የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 22 2017
የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብተወካዮች ምክር ቤት 6ኛ ዙር 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል ፡፡ ለሦስት ቀናት በወልቂጤ ከተማ የተካሄደው ጉባዔ በበርካታ ጉዳዮቹ ላይ መክሯል ፡፡ የክልሉን ዓመታዊ የሥራ ሪፖርት ያደመጡት የምክር ቤቱ አባላት ትኩረት ያሻቸዋል የሏቸውን ጉዳዮች በአስተያየትም በጥያቄም መልክ አንስተዋል ፡፡ በክልሉ በታችኛው የወረዳ አስተዳደር መዋቅሮች የሚስተዋለው የመልካም አስተዳደር እጦት አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን አባላቱ ተናግረዋል ፡፡
“ ትናንሽ መንግሥታት “
በምክር ቤቱ ጉባዔ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች መካከል በተለይ በታችኛው የአስተዳደር መዋቅሮች የሚታየው የመልካም አስተዳደር እጦት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ አባላቱ “ ትናንሽ መንግሥታት “ ሲሉ የጠሯቸው የወረዳ አስተዳደር መዋቅሮች ለመልካም አስተዳደር እጦት ፣ ለህዝብ ብሶት እና ቅሬታ ምክንያት መሆናቸው የክልሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ ተናግረዋል ፡፡
“ እዚህ ክልል ላይ ሲሪየስ / የምር / የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር እየታየ ነው “ በማለት አስተያየታቸውን የጀመሩት ሁለት የምክር ቤት አባላት “ ከላይ የክልል ካቢኔ ፣ የዞን አስተዳደር ይወስናል ፡፡ ነገር ግን ታች መሬቱ አካባቢ ሲደርስ ተፈጻሚ አይሆንም ፡፡ ምክንያቱም እዛ “ ትናንሽ መንግሥታት “ ተፈጥረዋል ፡፡ ጉዳዮችን ለመፈጸም ፍቃደኛ አይደሉም ፡፡ እነኝህ አካላት ታች ያለውን ማህበረሰብ እያገለገሉ አይደለም ፡፡ ይህ በጣም አደገኛ ነው ፡፡ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል “ ብለዋል ፡፡
ተጠያቂነት እንዴት ይሥፈን ?
የምክር ቤት አባላቱ ያነሷቸውየመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትክክለኛ መሆናቸውን የጠቀሱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ተጠያቂነትን ለማስፈን በጋራ መሥራት እንደሚገባ ጠቁመዋል ፡፡በአገልግሎት አሰጣጥ ህዝብን የሚያሰቃዩ አመራሮች መኖራቸውን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ “ አንዳንዱ ወደ አመራርነት የሚቀላቀለው ትንሽ ጊዜ ሠርቶ የምትገኝ ነገር ካለችም ጭልፍ አርጎ ለመሄድ ነው ፡፡ በዚህ ውስጥ ጎሰኝነቱ አለ ፡፡ የአካባቢ ሰው የሚባል ነገር አለ ፡፡ ችግሩ ውስብስብ ነው ፡፡ ነገር ግን የደረስንባቸው ላይ እርምጃ እየወሰድን እንገኛለን ፡፡ እነዚህን እያጠራን እያስተካከልን እንሄዳለን ፡፡ ለዚህ ደግሞ የሁሉንም ትብብር ሥለሚፈልግ በጋራ ልንሥራ ይገባል “ ብለዋል ፡፡
ምክር ቤቱ የተለያዩ ደንብና አዋጆችንእንዲሁም የ37 እጩ ዳኞች ሹመትን አጽድቋል። በተጨማሪም የክልሉ የ2018 በጀት ዓመት የሚውል የ43 ቢሊየን 252ሚሊየን ብረ በጀት አጽድቋል፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ታምራት ዲንሳ