1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሬት መንቀጥቀጥ በሰሜን ኢትዮጵያ

ሰኞ፣ ግንቦት 28 2015

መቐለን ጨምሮ በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች እንዲሁም አዋሳኝ የአፋርና የኤርትራ ቦታዎች 4.7 ሬክተር ስኬል የተለካ ርእደ መሬት ተከሰተ። ተመሳሳይ መጠን ያለው ርእደ መሬት በአካባቢው ሲያጋጥም በአምስት ወራት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ግዜ ነው።

Äthiopien Erdbeben in Mekele in Tigray
መቐለ ከተማምስል Million Hailessilase/DW

ርእደ መሬት በአካባቢው ሲያጋጥም በአምስት ወራት ግዜ ዉስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው

This browser does not support the audio element.

መቐለን ጨምሮ በበርካታ የትግራይ አካባቢዎች እንዲሁም አዋሳኝ የአፋር እና የኤርትራ ቦታዎች 4.7 ሬክተር ስኬል የተለካ ርእደ መሬት ተከስቷል። ተመሳሳይ መጠን ያለው ርእደ መሬት በአካባቢው ሲያጋጥም በአምስት ወራት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ግዜ ነው። ምሁራን ተፈጥሮአዊው ክስተት የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ ሊያስከትለው የሚችል አደጋ መቀነስ እንደሚቻል ያነሳሉ።

በዋነኝነት በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም አዋሳኝ የዓፋርና ኤርትራ ቦታዎች ትላንት የተከሰተው ርእደ መሬት 4.7 ሬክተር ስኬል እንደሚለካ የየተለያዩ ዓለምአቀፍ ተቋማት መረጃዎች ያመለክታሉ። የአሜሪካው ስነምድር ጥናት ተቋም USGS ሪፖርት እንደሚያሳየው የርእደ መሬቱ መነሻ ከዓዲግራት ወደ ምስራቅ አቅጣጫ በትግራይ፣ ዓፋር እና ኤርትራ አዋሳኝ አካባቢ መሆኑ የሚገልፅ ሲሆን የርእደ መሬቱ የመሬት ውስጥ ጥልቅ ርቀት ደግሞ 10 ነጥብ 0 ኪሎሜትር ስለመሆኑ ተነግሯል። በትግራይ፣ ዓፋር እና ኤርትራ አዋሳኝ አካባቢዎች ተመሳሳይ መጠን ያለው ርዕደ መሬት ሲከሰት በአምስት ወራት ውስጥ የትላንቱ ለሁለተኛ ግዜ ነው። ባለፈው ታህሳስ ወር መጨረሻም እንዲሁ ተመሳሳይ ንዝረት ያለው ርእደ መሬት በአካባቢው ተከስቶ ነበር።

መቐለ ከተማምስል Million Hailessilase/DW

ቀጠናው ለርእደ መሬት ተጋላጭ መሆኑ የሚያነሱ የዘርፉ ምሁራን፣ ተፈጥሮአዊ ክስተቱ ሊያደርሰው የሚችል አደጋ የሚቀንሱ እርምጃዎች አስቀድሞ መወሰድ እንዳለበትም ይመክራሉ። በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምህንድስና መምህሩ እና በርዕደ መሬት ዙርያ ተዛማጅ ጥናቶች የሚሰሩት አቶ ብርሃነ አረጋዊ በተደጋጋሚ እየታዩ ያሉ በመጠን ያነሱ የርዕደ መሬት ክስተቶች መነሻ በማድረግ ጥናቶች ሊሰሩ፣ የጥንቃቄ እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚገባ ያወሳሉ።

ሌላው ከፍተኛ ንዝረት ካስተናገደችው ዓዲግራት ከተማ ያነጋገርናቸው በዓዲግራት ዩኒቨርስቲ የጂኦሎጂ ምሁሩ ግርማይ ካሳ፥ በተለይም ከቅርብ ግዜ ወዲህ በመጠን አነስተኛ የሆኑም ቢሆን ተደጋጋሚ የርዕደ መሬት ክስተቶች መታየታቸው ያልተለመደ ያሉት ሲሆን የትላንቱ አጋጣሚ ካለፉት ከፍ ያለ እንደነበር መታዘባቸውም ገልፀውልናል።  

እንደ የምህንድስና እና ርዕደ መሬት ጉዳዮች አጥኚው አቶ ብርሃነ አረጋዊ ገለፃ፥ ርዕደ መሬት ጨምሮ የተለያዩ አደጋዎች ለመከላከል በህንፃዎች ጥራት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራ ይገባል ይላሉ።

ትላንት በተለያዩ የትግራይ እንዲሁም አዋሳኝ የዓፋር እና ኤርትራ አካባቢዎች ተስተዋለ የተባለው ርዕደ መሬት አስከተለው ተብሎ ሪፖርት የተደረገ ጉዳት እስካሁን የለም።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW