴኒስ ድል ተቀዳጅቷል ። በፓሪስ ኦሎምፒክ ትሪያትሎን የተሳተፉ አትሌቶች ከወንዙ ጋ በተገናኛ ለሕመም መዳረጋቸው ተዘቧል ።

ፎቶ ከማኅደር፦ ኢትዮጵያውያን፤ ኬንያውያን እና ኔዘርላንዳዊቷ ትውልደ ኢትዮፕያ ተፎካካሪዎች ምሽቱን በ5000 ሜትር ፍጻሜ ይጠበቃሉ
ፎቶ ከማኅደር፦ ኢትዮጵያውያን፤ ኬንያውያን እና ኔዘርላንዳዊቷ ትውልደ ኢትዮጵያ ተፎካካሪዎች ምሽቱን በ5000 ሜትር ፍጻሜ ይጠበቃሉምስል JAVIER SORIANO/AFP

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

የፓሪስ ኦሎምፒክ ቀጥሏል ። በዐሥር ሺህ ሜትር የወንዶች ፉክክር የብር ሜዳሊያ ያገኘችው ኢትዮጵያ በሴቶቹ አምስት ሺህ እና ስምንት መቶ ሜትር ፉክክር ምሽቱን ተጨማሪ ሜዳሊያ ትጠብቃለች ። የ37 ዓመቱ ኖቫክ ጄኮቪች የማታ ማታ በሜዳ ቴኒስ ድል ተቀዳጅቷል ። በፓሪስ ኦሎምፒክ የትሪያትሎን ተፎካካሪ ተሳተፉ አትሌቶች ከወንዙ ጋ በተገናኛ ለሕመም መዳረጋቸው ተዘግቧል ። በፓሪስ እና አካባቢዋ ወንዞችን ለማጽዳት ከ1.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ መውጣቱ ቀደም ሲል ተገልጦ ነበር ። 

የፓሪስ ኦሎምፒክ

በኦሎምፒክ ውድድር ታሪክ  የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በሲድኒ እና ቤጂንግ አራት አራት የወርቅ ሜዳሊያዎችን በማግኘት ያስመዘገባቸው ውጤቶች አመርቂ ተብለው ተመዝግበዋል ። ዛሬ ማታ በሴቶች የ5000 ሜትር እና የ800 ሜትር የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ለሜዳሊያ ይጠበቃሉ ። 

በ5000 ሜትር ሴቶች ፍጻሜ በዩጂን የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ጉዳፍ ፀጋዬ እና ኬኒያዊቷ የሪዮ ዴ ጄኔሮ ኦሎምፒክ ክብረወሰን ባለድል ቪቪያን ጄፕኬሚ ቼሩዮት ተሳታፊ ናቸው ። እነ መዲና ኢሳ እና እጅጋየሁ ታዬም ኢትዮጵያን ወክለው ይሳተፋሉ ። የኔዘርላንዷ ሲፋን ሐሰን እና ኬንያዊቷ ኪፕዬጎ ብርቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል ። በሴቶች 800 ሜትር የፍጻሜ ውድድር ኢትዮፕያ በፅጌ ዱጉማ እና ወርቅነሽ መለሠ ተወክላለች ። በርቀቱ የዓለም እና የኦሎምፒክ ክብረወሰኖች በቼኳ ጃርሚላ ክራቶችቪሎቫ 1983 ሙይንሽን እና በሩስያዊቷ ናዴዣኦሊዛሬንኮ በ198 ሞስኮ ኦሎምፒክ የተያዘ ነው ። የሁለቱም በጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ነው ።

ኢትዮጵያ በፓሪስ ኦሎምፒክ

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በብዛት የሚጠበቁበት  የፓሪስ ኦሎምፒክ  ፉክክር ቀጥሏል ። ኢትዮጵያ እስካሁን በወንዶች 10,000 ሜትር የፍጻሜ ፉክክር በበሪሁ አረጋዊ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች ። በፍጻሜው ስለተገኘው እና ስለሌሎች ውድድሮች ከፓሪስ ወኪላችን ሃይማኖት ጥሩነህ ጋ ቃለ መጠይቅ አድርገናል ወደዚያው እንለፍ ።

በርምጃ እና ውኃ ዋና ውድድሮችም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተፎካካሪ ነበሩ ። በተለይ  በአትሌት ምሥጋናው ዋቁማ  ስድስተኛ ደረጃ የተገኘበት የርምጃ ፉክክር ኢትዮጵያ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ ኦሎምፒክ ብቅ ያለችበት በመሆኑ ውጤቱ የሚወደስ ነው ። አትሌት ምሥጋናው ዋቁማ በቅርቡ በተኪያሄደው የአፍሪቃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የርምጃ ፉክክር ባለድል ነው ። በመላው አፍሪቃ ጨዋታዎች የኢትዮጵያ ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ሊና ዓለማየሁም በዋና ውድድር በፓሪስ ኦሎምፒክ መሳተፏም አበረታች ነው ።

ሰዎች በፓሪስ ኦሎምፒክ ወቅት በሉቭር ቆመው ሲመለከቱምስል Natacha Pisarenko/AP/picture alliance

ዩጋንዳዊው እንደምን ከኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች አፍትሎ ወጣ?

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች እስከ ውድድሩ መገባደጃ ድረስ በአብዛኛው ፊታውራሪ በነበሩበት የ10,000 ሜትር የወንዶች የፍጻሜ ፉክክር በአጨራረስ ብቃት ዩጋንዳ ወርቁን ከኢትዮጵያ ፈልቅቃ ወስዳለች ። በ10,000 ሜትር የዓለም ፍጻሜ የሁለት ጊዜ ባለድሉ ጆሹዋ ቺፕቼጌ በውድድሩ መገባደጃ ልክ እንደነ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ የአሯሯጥ ስልት በድንገት አፈትልኮ በመውጣት አሸናፊ ሁኗል ። ጆሹዋ ዓርብ ዕለት ያሸነፈውም 26 ደቂቃ ከ43.14 በመግባት ነው ።

በሪሁ አረጋዊም ጆሹዋን በመከተል ከኋላ ተፈትልኮ ከፊት ለፊቱ የነበሩትን አትሌቶች በመደረብ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል ። በጆሹዋ የተበለጠው በማይክሮ ሰከንዶች ሲሆን የገባበት ሰአት 26:43.44 ነው ። ምናልባትም በሪሁ አፈትልኮ የወጣበት ሁኔታ ቀድሞ የተከወነ ቢሆን ኑሮ ከጆሹዋ ቀድሞም በማሸነፍ ክብረወሰኑ ለእሱ ይሆን ነበር ። በዚህ ረገድ አትሌቶቹ በተናጠል አሰልጣኞች መሰልጠናቸው አስተዋጽዖ ሳያደርግ አይቀርም መባሉን ሃይማኖት ጠቁማለች ።  በፓሪስ ኦሎምፒክ አትሌቶቹ ለረዥም ጊዜ ከፊት ሆነው ውድድሩን ለመምራት ኃላፊነት የወሰደው ማነው የሚለውም እያነጋገረ ነው ። በ10,000 ሜትር የፍጻሜ ፉክክር ሰለሞን ባረጋ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ እና በሪሁ አረጋዊ ተሳታፊ ነበሩ ።

በፓሪስ ኦሎምፒክ ድል የተቀዳጁ አትሌቶች በከፊልምስል Li Jing/Xinhua/IMAGO

የሜዳ ቴኒስ

የ37 ዓመቱ የሜዳ ቴኒስ የምንጊዜም ብርቱ ተፎካካሪ ኖቫክ ጄኮቪች ስፔናዊውን ሮላንድ ጋሮስ በመርታት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል ። ሠርቢያዊው የሜዳ ቴኒስ ባለድል ስፔናዊውን የ21 ዓመት ወጣት የረታው ለሁለት ጊዜ  7-6 እና 7-6 በማሸነፍ ነው ።  ኖቫክ ጄኮቪች ለሠርቢያ ሁለተኛ ወርቅ ነው ያስገኘው ። ከትናንቱ ድል በኋላ ኖቫክ ጄኮቪች በደስታ ፊቱን በነች ፎጣ ሸፍኖ ሲንሰቀሰቅ እና እጆቹ ሲንቀጠቀጡ ታይቷል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2008 የቤጂንግ ኦሎምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ ካገኘ ወዲህ በኦሎምፒክ ድል ሲያስመዘግብ ይህ የመጀመሪያው ነው ።

የ37 ዓመቱ የሜዳ ቴኒስ የምንጊዜም ብርቱ ተፎካካሪ ኖቫክ ጄኮቪች ስፔናዊውን ሮላንድ ጋሮስ በመርታት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል ምስል Marijan Murat/dpa/picture alliance

ላለፉት ሦስት የኦሎምፒክ ውድድሮችም ማጣሪያውና ሳያልፍ በመቅረቱ ለ37 ዓመቱ አትሌት የትናንቱ የኦሎምፒክ ድል እጅግ በልዩ ሁኔታ የሚታይ ነው ።  የሐምሌ 22 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

የውኃ ዋና

የፓሪስ ኦሎምፒክ የወንዞች ተፋሰሶችን ከብክለት ለማጽዳት በሚል 1,5 ቢሊዮን ዶላር እንደፈሰሰ ተነግሮ ነበር ። ሆኖም በትሪያትሎን ተሳታፊ የነበሩ ተወዳዳሪዎች በባክቴሪያ የተነሳ ለሕመም መዳረጋቸው አነጋጋሪ ሁኗል ። ቤልጂየም ሰኞ ዕለት አንድተፎካካሪዋ በመታመሙ ዋና፤ ሩጫ እና ብስክሌት ግልቢያን በሚያጣምረው የትሪያትሎን ፉክክር ላይ አልተወዳደረችም ። የስዊትዘርላንድ፤ የኖርዌይ የትሪያትሎን ቡድን አባላትም በባክቴሪያ መታመማቸው ያ ሁሉ ገንዘብ የተከሰከሰበት የወንዙ ጥራት ጉዳይ አነጋጋቲነቱ ቀጥሏል ።

የፓሪስ ኦሎምፒክ የወንዞች ተፋሰሶችን ከብክለት ለማጽዳት በሚል 1,5 ቢሊዮን ዶላር እንደፈሰሰ ተነግሮ ነበርምስል Jasper Jacobs/Belga/dpa/picture alliance

ቡጢ

የአልጀሪያዋ ቡጢኛ የጾታ ጉዳይ በፓሪስ የኦሎምፒክ ውድድር ውዝግብ አስነስቷል ። አልጀሪያዊቷ ቡጢኛ ኢማኔ ከሊፋ እና የታይዋኗ ቡጢኛ ሊን ዩ-ቲንግ በፓሪስ ኦሎምፒክ መወዳደር ነበረባቸው አልነበረባቸው አጨቃጭቋል ። ሁለቱ ቡጢኞች ባለፈው ዓመት በተደረገው የዓለም የሴቶች የቡጢ ፍልሚያ ላይ የጾታ ብቃት መመዘኛዎችን አላሟሉም በሚል እገዳ ተጥሎባቸው ሳይወዳደሩ ቆይተው ነበር ። የዘንድሮው የፓሪስ ኦሎምፒክ የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ቅድመ ዝግጅት

የአልጀሪያዋ ቡጢኛ ከጣሊያናዊቷ ተጋጣሚ ጋ ያደረገችው ቡጢ የተጠናቀቀው አንድ ደቂቃም ሳይሞላ ነበርምስል Ciro Fusco/ZUMA Press/IMAGO

በተለይ በተክለ ሰውነት ገዘፍ ያለችው የአልጀሪያዋ ቡጢኛ ከጣሊያናዊቷ ተጋጣሚ ጋ ያደረገችው ቡጢ የተጠናቀቀው አንድ ደቂቃም ሳይሞላ ነበር ። ምክንያቱ ደግሞ ጣሊያናዊቷ ቡጢኛ አንጄላ ካሪኒ ያረፈባት ቡጢ ከዚህ ቀደም ከሴቶች ተወዳዳሪዎች ከሚሰነዘረው የተለየ በመሆኑ ለሕይወቴ ሰግቼ ነው ብላለች ። የዓለም ቡጢ ማኅበር ሁለቱ ቡጢኞች እንዳይወዳደሩ በሚል የከለከለውን በፓሪስ ኦሎምፒክ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ሽሮ ተፎካካሪዎች ማድረጉ አወዛግቧል ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ሃይማኖት ጥሩነህ

ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW