የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የሩሲያ ጉብኝትና የዩክሬን ጦርነትን ለማቆም የሚደረገው ጥረት
ዓርብ፣ ኅዳር 19 2018
የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የሩሲያ እና የዩናይትድ ስቴትስ ስብሰባ በቡዳፔስት እንዲካሔድ በድጋሚ ጥሪ አቀረቡ። ፕሬዝደንቱ ጥሪውን ያቀረቡት ዛሬ ከሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሞስኮ በተወያዩበት ወቅት ነው።
ለግብዣው ምሥጋናቸውን ያቀረቡት ቭላድሚር ፑቲን የአሜሪካው አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ የመገናኘት ሐሳብ እንዳቀረቡ ገልጸዋል። ፑቲን በዩክሬን የሚካሔደውን ጦርነትለማቆም እየተደረጉ የሚገኙ ድርድሮች ተገቢውን ውጤቶች ካስገኙ ከዶናልድ ትራምፕ ለመገናኘት እንደሚዘጋጁ ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን የሚገናኙበትን ስብሰባ ሐንጋሪ ታዘጋጃለች ተብሎ ነበር። ይሁንና በቡዳፔስት ይካሔዳል ተብሎ የነበረው የሁለቱ መሪዎች ስብሰባ ጊዜ ማባከን እንዲሆን አልፈልግም ያሉት ትራምፕ እንደማይሳተፉ አስታውቀው ተሰርዟል።
የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ወደ ሩሲያ ከማቅናታቸው በፊት ኦርባን በዩክሬንየሚካሔደውን ጦርነት ለማቆም የቀረቡት“የሰላም ምክረ-ሐሳቦች ወደ ተኩስ አቁም እና ሰላም ይመራሉ ብለን እጅግ ተስፋ እናደርጋለን” ብለው ነበር። ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ርዕዮት የሚከተሉት ኦርባን ወደ ሞስኮ ካቀኑባቸው ጉዳዮች አንዱ ሩሲያ ለሐንጋሪ በምታቀርበው ድፍድፍ ነዳጅ እና ጋዝ ላይ ለመነጋገር ነበር።
ሐንጋሪ የአውሮፓ ኅብረት እና የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) አባል ሀገራት አንዷ ብትሆንም ቪክቶር ኦርባን ለፑቲን የጠበቀ ግንኙነት አላቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሩሲያ ያቀኑት የፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ በሚቀጥለው ሣምንት በሞስኮ የዩክሬን ጦርነትን ለማቆም በተጀመረው አዲስ ጥረት ላይ ከፑቲን ለመነጋገር ወደ ሞስኮ ያቀናሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።
የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን የሩሲያ ጉብኝት እና የዩክሬን ጦርነትን ለማቆም የሚደረገውን ጥረት በተመለከተ ወደ ገበያው ንጉሤን በስልክ አነጋግሬዋለሁ።
ገበያው ንጉሤ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ