1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመሬት መንቀጥቀጥ እና የኢትዮ - ጅቡቲ መስመር ኹኔታ

ሐሙስ፣ ታኅሣሥ 24 2017

አቶ ሰለሞን ዘውዴ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር የሥራ አስፈፃሚ አባል ናቸው። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በዚህ ኹነኛ መስመር ላይ ባለው የከበድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ያስከትለው ተፅዕኖ ስለመኖር አለመኖሩ ጠይቀናቸው «የመሬት መንቀጥቀጥ በአሽከርካሪዎች ላይ የፈጠረው ነገር የደረሰኝ ሪፓርት የለም» ሲሉ መልሰዋል።

የመሬት መንቀጥቀጡ አዋሽ-ፈታሌ ዉስጥ በተለያዩ ቀበሌዎች ካደረሰዉ ጉዳት በተጨማሪ የኢትዮ-ጅቢቲ የመኪና መንገድ ላይ ጉዳት ያደርሳል የሚል ሥጋት አሳድሯል።
ኢትዮጵያ ዉስጥ በአፋር ክልል አዋሽ-ፈንታሌ አካባቢ በተደጋጋሚ የሚደርሰዉ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ እስካሁን በሰዉ ሕይወት ላይ አደጋ ባያደርስም ንብረቶችና ቤቶችን እያጠፋ ነዉ።ምስል private

የመሬት መንቀጥቀጥ እና የኢትዮ - ጅቡቲ መስመር ኹኔታ

This browser does not support the audio element.

በኢትዮጵያ አፋር ክልል ውስጥ ተደጋግሞ እየተከሰተ ያለው የመሬት መንቀጥቀጥ ብርቱ ሥጋት ደቅኗል።በዚህ አካባቢ እየደረሰ ያለው ይህ አደጋ አስከታይ ተፈጥሯዊ ክስተት አዲስ አበባ ውስጥ ጭምር ቀላል የማይባል ንዝረትን እያስከተለ ይገኛል።ኤርትራ ራሷን የቻለች ሀገር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ ጉሮሮ ሆናለች ከምትባለው ጅቡቲ በየዕለቱ ጭነት በሰፊው የሚያጓጉዙት የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት እያደረጋቸው ይሆን? በሥራቸው ላይስ ያስከተለው ተፅዕኖ ይኖር ይሆን ? የተወሰኑትን ጠይቀናል።//

የመሬት መንቀጥቀጡ በኢትዮ - ጅቡቲ መስመር ላይ ምን አስከተለ?

ሰሞኑን የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥ በሚከሰትበት የኢትዮጵያ የገቢ ምርት ዋና በር በሆነው የኢትዮ - ጅቡት መስመር ማለፊያ አፋር ክልል ላይ ደረቅ እና ፈሳሽ ጭነቶችን የሚያጓጉዙ ከ22 እስከ 30 ሺህ የሚገመቱ ተሽከርካሪዎች ይመላለሱበታል።


አቶ ሰለሞን ዘውዴ የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማሕበር የሥራ አስፈፃሚ አባል ናቸው። ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በዚህ ኹነኛ መስመር ላይ ባለው የከበድ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ያስከትለው ተፅዕኖ ስለመኖር አለመኖሩ ጠይቀናቸው "የመሬት መንቀጥቀጥ በአሽከርካሪዎች ላይ የፈጠረው ነገር የደረሰኝ ሪፓርት የለም" ሲሉ መልሰዋል።

ስለ መሬት መንቀጥቀጡ የአሽከርካሪዎች አስተያየት 

ይህ የተፈጥሮ ክስተት ትናንትም ከዚያም ቀደም ብሎ ባሉት ቀናትም ተደጋግሞ ተከስቷል። በዚሁ ቀጣና በተዘረጋው አውራ ጎዳና ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ከባድ መኪና ያሽከረከሩት አቶ ወንድወሰን የተባሉ ባለሙያ እንደዚህ ዓመቱ ያለ ኹኔታ ግን ገጥሟቸው አያውቅም።

ከጁቡቲ ወደ መሐል ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የሚጓጓዙ የከባድ የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች የመሬት መንቀጥቀጡ እንደሚያሰጋቸዉ አስታዉቀዋልምስል Solomon Muchie/DW

"እኔ በሕይወት ታሪኬ እንደዚህ አይነት ነገር አይቼ አላውቅም"።

ሌላኛው አቶ ዳመነ የተባሉ የሀገር አቋራጭ ከባድ መኪና አሽከርካሪ - ሾፌር፤ በሚጓዙበት መንገድ ላይ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት እስካሁን ችግር ባይገጥማቸውም ሥጋቱና የፈጠረው ፍራቻ ግን በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

"ሌሊት በቆምንበት ነው ይሄን ነገር የምንሰማው። አሁን ለእኛ ሥራ መስተጓጎል ይፈጥራል ብለን አናስብም። መንገድ ላይ አሁን የተፈጠረ ነገር የለም። መሰንጠቁ ቢያንስ እኛ ከምንሄድበት መንገድ 45፣ 25፣ 35 ኪሎ ሜትር አካባቢ ወደ ውስጥ የገባ ስለሆነ እኛ ዕይታ ውስጥ የለም" ብለዋል።

አቶ ወንድወሰንም ይህንኑ አረጋግጠው ንዝረቱ ግን አሰበ ተፈሪ ድረስ ጫን ያለና "ከባድ" እንደነበር በዚያው መስመር የሚገኝ ጓደኛቸው በስልክ እንደገለፀላቸው ተናግረዋል።

የጥንቃቄ መልዕክቶችን ቶሎ ቶሎ እንለዋወጣለን - የአሽከርካሪዎች ማህበር


 በአሽከርካሪዎች ላይ የፀጥታ ሥጋት ያልተቀረፈበት ይህ ቁልፍ የመጓጓዣ መስመር ከአዳማ እስከ መተሃራ ባለው የወለንጭቲ ጎዳና ላይ ከታህሳስ 17 እስከ 19 የነበረውን መጨናነቅ ተከትሎ አራት ተሽከርካሪዎች በተለዋጭ መንገድ እንሂድ በሚል ከዋና መንገድ ውጪ ሲጓዙ በታጣቂዎች ታፍነው ተወስደው የነበረ ሲሆን "ጥምር" ባሉት ኃይል በፍጥነት እንዲለቀቁ መደረጋቸውን አቶ ሰለምን ዘውዴ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።


መሬት መንቀጥቀጥ ሲኖር በዋናነት ሊጎዱ የሚችሉት ድልድዮች ናቸው የሚሉት አቶ ሰለሞን ይህም በመሆኑ መረጃዎችን በፍጥነት እንለዋወጣለን ብለዋል።

"የአስፓልት መሰንጠቅ ካለ፣ የድልድዮች መሰንጠቅ ካለ አሽከርካሪዎች ጥንቃቄ አድርገው እንዲጓዙ ነው የምናደርገው። ምክራችን ይሄ ነው ሁልጊዜ"። 

ጅቡቲ ለኢትዮጵያ ኅልውና ያላት ወሳኝ ሚና

ኢትዮጵያ 80 በመቶ የነዳጅ ፍጆታዋን በጅቡቲ መስመር የምታገባ እንደመሆኑ በዚህ አካባቢ ያለው የየብስ መጓጓዣ ልዩ ክትትል እና ትኩረት የሚያሻው ነው። ለዚህም ይመስላል ከዚህ በፊት ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው አንድ የዓለም አቀፍ ሕግና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ፤ "ኤርትራ ራሷን የቻለች ሀገር ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ጅቡቲ በኢትዮጵያ የፀጥታ፣ የደኅንነት እንዲሁም የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖራት ተጽዕኖ እና ፋይዳ ከፍ ብሏል" ሲሉ ሀገሪቱንም "ለኢትዮጵያ እንደ ጉሮሮ ሆናለች" በማለት የተረጎሟት። 

አዋሽ-አንታሌና አካባቢዉ በተደጋጋሚ የሚደርሰዉ የመሬት መንቀጥቀጥ የጅቡቲ አዲስ አበባ መንገድን እስካሁን አላወወከዉም።ምስል Solomon Muchie/DW

ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ በመጓጓዣ መስመሩ ላይ ያደረሰው እክል ስለመኖሩ እና የተተለሙ አማራጮች ይኖሩ እንደሆን ለመጠየቅ ወደ ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኔስቴር የሕዝብ ግንኙነት ክፍል የሥልክ ጥሪ ብናደርግም ለጊዜው ልናገኘቸው አልቻልንም።

ሶሎሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ታምራት ዲንሳ


 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW