የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአብላጫ ድምፅ ያጸደቀው ረቂቅ አዋጅ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 10 2017
የመርማሪዎችን የወንጀል ተጠያቂነት ያጠበበውና ጥያቄ የተነሳበት ረቂቅ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ ፀደቀ። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወንጀል የተገኘ ንብረት ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ በሦስት ተቃውሞ፣ በአንድ ድምፀ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ አፅድቆታል። በዚህ ዐዋጅ መሠረት መሰል ወንጀሎችን ለመመርመር የተመደበ ሰው በግዴታው ላይ እያለ «ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም» በሚል መደንገጉ ጥያቄ አስነስቷል። ይህ ድንጋጌ በምርመራ ሽፋን የመንግሥት ተቃዋሚዎችን፣ የመብት ተሟጋቾችን፣ ጋዜጠኞችን እና ነጋዴዎችን ለማጥቃት የተረቀቀ እና የዜጎችን መብት የሚጎዳ ነው የሚል ተቃውሞ ገጥሞታል። አዋጁን ያዘጋጁት አካላት ግን የሕጉ መንፈስ ይህ አለመሆኑን ጠቅሰው አላማው ሽብርተኝነትን መከላከል ነው ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለማሻሻል የቀረበውን አዋጅ ቁጥር 780/ 2005ን ዛሬ ማክሰኞ፤ ሰኔ 10 2017 ዓ.ም በአብላጫ ድምፅ አሻሽሎ ሲያፀድቅ በማሻሻያው ከተካተቱትና ጥያቄ ካስነሱት ጉዳዮች አንዱ የዚህ ወንጀል መርማሪ ሆኖ ለሚሰየም ሰው «በግዴታው ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፍቃዱ ውጪ ሆኖ ከድግያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም» የሚለው ዋናው ነበር።
በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳብ ኢሳ ቦሩ የዚህን ምክንያት ጠቅሰዋል።
«ልዩ የምርመራ ዘዴን የሚያከናውን ሰው የሕዝብ ጥቅም ለማስከበር የሚሠራ እንደመሆኑ፤ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት የሚቆይበት ጊዜ ወንጀል ቢፈጽም እንኳን ከወንጀል ክስ ነፃ ስለሚሆንበት አግባብ መደንገግ ሥራውን ውጤታማ ስለሚያደርገው ነው»።
ይህ ምክንያት ግን ጥያቄም ተቃውሞም ቀርቦበታል።በተለይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት «ጥቂት የፀጥታ አካላት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አስከትለው ነበር» የሚለው ተጠቅሶ ጭምር ነው ተቃውሞዎች የቀረቡት።
«ከግድያ መለስ ብዙ ወንጀሎች አሉ። አካል ማጉደል አለ፣ ንብረት ማበላሸት አሉ እና ይህ ሰው እንደፈለገ የሚያደርግ በመሆኑ መብቱን መዘርዘር ነው [የሚሻለው»።
«መንግሥት ውስጥ ሆነው የተለየ ድምፅ ያላቸው እና መንግሥትን የመተቸት አዝማሚያ ያላቸውን ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት አራማጆችን ነው ለመክሰሻ የዋሉት [የቀደሙ ሕጎች]። ይህም የማሻሻያ አዋጅ በተመሳሳይ መንገድ እነዚህን አካላት እና በተጨማር ደግሞ የንግዱን ማኅበረሰብ በተለይ ከመንግሥት ጋር ተጠግተው የማይነግዱ ወይም ለመንግሥት ፋይናንስ የማያደርጉ ግለሰቦችን ለማጥቃት ሊውል ይችላል»።
አዋጁ ሰው [መርማሪዎች] እንደፈለገ እንዲሆን የሚያደርግ፣ ያልተገባ ሥልጣንን በመስጠት የዜጎችን መብት የሚጋፋ ይሆናል ተብሎም ማሻሻያው ከመጽደቁ በፊት ማስተካከያ ተጠይቆበት ነበር። ማሻሻያ የተደረገበት ይህ ሕግ ዓለምአቀፍ አሠራርን መነሻ ያደረገ እና አስፈላጊነቱ የሚያጠያይቅ እንዳልሆና ተገልጾም በምክር ቤቱ ድጋፍ አግኝቷል።
«ሥጋት አድርጎ ሊወስድ የሚችል ወገን ሊኖር ይችላል [ሕጉን]። ግን ለምን ይሰጋል ነው ያ ወገን»።
በምክር ቤቱ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳብ ኢሳ ቦሩ ለተነሱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ይህ ማሻሻያ ሕግ «ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ደህንነት ተቋም የሰጠውን ምክረ ሀሳብ መነሻ በማድረግ» መዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል።
«እኛ ፖለቲከኞችን ሆን ብሎ ለማጥቃት በምንም ተዐምር ያለመ እንዳልሆነ መያዝ አለበት»።
ይህንን ወንጀል ለመከላከል «አስቸኳይ ሁኔታ ባጋጠመ ጊዜ 'መርማሪ' ተብሎ የተጠቀሰው አካል የዐቃቤ ሕግ የበላይ ኃላፊ ሲፈቅድ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የወንጀል ፍሬን ተከታትሎ ለመለየት በባንክ ሒሳቦች እና በሌሎች ተመሳሳይ ሒሳቦች ላይ ክትትል ለማድረግ፣ የኮምፒውተር መረቦችን እና ሰርቨሮችን ለመለየት፣ መገናኛዎችን በክትትል ሥር ለማዋል ወይም ለመጥለፍ ፣ የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ እና ለመያዝ» እንዲችል ሥልጣን ይሰጣል። ይህንንም በ48 ሰዓታት ውስጥ ለፍርድ ቤት ማሳወቅ ይኖርበታል ተብሏል።
በዚህ ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘ ሰው የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከ15 እስከ 25 ዓመት ጽኑ እስራት እና እስከ አንድ ሚሊዮን ብር መቀጮ እንዳለውም ቅጣትን በሚመለከተው የድንጋጌው ክፍል ላይ ተጠቅሷል።
ሰሎሞን ሙጬ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ