1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሬት መንሸራረት መንስኤና መፍትሄው

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30 2016

የመሬት መንሸራተት አደጋ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ በተደጋጋሚ ይከሰታል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ተመራማሪዎች በቅርቡ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ የደረሰውና ከ250 በላይ ሕይወት የቀጠፈው የመሬት መንሸራተት የብዙዎችን ትኩረት ሳበ እንጂ ክስተቱ መደጋገሙን ይናገራሉ።

ሲዳማ
በሲዳማ የደረሰው የመሬት መንሸራተት ምስል Bureau of Government Communications Affairs of Sidama Region

የመሬት መንሸራረት መንስኤና መፍትሄው

This browser does not support the audio element.

ተመራማሪዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ 49.1 በመቶ የሚሆነው የመሬት ገጽታ ለመሬት መንሸራተት የተጋለጠ ነው። የመሬት መንሸራተትም ሆነ የድንጋይ ናዳ በብዛት የሚያጋጥመው ደግሞ በተለይ በማዕከላዊ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ነው። በተመሳሳይ በሰሜንና በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያም ይኸ ክስተት ያጋጥማል። ጤና ይስጥልን የዝግጅታችን ተከታታዮች እንደምን ሰነበታችሁ? ከሳምንት በፊት በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ የደረሰው የመሬት መንሸራተት የ257 ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ሺህዎችንም ከአካባቢው አፈናቅሏል። የመሬት መናዱ በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ አሁንም ቀጥሏል። ለምን ይሆን ይህ የተፈጥሮ አደጋ በተጠቀሰው አካባቢ የሚደጋገመው? የዘርፉን ተመራማሪዎች ጠይቀናል።

የመሬት መንሸራተት መንስኤ

የመሬት መንቀጥቀጥ፤ ለመሬት መንሸራተትና ናዳ መከሰት ቀዳሚው ምክንያት ሲሆን የመሬት አጠቃቀምም ለመሬት መንሸራተት ወሳኝ ሚና እንዳለው ይነገራል። የመሬት መንሸራተት የሚከሰተው የዕጽዋት ልባስ በሌለበት ማለትም በደን ባልተሸፈነ አካባቢ እንደሆነም ነው ምሁራኑ የጠቆሙት።

ዶክተር ተሻለ ወልደአማኑኤል የወንዶ ገነት የግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲን እና የደን ዘርፍ ተመራማሪ ናቸው። ለመሬት መንሸራተት መንስኤዎቹ ምን ምን ናቸው ያልናቸው ዶክተር ተሻለ መሬትን ሸፍነው የነበሩ ዛፎችም ሆኑ ሳሮች ሲራቆቱ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል ነው የሚሉት።  

እሳቸው እንደሚሉት ዝናብ በሚዘንብበት ጊዜ ዛፍና ሣር ባለበት ቦታ አፈሩ የተረጋጋ ይሆናል። ምክንያቱ ደግሞ የየተክሎቹ ስር ዘነበው ዝናብ አፈሩ ላይ እንደ እስፖንጅ ሆኖ ውኃውን በመያዝ ወደ መሬት ስርም ቀስ እያለ እንዲሰርግ ያገለግለዋል እና ነው። ይህ በሌለበት ግን የሚወርደው ዝናብ አፈሩ ከሚሸከመው አቅም በላይ ስለሚሆን የመሸርሸር ዕድሉ በጣም ከፍተኛ ይሆናል።

በቅርቡ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በምትገኘው የኬንቾ ሻቻ ቀበሌ ከ250 በላይ ነዋሪዎችን ሕይወት ለቀጠፈው የመሬት መንሸራተት፤ የተጠቀሱት መንስኤ ሊሆኑ ቢችሉም ሌሎች ምክንያቶች ለመኖራቸው የስነምድር ምርምር ባለሙያዎች ጥናት ሊያደርጉበት ሊደረስበት እንደሚገባም ነው ያመለከቱት።

በገዜ ጎፋ የተከሰተው የመሬት መንሸራተት ምስል Isayas Churga/AP/picture alliance

የአፈር ይዘትና የመሬት አቀማመጥ

የመሬት መንሸራተትም ሆነ ናዳ በተመሳሳይ በሰሜንና በሰሜን ምዕራብ እንደሚደጋገም ነው የሚነገረው። የዘርፉ ምሁራኑ እንደሚሉት ለአፈር መንሸራተት የአካባቢው የአፈር ይዘት/ ባህሪ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። የኢትዮጵያ 49.1 በመቶ የሚሆነው የመሬት ገጽታ ለመሬት መንሸራተት የተጋለጠ መሆኑ ይነገራል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ የጠፈር ሳይንስና ስነክዋክብት ተቋም ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ጌትነት መዋ የዚህ እውነትነት አያጠያይቅም ነው የሚሉት።

ሰሞኑን በደቡብ ኢትዮጵያ ጎፋ ዞን የደረሰው የመሬት መንሸራተት ዋነኛ መንስኤ ከሆኑት አንዱ የመሬቱ አቀማመጥ ነው መሆኑን ዶክተር ጌትነት ያስረዳሉ።

እሳቸው እንደሚሉትም በቀናት ዝናብ የረሰረሰው ከ45 ዲግሪ በላይ የሆነው ተዳፋት መሬት መጀመሪያ ከላይ የነበረው አፈሩ በመጠኑ ከተደረመሰ በኋላ፤ በቀጣይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰው ከባድ ናዳ ወረደ።

የመሬት መንሸራተቱ አደጋክረምቱን ተከትሎ በዝናብ ጊዜ የሚከሰት መሆኑን ያመለከቱት ዶክተር ጌትነት፤ እንዲህ ባሉ አካባቢዎች ታዲያ ዛፎች መኖራቸው ችግሩን ለመቀነስ እንደሚረዱ ነው እሳቸውም የተናገሩት። የመልክአ ምድር ባለሙያዎችን በየአካባቢው ማሰማራት ለማኅበረሰቡ ግንዛቤ መስጠትም ወሳኝ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

መፍትሄዎች

የመሬት አጠቃቀምን በተመለከተም ብዙ ሥራ መሠራት አለበት የሚሉት ባለሙያዎቹ ሰዎች የት መስፈር እንዳለባቸው እና እንደሌለባቸው መለየት የግድ መሆኑን፤ የመኖሪያ አካባቢ፣ የእርሻ እንዲሁም የተከለከለ ጥብቅ የደን አካባቢ ተለይቶ ሊመላከት እንደሚገባ አሳስበዋል። መሬትን የምንጠቀምበት መንገድ ሲበላሽ ቁጣዋ ይቀሰቀሳል ያሉት ዶክተር ጌትነት ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በስተደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ አካባቢ የመሬት መንሸራተት እየተደጋገመ ነው። የአፈሩ ለምነት ከመሬቱ መራቆት ጋር ተዳምሮ ለተፈጥሮ አደጋው አንዱ መንስኤ መሆኑን ባለሙያዎቹ አመልክተዋል። የተጋለጠውን አካባቢ በዛፎች እየሸፈኑ ሰዎች ሊሰፍሩባቸው የሚገባውን አካባቢ መለየት አማራጭ እንደሌለውም አሳስበዋል። ለሰጡን ማብራሪያ ተመራማሪዎቹን እናመሰግናለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ልደት አበበ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW