1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐይማኖት መሪዎች ከትግራይ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ጋር ተወያዩ

እሑድ፣ ጥር 5 2011

ከሁሉም ቤተ እምነቶችና አካባቢዎች የተውጣጡ የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በትናንትናው ዕለት ከትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ-መሥተዳድር ጋር መክረዋል። የኢትዮጵያ ነባራዊ ኹኔታ እና የሰላም እጦት ከዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል ጋር በመቐለ ከተማ በተደረገው ውይይት ዋንኛ ርዕሰ-ጉዳይ ነበሩ። 

Ethiopian religious leaders met with the head of Tigray regional government Dr. Debretsion Gebremichael
ምስል DW/M. Haileselassie

የሐይማኖት መሪዎቹ ውይይት በትግራይ

This browser does not support the audio element.

የሃይማኖት መሪዎቹና የሀገር ሽማግሌዎቹ በተለይም በስልጣን ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ሰላም ጉዳይ ተቀራርበው እንዲወያዩ በመቐለ ቆይታቸው ምክትል ርእሰ መስተዳድሩን ጠይቀዋል፡፡ ዶክተር ደብረፅዮን በበኩላቸው የሃይማኖት መሪዎቹና የሀገር ሽማግሌዎቹ የሰላም ጥረት እንደሚያግዙ ገልፀውላቸዋል፡፡ 
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዘዋወር ስለ ሀገራዊ ሰላም ጉዳይ ከመሪዎች ጋር እየተወያዩ የሚገኙት የሃይማኖት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች በአሁኑ ግዜ ኢትዮጵያ  "በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ትገኛለች" ብለዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በስነ- ስርዓቱ "መቋጫ ያላገኘው ሀገራዊ ችግር ለመፍታት ፖለቲከኞች በቂ ትኩረት ሰጥተው ይስሩ" ብለዋል፡፡ 
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ አሚን ጀማል በበኩላቸው ሁሉም በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት አመራር የሰላምን ጉዳይ ያስቀድም በማለት አሳስበዋል፡፡ 
የሌሎች ቤተ እምነቶች ተወካዮችና የሀገር ሽማግሌዎችም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡"በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች እየታዩ ላሉ ችግሮች መነሻው በስልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ አመራር ሀላፊነቱ በሚገባ ባለመወጣቱ ነው" ያሉ ደግሞ የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ናቸው፡፡ ዶክተር ደብረፅዮን የሃይማኖት መሪዎችና ሀገር ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆን  አመራሩ ለሀገር ሰላም ይስራ ብለዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ለሁሉም ችግሮች ተጠያቂ ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አድርጎ ማቅረብ አይገባም ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ፣ የትግራይ ክልል መንግስት አመራሮች ከሌላው የኢትዮጵያ ክልል መሪዎች ጋር ተቀራርበው እንዲወያዩ በሃይማኖት መሪዎቹና ሀገር ሽማግሌዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ ዝግጁ መሆናቸው ገልፀዋል፡፡ "ከዚህ በፊትም ወደ አማራ ክልል የትኛውም ከተማ ሄጄ ለመወያየት ዝግጁ መሆኔ ለሁሉም አመራሮች ነግሬ ነበር" ብለዋል፡፡የሃይማኖት መሪዎቹና ሀገር ሽማግሌዎች በአማራ ክልል በነበራቸው ቆይታ ከክልሉ አመራሮች ተመሳሳይ ዝግጁነት እንዳለ መታዘባቸው ገልፀዋል፡፡
ሚሊዮን ኃይለስላሴ 
እሸቴ በቀለ

ምስል DW/M. Haileselassie
ምስል DW/M. Haileselassie
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW