የሕዳሴ ግድብ ጥቅምንና አስተዳደርን የቃኘ ዉይይት ተደረገ
ረቡዕ፣ ጳጉሜን 5 2017
ኢትዮጵያ በዐባይ ወንዝ ላይ ያስገነባችዉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሕዳሴ ግድብ ትናንት መመረቁን ምክንያት በማድረግ የባለሙያዎች ሲፖዚም ተደርጓል። የሲፖዚየሙን አዘጋጆች እንዳሉት ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ዉጪ የሚኖሩ ባለሙያዎች፣ የሕዳሴ ግድብ ለታለመለት ዓላማ እንዲዉል «ይረዳል» ያሉትን መርሕና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን አንስተዉ ተነጋግረዋል።የሕዳሴ ግድብ ዓለም አቀፍ ጥምረት ሰብሳቢአቶ ዳንኤል ጌታቸዉ እንዳሉት ግድቡ ዉጤታማና ለሕዝብ አስተማማኝ የኃይል ምንጭ የሚሆንበት ሥልት በዉይይቱ ከተነሱት ጉዳዮች አንዱ ነዉ።የኢትዮጵያ የዉኃ ጉዳዮች መማክርት ሊቀመንበር ፕሮፌሰር አቻምየለሕ ደበላ በበኩላቸዉ ለግድቡ ግንባታ አስተዋፅኦ ያደረጉ ከኢትዮጵያ ዉጪ የሚገኙ ድርጅቶችና ባለሙያዎች ዕዉቅና ተሰጥቷቸዋል።ታሪኩ ኃይሉ ከአትላንታ ዝዝር ዘገባ ልኮልናል።
የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አለማቀፍ ትብብር ጥምረት፣ በመላው ዓለም በታላቁ ኅደሴ ግድብ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችና ባለሙዎችን ያቀፈ ድርጅት ነው።
ድርጅቱ፤ የህዳሴ ግድብን መጠናቀቅና ምረቃውንም በማስመልክቶ ሰሞኑን የባለሙያዎች ሲምፖዚየም አኳሄዷል። የሲምፖዚየሙን ዓላማ አስመልክቶ የጠየቅናቸው የጥምረቱ ሰብሳቢ፣አቶ ዳንኤል ጌታቸው እንደሚከተለው መልሰዋል።
የግድቡ ፖሊሲ እና አስተዳደር
''እንግዲህ የዳሴ ግድብ ካለቀ በኋላ፣ምንድነው የሚቀጥለው ሂደት መምሰል ያለበት፣ስለዚህ የሚቀጥለው ሂደት ይህንን ታላቅ ግድብ ለታለመለት ዓላማ ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ በተለይ የፖሊሲና አስተዳደራዊ ሁኔታዎች ምን መምሰል አለባቸው የሚል ጠቃሚ የሆነ የባለሙዎች ውይይት ነው። ''
በኢትዮጵያና በውጭ ያሉ ከፍተኛ የውሃ ጉዳይ ባለሙያዎች፣በተሳተፉበት በዚሁ ሲምፖዚየም ላይ አስተማማኝ ፣የኤሌክትሪክ ኃይል ለህዝቡ ማቅረብ እና የአየር ትንበያ አቅምን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መምከራቸውን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
ይኸው ጥምረት፣በህዳሴ ግድቡ የግንባታ ሂደት ትልቅ የሆነ ድርሻ እንደነበረውም ሰብሳቢው አመልክተዋል።
ጥምረቱ ያበረከተው አስተዋጽኦ
''ለምሳሌ ካምፔን በማድረግ ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሜሪካ ሃገር ለኮንግረስ ደብዳቤ በመፃፍ ፣የኮንግረስ አባሎችን የአፍሪካን ኮከስ በማነጋገር፣ኢትዮጵያ በመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት በሚደረግበት ጊዜ፣በዲሲ እና አካባቢው፣በኒውዮርክ ያሉ እንደዚህ ዐይነት ድርጅቶች ለምሳሌ ''ዊ አስፓይር እዛ በተደራዳሪነትለነበሩት የኢትዮጵያ ኤምባሲ የዲፕሎማሲ ሰዎች ትልቅ አስተዋጸኦ አድርጓል። ''
በውጭ የሚገኙ የውሃ ባለሙያዎችን በማቀፍ የጥምረቱ አባል የሆነው የኢትዮጵያ የውኃ ጉዳዮች መማክርት ፕሬዘዳንት፣ፕሮፌሰር አቻምየለህ ደበላ በበኩላቸው፣የድርጅታቸውን አበርክቶ እንደሚከተለው ገልፀዋል።
''በዚህ በሰሜን አሜሪካ አካባቢ አውሮፓንም ጨምሮ ቅርንጫፎችን ጭምር አቋቁመን በዓባይ ውሃ አካባቢ በመጀመሪያ አንድ ድርጅት አቋቆምን። በዓባይ ውኃ አካባቢ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶችን አስመልክቶ በተለያዩ ሁኔታዎች ሳይንሳዊ የሆኑ ጥናቶችን በማቅረብ ሲምፖዚየሞችን እና የተለያዩ ጽሁፎችንም እንግዶችንም የውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ ያሉ ኢንጂነሮችን እየጋበዝን፣እኛም እየተማርን ለሌሎችም ማስተማር የምንችልበት ነው። ''
እንደፕሮፌሰር አቻምየለህ ገለጻ፣በሲምፓዚየሙ ላይ፣በተለይ በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም የውሃ ባለሙያዎች ለኅዳሴው ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅ ላበረከቱት አስተዋጸኦ ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
''በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ያደረገውን አስመልክተን፣ መዘክር ድርጅቶችንም ሆነ ግለሰቦችን ለማመስገን፣እንዲሁም ወደፊት ደግሞ በምን መልኩ ቢሰራ ይህ ስኬት፣የኢትዮጵያን የወደፊት ልማት እንዴት ይቀየራል ለሚለው ሃሳባችንንም ለማካፈል፣ከኢትዮጵያ ዉጪ ያሉ ድርጅቶችና ኤክስፐርቶች ያደረጉትን አስተዋጽኦ ለመዘክር በሚል ነው። ''ብለዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
ነጋሽ መሐመድ
ማንተጋፍቶት ስለሺ