1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መኢአድ በዘር ላይ የተመሠረተ ያለዉ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ።

ዓርብ፣ ነሐሴ 29 2012

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በዘር ላይ የተመሠረተ ያለዉ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ። ድርጅቱ ዛሬ በፅሁፍ ባሰራጨዉ  መግለጫ  «ኢትዮጵያ እያስተናገደች ያለው ውስብስብ እና ዘር ተኮር የማሕበረሰብ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄዷል» ብሏል።

Logo Äthiopien Opposition Partei AEUP

የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በዘር ላይ የተመሠረተ ያለዉ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠየቀ። ድርጅቱ ዛሬ በፅሁፍ ባሰራጨዉ  መግለጫ  «ኢትዮጵያ እያስተናገደች ያለው ውስብስብ እና ዘር ተኮር የማሕበረሰብ ቀውስ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄዷል» ብሏል። መኢአድ በመላው ኦሮሚያ የተፈጠረውን ቀውስ ጨምሮ በወልቃይት ጠገዴ፣ በጠለምት ፣ በስቲት ሁመራ ፣ በራያ እና አዘቦ ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ መተከል እና አካባቢው ዘርን መሰረት አድርጎ ለተከሰተው ቀውስ ሕወሓትን ተጠያቂ አድርጓል። ስምንት ነጥቦች ያሉት ይኸው የመኢአድ መግለጫ የፌዴራል መንግስት፣ ሕዋሓት አካሂዳለው ያለውን «ሕገ ወጥ » ምርጫ ሌላ ቀውስ ከማስከተሉ በፊት ጣልቃ ገብቶ ያስቁም ሲል ጠይቋልም። በአዲስ  አበባ ከተማ አስተዳደር «እየተፈጸመ ነዉ» ያለው ህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና የጋራ መኖርያ ቤቶች ቅርምትን አጥብቄ እቃወማለሁ ሲልም ገልጿል። ከደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ታግተው የተወሰዱ እና እስካሁን የት እንደደረሱ ያልታወቀው ተማሪዎች ጉዳይን አስመልክቶ መንግስት ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ መኢአድ በመግለጫው ጠይቋል። በአዲስ አበባ የኦሮምኛ ቋንቋ ትምሕርት ቤቶች ሊሰጥ የታቀደው የገዳ ስረዓት ትምህርት ጉዳይም ጊዜውን ያልጠበቀ እና አስቸኳይ እርምት ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል። የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ህይወታቸው ለጠፋባቸው ሰዎች ቤተሰቦች ፣ ለአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ትኩረት መነፈጉ እንዳሳዘነው ተቃዋሚ ፓርቲ አስታውቋል። በሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ እየደረሰ ባለው ሰቆቃ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ዜጎቹን ወደ ሀገር ቤት እንዲመልስም ጠይቋል።NM

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW