1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የሐኪሞች አቤቱታ በአማራ ክልል

ረቡዕ፣ መጋቢት 8 2013

በአማራ ክልል ከ2012 ዓ.ም ጀመሮ በህክምና ሞያ ከተመረቁ ዶክተሮች መካከል 400 የሚሆኑት ሥራ መቀጠር እንዳልቻሉ ተወካዮቻቸው አመለከቱ። በአነስተኛ በጀት ችግራችን መፍታት እየተቻለ ሰሚ አጥተናል ብለዋል። በግል ተቀጥሮ ለመሥራት የሦስት ዓመት ልምድ መጠየቊም ብርቱ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ገልጠዋል።

Äthiopien I Absage des geplanten Treffens mit Demonstranten
ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

ከክልል እስከ ፌዴራል ሰሚ አጠናል ብለዋል

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ከ2012 ዓ.ም ጀመሮ በህክምና ሞያ ከተመረቁ ዶክተሮች መካከል 400 የሚሆኑት ሥራ መቀጠር እንዳልቻሉ ተወካዮቻቸው አመለከቱ። በአነስተኛ በጀት ችግራችን መፍታት እየተቻለ ሰሚ አጥተናል ብለዋል። በግል ተቀጥሮ ለመሥራት የሦስት ዓመት ልምድ መጠየቊም ብርቱ ተግዳሮት እንደሆነባቸው ገልጠዋል። ምሩቅ ሐኪሞቹ ለአንድ ዓመት ያህል በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን ዐሳውቀዋል። ባለፈው ሰኞ ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለማሳየት ቢሞክሩም በፀጥታ ኃይላት ሳይሳካ መቅረቱን ገልጠዋል። ሐኪሞቹ ዛሬ ለሦስተኛ ቀንም በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ተገኝተው እንደነበር የባሕር ዳሩ ወኪላችን ዓለምነው መኮንን የላከልን ዘገባ ይጠቊማል። 

ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከ2012 ዓ ም ጀምሮ ከተመረቁ የህክምና ዶክተሮች መካከል 400 የሚሆኑት ሥራ እንዳልተቀጠሩ የተመራቂ ሥራ ፈላጊዎች ተወካዮች አመልክተዋል፣ ከተወካዮች መካከል ዶ/ር ዓለማየሁ አባተ እንዳሉት ችግሮቻቸው እንዲፈቱላቸው በተደጋጋሚ ያደረጉት ጥረትም ሰሚ አላገኘም። ከዚህ በፊት ምደባ በፌደራል መንግስት ይካሄድ እንደነበር የሚናገሩት ተወካዮቹ ምደባ በየክልል እንዲሆን ከተወሰነ በኋላ የመጣ ችግር እንደሆነም አመልከተዋል።

 ሌላው ተወካይ ዶ/ር መልካሙ ተሰማ በበኩላቸው በግል ተቀጥሮ ለመስራት የግድ የ3 ዓመት የስራ ልምድ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው ታዲያ ሥራ ሳትቀጠር ልምድ የት ታገኛለህ? ሲሉ ይጠይቃሉ:: ወደ ሌሎች ክልሎች ሄዶ ለመስራት ደግሞ አንዳንዶቹ “የክልሌን ቋንቋ አትናገርም” በሚል ሊቀጥሩ ፈቃደኛ አይደሉም በማለት ተናግረዋል፣ በአጠቃላይ ሙያው እንዲጠላ እየተደረገ ነው የሚሉት ዶ/ር መልካሙ፣ የአማራ ክልል ጤና ቢሮም የሚሰጠው ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው ነው መለከቱት። ችግሮቻቸውንም በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለፅ ባለፈው ሰኞ ያደረጉት ሙከራ በፀጥታ ኃይሎች እንዳልተሳካ ዶ/ር ዓለማየሁ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ዶ/ር መልካሙም ቢሆኑ የሰልፉን ክልከላን በፅኑ ኮንነውታል።

የባህር ዳር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር ታደሰ ዳኛቸው ሰልፉ ለምን ተከለከለ በሚል በስልክ ጠይቄያቸው ነበር፣ ጉዳዩን በግልፅ እንደማያውቁትና ምናልባትም ያልተፈቀደ ሰልፍ ሊሆን ይችላል ብለዋል። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር መሰረት ደባልቄም ዝርዝር ጉዳዩን እንደማያውቁ አመልክተዋል።
 ከሰልፉ አስተባባሪ አንዱ ዶ/ር እንግዳየሁ ግርማ ግን ሰልፍ እንደሚያደርጉ ለክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ለአድማ ብተና፣ ለሰላምና ደህንነት፣ ለብልፅግና ፓርቲ፣ ለርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት፣ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ለሲቪል ሰርቪስና ለሌሎችም በርካታ መስሪያ ቤቶች ማሳወቃቸውን አብራርተዋል።

ዶክተሮቹ ዛሬ ለ3ኛ ጊዜ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት እስከከቀኑ 6 ሰዓት ጊዜ ድረስ በአማራ ክልል ጤና ቢሮ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነበሩ። የክልሉን ጤና ቢሮ የስራኃላፊዎች አስተያየት ለማካተት ላለፉት 3 ቀናት በስልክና በአካል ያደረግሁት ጥረት አልተሳካም። ከቢሮው መግቢያ ላይ ያለው ማስታወቂያ እንደሚያሳየውም ኃላፊዎች በስብሰባ ምክንያት ቢሮ ውስጥ የሉም። 
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW