1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመማር ተስፋን ያጨለመው ትውልድ ተሻጋሪ ቀውስ፤ እንዴት ይታከም?

ማክሰኞ፣ መስከረም 28 2017

የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቅርቡ እንዳስታወቀው በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት አቅዶ የነበረ የተመዘገቡት ግን ከ2 ሚሊዮን አይበልጡም። በጦርነቱ ሳቢያ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸው ከሚያሳድረው የሥነ-ልቡና ጫና ባሻገር ትውልድ ተሻጋሪ ቀውስ እንዳያስከትል አስግቷል።

የአማራ ክልል  ትምህርት ቢሮ
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮምስል Alemnew Mekonnen/DW

ተማሪ ምስጋናው ስንታየው በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ ወረዳ መሰቦ ቀበሌ ነዋሪ ነው። በአዴት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከ 9ኛ ክፍል ትህምህርቱን መከታተል የቻለ የ18 ዓመት ታዳጊ ወጣት ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት በክልሉ በመንግስት የጸጥታ ኃይልና በፋኖ ታጣቂ መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት አዘል ግጭት ሳቢያ ትምህርቱን መቀጠል ባለመቻሉ ቤተሰቡን በስራ እያገዘ ይገኛል።
ከብት ከሚያግድበት ቀዬ በአባቱ አርሶ አደር ስንታየሁ ሁነኛው ጥሪ ዶይቼ ቬለ ለቃለ-መጠይቅ ያገኘው ተማሪ ምስጋናው፤ ትምህርቱን ከ9ኛ ወደ 10ኛ ክፍል በ2015 ዓ.ም. ያለፈ ቢሆንም 2016 ዓ.ም. ላይ «አገር ሰላም ባለመሆኑ» የ10ኛ ክፍል ትምህርቴን መቀጠል አልቻልኩም ሲል ነግሮናል።

ተማሪው ተምሮ ዶክተር የመሆን  ትህልም ሰንቋል። ዶክተር መሆን የምፈልገው «ህዝብ ለማከም ነው» የሚለው ተማሪ ምስጋናው «ከትምህርት ሰላም ይቀድማል፤ ሰላም ከሌለ ትምህርት መቀጠል አይቻልም።» በሚል ሰላም በአካባቢው ባለመኖሩ የመማር ህልሙን እንዳጨለመበት ይናገራል።

ተማሪ ስንታየውን ጨምሮ 5 ልጆች ያላቸው አርሶ አደር ስንታየው ልጃቸው ወደ 5 ኪሎ ሜትር ተጉዞ አዴት እየተማረ እንደነበር በማስታወስ በጦርነቱ ምክኒያት ትምህርት እንደተቋረጠ ይናገራሉ። «እያለፈ ያለው የንፁሐን ሕይወት ነው፤ ይህም የተማሪ ልጆቻችንን ስነ-ልቦና እንዲሟሽሽ አድርጓል» ሲሉ የቀጠሉት አርሶ አደሩ ሌሎች ሶስት ልጆቻቸውም ትምህርት ጨርሰው ስራ አጥተው እቤት መቀመጣቸውን ይናገራሉ።

በጦርነቱ ሳቢያ በአማራ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸውምስል Arega Mengistu/Kidamit elementary school

አቶ በላይ (ስማቸው የተቀየረ) በክልሉ ምህራብ ጎጃም ዞን ደጋ ዳሞት ወረዳ ፈረስ ቤት ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ ባለትዳርና የ4 ልጆች አባት ናቸው። የ17 ዓመት ሴት ልጃቸው እዚያው ከእርሳቸው ቀዬ እንድትማር ፍላጎት ያላቸው ቢሆንም መሻታቸው ግን እውን ሊሆን አልቻለም። ልጃቸው በ2015 ዓ.ም. ከ9ኛ ክፍል ወደ 10ኛ ክፍል ብትዛወርም በአካባቢው ባለው ጦርነት አዘል ግጭት ምክኒያት በ2016 ዓ.ም. ትምህርቷን መከታተል በነበረባት ፈረስ ቤት 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መከታተል ሳትችል ቀርታለች። በዚህም ምክኒያት እቤት ውስጥ ካለትምህርት ለ1 ዓመት የተቀመጠችው የአቶ በላይ ልጅ ለ«ጭንቀት» ተዳርጋ እንደነበር አባትዬው ሲናገሩም፤ «ልጄ ከፍተኛ የማወቅና የመማር ፍላጎት ስላላት በየወቅቱ ትምህርት አይከፈትም? እያለች ትጠይቀኛለች። እኔ ይከፈት ይሆናል ምኑ ታውቆ ብለሽ ነው እያልኩ አረጋጋት ነበርና ሁል ግዜ እራሴን አመመኝ ትላላች» በማለት ልጃቸው ለትምህርት ባላት ጉጉት «ሳይከፈት ቢቀር ሳልማር ልቀር ነው? በሚል ጭንቀት» ውስጥ እንደነበረች ይናገራሉ።

የልጃጀው የሥነልቡና ደህንነት ያሳስባቸው የነበረው አቶ በላይ በያዝነው 2017 ዓ.ም. ላይ ልጃቸውን ባለትዳር ወደሆነች ታላቅ እህቷ ወደምትገኝባት ሌላ ቀዬ ሰድደዋታል። «አሁንማ በጣም ደስ ብሎኛል ። በቃ ትምህርቴን ልቀጥል ነው። እዚህ ደግሞ አሁን ሰላም ነው። በሰላም እየተማርኩ ነው ስትል።» ወደፊት ዶክተር በመሆን «ሁሉን ሰው በማከም ማትረፍ» የምትሻዋ የ17 ዓመቷ ሴት ታዳጊ ተማሪ ደስታዋን እና ተስፋዋን ሳቅ በቀላቀለ ድምፀት ለዶይቼ ቬለ አጋርታለች።

የጦርነቱ ጉዳት ጥልቀት

የፌደራል መንግስት መከላከያ ሰራዊትከአማራ ክልላዊ መንግስት የፀጥታ ኃይል ጋር በጥምረት በመሆን በክልሉ ከሚንቀሳቀሰው ፋኖ ከተሰኘ  ታጣቂ ቡድን ጋር ጦርነት አዘል ግጭት ውስጥ ከገቡ አንድ ዓመት ተሻግሯል። በዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ላይ የሞት፣ የመቁሰል፣ የማህበራዊ እና የስነ ልቦና ጉዳቶች መድረሳቸውን ከኢትዮጵያ ሰባዊ መብት ኮሚሽን እና ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚወጡ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። በተቃራኒ ጎራ ተሰልፈው ደም አፋሳሽ ጦርነት ውስጥ ባሉት የአንድ አገር ሰዎች ምክኒያት የተፈጠረው ቀውስ የቀጣይ ትውልድ እጣ ፈንታን ጭምር የሚፈታተን ሆኖ ታይቷል።

በአማራ ክልል አንዳንድ ትምህርት ቤቶች በጦርነቱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።ምስል Arega Mengistu/Kidamit elementary school

የተባበሩት መንግስታት የሰባዊ ጉዳዬች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (UNOCHA) በሚያዚያ ወር 2016 ዓ.ም. ባወጣው ዘገባ በትምህርት ዘመኑ ከ4.1 ሚሊየን በላይ ህፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን እንዲሁም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በነበረውና ባለው ጦርነት ሳቢያ ከተዘጉ አጠቃላይ 4,178 ትምህርት ቤቶች 41 በመቶ የሚሆኑት በአማራ ክልል የሚገኙ መሆናቸውን አመላክቷል።

በክልሉ በሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. ላይ በተሰጠው የ8ኛ ክፍል ክልል አቀፍ ፈተናን መፈተን ከነበረባቸው ውስጥ ከ185 ሺህ ተማሪዎች በላይ ፈተናውን መፈተን ያለመቻላቸውን የክልሉ ትምህርት ቢሮ በወቅቱ ያሳወቀ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን የ9ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎችም እንዲሁ ትምህርታቸውን ለማቋራጥ ተገደዋል። ዶቼ ቬለ  የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ በቅርቡ ባነጋገረበት ወቅትም ቢሮው በ2017 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን 7 ሚሊዮን ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት ለማስገባት አቅዶ የነበረ ቢሆንም የተመዘገቡት ግን ከ2 ሚሊዮን እንደማይበልጡ አስታውቋል። ይህም በተማሪዎቹ ሥነ-ልቡና ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ከመገኘቱ ባለፈ ትውልድ ተሻጋሪ ቀውስ እንዳያስከትል አስግቷል።

የትምህርት መቋረጥ እና የሥነ-ልቦና ቀውስ 

ትምህርት አንድን አገር ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገቶችን በማቀላጠፍ ሁሉ አቀፍ ልማትን ለማስፈን ያለው ቁልፍ ሚና የላቀ መሆኑ ብዙኅንን የሚያግባባ እውነታ ነው። በዚህም ምክኒያት በተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መካከል አንቀፅ 26 ሁሉም ሰው ትምህርት የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል።ትምህርት ከሰብዓዊ መብት ባለፈም ለሌሎች የሰብዓዊ መብቶች መከበርም የጎላ ድርሻ እናዳለው አመላክቷል። ሆኖም በአማራ ክልል የመማር ሰብዓዊ መብታቸውን የተገፈፉት በሚሊየን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ጭንቀትን ጨምሮ ለተለያዩ የአህምሮ ጤና እክል መዳረጋቸውን ዶቼ ቬለ ከአነጋገራቸው ተማሪዎችና ወላጆች ለመረዳት ችሏል።
ነዋሪታቸውን በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ያደረጉት የስነ-ልቦና ባለሞያ የሆኑት አቶ የሻምባው ወርቄ፤ «የአምሮ ጤና እክል በማንኛውም ወቅት ሊከሰት ይችላል። ሆኖም ግን የአህምሮ መታወክ የማህበራዊያለመረጋጋት በሚኖርበት ወቅት እና በጦርነት ወቅት በእጥፍ ሊጨምር ይችላል።» በማለት የሰው ልጅ አካባቢን ተላምዶ እንደመኖሩ አካባቢ ሲታወክና የየተህለት ህይወት ሲጨልም አህምሮም አብሮ ሊታወክ  እንደሚችል አመላክተዋል።

ባለሙያው እንዳሉት ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሄደው ከትምህርት ማግኘት ያለባቸውን እውቀት ማግኘት ያለመቻላቸው የአእምሮ እድገትን ይገታልምስል Alemnew Mekonnen/DW

ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሄደው ከትምህርት ማግኘት ያለባቸውን እውቀት ማግኘት ያለመቻላቸው የአእምሮ እድገትን እንደሚገታና «አእምሮአችንን ስንገታው ይታወካል» የሚሉት ባለሞያው ከሚከሰቱት የአእምሮ መታወኮች መካከል «ጭንቀት» አንዱ መሆኑን ይጠቁማሉ። «በአፍላ እድሜ ክልል ውስጥ ያሉት ትምህርት ሲቋረችጥባቸው ነገን አጨልመው ያዩታል። ተስፋ ይቆርጣሉ። ከፍተኛ የአእምሮ ቀውስ ውስጥ ይገባሉ።» ሲሉ ተማሪዎች የሚገጥማቸውን የስነ-ልቦና ጉዳት የሚያብራሩት አቶ የሻምባው ችግሩን ከእነሱ አቅም በላይ ስለሚሆን «ድብርት ውስጥ ሊገቡ» እንደሚችሉም ይናገራሉ።
የሥነ-ልቦና ባለሞያው ልጆች በአካባቢያቸው አስደንጋጭ ነገሮችን እያዩና እየሰሙ ማደጋቸው አእምሮን የሚጎዳ ስቃይ (trauma) ሊፈጥር ከመቻሉም ባለፈ «ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር (transgenerational trauma) የሚባል የአህምሮ መታወክ ውስጥ ሊከት ስለመቻሉ» አስጠንቅቀዋል። እንደ መፍትሄም የተማሪዎች ወላጆችና ማህበረሰቡ ከእነሱ አቅም በላይ በሆነ ችግር የትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ያልቻሉት ልጆቻቸው ሁሌም በጎ እይታዎችን እንዲያዩ እና እንዲያስቡ አእምሮአቸውን በሌላ ስራ መጥመድ እንዲሚያስፈልግ የሥነ-ልቦና ባለሞያው ምክራቸውን ይለግሳሉ። ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥምም ጠንክሮ በፅናት ማለፍና «ችግሩን አጉልቶ ከማየት ችግርን የምንፈታበትን መነፅር መቀየርና የስሜት ልዕቀትን ማበልፀግ» እንደሚገባም አመላክተዋል። ዶቼ ቬለ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ትምህርት ሚኒስቴር የችግሩን ጥልቀት እንዴት ትገመግሙታላችው? የሚል ጥያቄ ይዞ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊን ቢያነጋግርም «ጉዳዩ የሚመለከተው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ነው» የሚል ምላሽ ማግኘቱን ለመግለጥ ይወዳል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ ዘገባው እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ አለመሳካቱን ለመግለጥ እንወዳለን።

 

ዳግም አዳነ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW