የሕንድ ጠቅላይ ሚንስትር የኢትዮጵያ ጉብኝት እንደምታ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 8 2018
የሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ዛሬ ለኢትዮጵያ የሕዝብ እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ንግግር አድረገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ አስቀድሞ ከኢትዮጵያ አቻቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል። የሁለቱ ሀገራት መሪዎች የሀገራቱን የሁለትዮሽ ግንኙነት ወደ "ስልታዊ" አጋርነት ከፍ ለማድረግ መወሰናቸው ተሰምቷል። የዚህን ጉብኝት እንደምታ በተመለከተ ለዶቼ ቬለ አስተያየት የሰጡ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር፤ ሁለቱ ሀገራት በዘርፈ ብዙ መስኮች የመሠረቷቸውን ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነቶች በላቀ ለማሳደግ ዕድል የሚሠጥ ነው ብለዋል።
በሕዝብ ቁጥር ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚዋ ከዓለም ግዙፍ አምስት ምጣኔ ሀብቶች አንዱ ወደመሆን ያደገው ሕንድ ጠቅላይ ሚኒስትሯ ናሬንድራ ሞዲ ኢትዮጵያን ከትናንት ጀምሮ ጎብኝተዋል። ሕንድ በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ የመረጃ ማዕከል መገንባትን ጨምሮ በጉምሩክ የጋራ አስተዳደር ዘርፍ ድጋፍ እንደምታደርግ የገለጡት ናሬንድራ ሞዲ፤ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም ማስከበር ሥራን የተመለከቱ የመግባቢያ ሥምምነቶችን ከትዮጵያው አቻቸው ጋር መፈረማቸው ተነግሯል።
ዛሬ ጠዋት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ለሁለቱ ምክር ቤቶች 36 ደቂቃ የወሰደ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ናረንድራ ሞዱ፤ በሁለቱ ሀገሮች መካከል አለ ያሉትን ጠንካራ የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር፣ ታሪካዊ ግንኙነት፣ በቀጣናዊ ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ የጋራ የዕድገት ዕድሎች ላይም ሰፋ ያለ ንግግር አድርገዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ጥጋቡ ፀጋዬ ይህ ጉብኝት ለኢትዮጵያ ቀላል ግምት የሌለው ዲፕሎማሲያዊ ጥቅም ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።
ጉብኝቱ የሁለቱ ሀገራት "ንግድ ይበልጥ የተሳለጠ እንዲሆን ያደርጋል" - የባለሙያ አስተያየት
ጠቅላይ ሚኒስትር ናረንድራ ሞዲ የሀገሪቱ ከፍተኛ ሽልማት የሆነው "የኢትዮጵያ ታላቅ የክብር ኒሻን" ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተበርክቶላቸዋል። ሞዲ በዛሬው የፓርላማው ንግግራቸው "የሕንድ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ፈሰስ ካደረጉት መካከል ናቸው" ሲሉ በተለያዩ ዘርፎች ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ፈሰስ ማድረጋቸውን እና በዚህም ከ75,000 በላይ ለሚሆኑ የኢትዮጵያ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻላቸውን ጠቅሰዋል።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ጥጋቡ ፀጋዬ የዚህን ጉብኝት እንደምታ ከዚህ ጋር አያይዘው ተንትነዋል። "ኢትዮጵያ በጣም ትላልቅ የሆኑ ማሽኖች ሊሆኑ ይችላሉ፣ የግብርና ግብዓቶችም ሊሆን ይችላል ከሕንድ እንደምታስገባ ይታወቃል። እና ንግዱ ይበልጥ የተሳለጠ እንዲሆን ያደርገዋል"
ኢትዮጵያ እና ሕንድ በትምህርት ዘርፍ የጠበቀ ትስስር አላቸው
የኢትዮጵያ እና የሕንድ መሪዎች ከንግድና ኢንቨስትመንት፣ ከፈጠራና ከቴክኖሎጂ ጉዳዮች ባለፈ በመከላከያ፣ በጤና፣ በምግብ ዋስትና፣ በግብርና እና በታዳሽ ኃይል ዘርፎች የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን በላቀ ለማስፋት ተወያይተዋል። ትምህርት በማህበራዊ ዘርፍ ሁለቱን ሀገራት የበለጠ ያስተሳሰረ መሆኑን ደግሞ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ አቶ ጥጋቡ ፀጋዬ ይጠቅሳሉ።
ኢትዮጵያ ሕንድን ጨምሮ ብራዚል፣ ራሺያ፣ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ ብቻ አባል የነበሩበትን ብሪክስ የተባለውን የባለ ብዙ ወገን የሀገራት ስብስብ ባለፈው ዓመት ተቀላቅላለች። ሕንድ
ከ77 ዓመታት በፊት ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር ሕጋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመረች ሲሆን በ1952 ጀምሮ ደግሞ በአምባሳደርነት ደረጃ የሚወከል ግንኙነት መስርታለች።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሠ