የሐገር ሽማግሌዎችና የትግራይ ክልል ፖለቲከኞች ዉይይት
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 22 2017
በህወሓት እና የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት መካከል የተፈጠረው መካረር ለመሸምገል ያለሙ የተባሉ የሀገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ትላንት ወደ በመቐለ በመጓዝ ከክልሉ ፖለቲከኞች ጋር ተወያዩ። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በትግራይ በኩል የሚጀመር ጦርነት በፍፁም አይኖርም ሲሉ ለሽማግሌዎቹ ተናግረዋል።
ትላንት መቐለ የመጡት ከኢትዮጵያ 12 ክልሎች እና 2 የከተማዋ አስተዳደሮች የተወከሉ 50 የሃገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶች ትላንትና ዛሬ ከክልሉ የአስዳደር አካላት፣ የተለያዩ ፓርቲ ፖለቲከኞች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና ሌሎች የተወያዩ ሲሆን ዋና አጀንዳቸውም ሰላም ማፅናት ላይ ማድረጋቸው ተገልጿል። በትላንትናው ዕለት ከትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት የተወያዩት እነዚህ ልኡካን ግጭት መልሶ እንዳይቀሰቀስ ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል። ከእነዚህ ልኡካን መካከል አንዱ፥ ያለፈው ጦርነት በሁሉም በኩል ዋጋ አስከፍሏል፥ ይህ መደገም የለበትም ብለዋል።
የሃገር ሽማግሌዎቹ "ዳግም በዊልቸር የሚገፉ ሰዎች እንዲፈጠሩ አንፈልግም፣ ዳግም እግራቸው አጥተው የሚያነክሱ ወጣቶች እንዲኖሩ አንሻም፣ ዳግም አይናቸው አጥተው በሰው የሚመሩ ሰዎች እንዲፈጠሩ አንፈልግም" ብለዋል።
ከሃገር ሽማግሌዎቹ እና የሃይማኖት አባቶቹ ጋር በነበረ ውይይት ሀሳብ የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በበኩላቸው፥ በትግራይ በኩል የሚጀመር ጦርነት በፍፁም አይኖርም ሲሉ ለሽማግሌዎቹ ተናግረዋል።ጀነራል ታደሰ ወረደ "በእኔ [የስልጣን] ወቅት በትግራይ ጦርነት አይኖርም። ለጦርነት የሚደረግ ዝግጅት የለም" ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጀነራል ታደሰ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ለተፈናቃዮች ጥያቄ ምላሽ በሚሰጥ እንዲሁም የትግራይ ዳግመ ግንባታ አጀንዳዎች ዙርያ እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።
ከኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማትየተወከሉ ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት መሪዎች ከሁለት ሳምንት በፊት በመቐለ በመገኘት በተመሳሳይ አጀንዳ ከግዚያዊ አስተዳደሩ እና ህወሓት መሪዎች ጋር መወያየታቸው የሚታወስ ሲሆን ከዛ ቀጥሎም ከትግራይ ወደ አዲስአበባ የተጓዙ የትግራይ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አሕመድ ጋር በፅሕፈት ቤታቸው መወያየታቸው ይታወሳል። እነዚህ ትላንት መቐለ የደረሱ የሰላም ልኡካን፥ ትላንት ከህወሓት መሪዎች ጋር በህወሓት ፅሕፈት ቤት ዛሬ ደግሞ በትግራይ ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በሰላም ጉዳይ ተወያይተዋል።
ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ