1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥና ስጋቱ

ሥዩም ጌቱ
ሰኞ፣ ታኅሣሥ 21 2017

«አብዛኞቹ በሬክተር ስኬል ሲታዩ አነስተኛ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴው ግን በመቀጠሉ ከዚህ የከፋ ነገር ቢመጣ፤ ለአብነትም ቅልጥ አለት ቢፈስ ሰውን ለማዳን ዘመቻው ከወረዳ እስከ ፌደራል መንግስት ምን ዝግጅት ተደርጓል ቢባል መሬት ላይ የሚታይ ነገር የለም፡፡» ባለሙያ

Namibia Trockenheit Dürre
ምስል Thomas Sbampato/imageBROKER/picture alliance

የመሬት መንቀጥጥና የፈጠረው ስጋት

This browser does not support the audio element.

የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥና ስጋቱ

በአፋር ክልል እና ኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ በተለይም ፈንታሌ እና ዶፋን ተራሮች አከባቢ በተደጋገመው  የመሬት መንቀጥቀጥ ነዋሪዎች ስጋት ላይ ነን እያሉ ነው፡፡

በአከባቢው እየጨመረ የመጣው የመሬት መንቀጥቀጥ ቀጣይነት ስለሚኖረው፤ ምናባትም ከዚህ የከፋ ችግር እንዳይፈጠር ጉዳዩን በቅርበት በመከታተል አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጥና የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እንዲሰሩ ደግሞ ባለሙያዎች ጠይቀዋል፡፡

“ከሶስት ቀናት በፊት ሁለት ቀን ተከታታይ 11 ሰዓት አከባቢ መሬት የወደቀ እስኪመስል አደገኛ ርዕደት ነበር፡፡ ትናንትና ማታ 5.1 ሬክተር ስኬል ተመዘገበ የተባለውም ከባድ ነው” የአሮሚያ ክልል ፈንታሌ ወረዳ መታሃራ ከተማ ነዋሪ ስጋት ስላጫረባቸው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥን የገለጹበት አስተያየት ነው፡፡

በአከባቢው የመሬት መሰንቀጥቀጥ ምልክቶች መስፋት

አቶ መስፍን መርጋ የተባሉት እኚህ የመታሃራ ነዋሪ በዚህ ቅርብ ርቀት ላይ በሚገኝ አፋር ክልል ፈንታሌ ተራራ ጀርባ ርዕደ መሬቱ የመሬት መሰንጠቅን እያስከተለም እንደሚገኝ ነው ያመለከቱት፡፡ “አፋር ክልል ሳሙሬ የሚባል ከፈንታሌ ተራራ ጀርባ ያለው ስፍራ ላይ ነው መሬት እየተሰነጠቀ ያለው፡፡ የስንጥቁ ቀዳዳም ሆነ ሸለቆውም እየሰፋ ነው የሄደው” ብለዋል፡፡

የአፋር ክልል አዋሽ 7 ኪሎ ነዋሪ አብዱ አህመድ በፊናቸው ዛሬም ድረስ የቀጠለው የመሬት መንቀጥቀጥ የአከባቢውን ነዋሪ ስጋት ውስጥ ከቶታል ባይ ናቸው፡፡ “ትናንትም ሆነ ዛሬ ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ ነበር፤ ሰዎች አሁን አሁን መኖሪያቸውን መልቀቅ ጀምረዋል፡፡ በተለይም አሚባራ መልካወረር፣ ሳቡሬ እና ዶዮኦ አከባቢ የአስፓልት መሰነጣጠቅና የመሬት መከፈል እየሰፋ ስለሆነ ማህበረሰቡ ከፍተኛ መጨናነቅ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እርግብግቢቱ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ ህብረተሰቡ ውጪ ነው እየተኛ ሚያድረው ” ብለዋል፡፡

ሊደረግ የሚገባው ጥናት እና አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ

ነዋሪው መንግስት ለጉዳዩ አስፈላጊውን ትኩረት ሰጥቶ ጥናቶችን በማካሄድ ቅድመ ጥንቃቄዎች መወሰድ አለባቸው፡፡ “ከፈንታሌ ጋር ተያያዥ የሆነ ዶፋን የሚባል ተራራ መልካ ወረር አከባቢ አለ፡፡ ያ ተራራ ክፉኛ እየተንቀጠቀጠ ነው፡፡ እናም መንግስት ዝም ሊለው አይገባም፡፡ አጥኚዎችን አስገብቶ ውጤቱን ለማህበረሰቡ ይፋ ማድረግ አለበት፡፡ ምናልባት መውጣት ያለባቸው የማህበረሰብ አካላት ካሉም በዚያው በጥናቱ መሰረት መነሳት ይኖርባቸዋል፡፡ ከሰም ግድብ በአከባቢው አለ፡፡ ማህበረሰቡ ግድቡ ቢደረመስ  ውሃው ይውጠን ይሆን ብሎ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገብቷልና ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን” ሲሉ ስጋቱ ማየሉንም አንስተዋል፡፡

ነዋሪው ትናንት ከወትሮ በተለየም ከፍተኛ ንዝረቱ ተደጋግሞ መስተዋሉን ተከትሎ የተሳሳተ መረጃም ተሰራጭቶ ማህበረሰቡን ጭንቀት ላይ ጥሎት እንደነበርም አንስተዋል፡፡ “ማታ ተነሱ የሚል ከፍተኛ የመሳሪያ ድምጽ ነበር፡፡ ያ መረጃ በተሳሳተ መልኩ ግድቡ ተሰብሯል የሚል ስለነበር አሚባራ አከባቢ ከብቶቻቸውን ነድተው ከአከባቢው የወጡ ነበሩ” ያሉት አስተያየት ሰጪው የአከባቢው ነዋሪ፤ ይህን የፈጠረው ደግሞ ያለው ስጋትና የጠራ የሚታመን መረጃ ባለመሰጠቱ ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡ ዛሬ ሰኞም የመሬት መንቀትቀጡ በከፍተኛ ድግግሞሽ መጨመሩን የአይን እማኞቹ ገልጸዋል፡፡

«ከወረዳ እስከ ፌደራል መንግስት ምን ዝግጅት ተደርጓል ቢባል መሬት ላይ የሚታይ ነገር የለም» ባለሙያምስል Seyoum Getu/DW

የባለሙዎች ምክርና አስተያየት

በአፋር ክልል አዋሽ አካባቢ ከሰሞኑ ከደረሱት የመሬት መንቀጥቀጥ ክሰተቶች በመጠኑ ከፍተኛ የሆነ ርዕደ መሬት ትናንት እሁድ ምሽት መከሰቱን የገለጸው የጀርመን የጂኦሳይንስ የምርምር ማዕከል፤ የእሁድ ምሽቱ የ2፡10 ርዕደ መሬት አምስት ሬክተር ስኬል ሆኖ መመዝገቡን አመልክቷል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስና ሳይንስ ምርምር ተቋም የሶስሞሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የመሬት መንቀጥቀጥ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ፤ ከሰሞኑ ከፍ ባለ መጠን የተደጋገመው የመሬት መንቀጥቀጥ ቀጣይነት ሊኖረው ስለሚችል ቅድመ ጥንቃቄዎች መወሰድ ይኖርባቸዋል ነው ያሉት፡፡ “ያለፈውን አራት ሰዓት መረጃ እንኳ ብነግርህ በሺዎች የሚቆጠሩ በርካታ ጊዜ የመሬት መንቀጥቀጦች ተከስተዋል፡፡ ግን አብዛኞቹ በሬክተር ስኬል ሲታዩ አነስተኛ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴው ግን በመቀጠሉ ከዚህ የከፋ ነገር ቢመጣ፤ ለአብነትም ቅልጥ አለት ቢፈስ ሰውን ለማዳን ዘመቻው ከወረዳ እስከ ፌደራል መንግስት ምን ዝግጅት ተደርጓል ቢባል መሬት ላይ የሚታይ ነገር የለም” ብለዋል፡፡

ባለሙያው ከዚህ በፊት የተከሰተውን ተመሳሳይ ክስተት ስያስታውሱም፤ “በ1997 ዓ.ም. ተመሳሳይ ነገር በአከባቢው ተከስቶ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ባለሙያዎችን አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተው ከአገር መከላከያ ሄሊኮብት ተመድቦ ባለሙያዎች ተመልክተው ተመልሰዋል” ብለዋል፡፡ እናም አሁንም ተመሳሳይ እርምጃዎች በመንግስት ተወስዶ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ መክረዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
ታምራት ዲንሳ

 

    

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW