1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመሬት ናዳ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለምን ይደጋገማል?

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ማክሰኞ፣ መጋቢት 15 2018

በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ የደረሰውን ጨምሮ ባለፉት አስር ዓመታት በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍሎች በተደጋጋሚ የተከሰቱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች የበርካታ ሰዎች ሕይወት አልፏል። አደጋዎቹ ሲደርሱ ከፍተኛ ሐዘን ቢፈጠርም ሲደጋገሙ የአካባቢው አስተዳደራዊ መዋቅሮችም ይሁኑ ሀገሪቱ ጉዳታቸውን ለመከላከል በቅጡ አለመዘጋጀታቸውን አሳይተዋል።

በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ አካባቢ ነዋሪዎች
በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በደረሰ የመሬት ናዳ 125 ገደማ ሰዎች ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ ለአካባቢው ነዋሪዎች ሰብአዊ ርዳታ ለቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው። ምስል፦ Gamo Zone Government Communication Affairs Department

የመሬት ናዳ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለምን ይደጋገማል?

This browser does not support the audio element.

በደቂቃዎች ልዩነት ሚስትን ፣ ልጆችን እና የልጅ ልጆችን ማጣት በእርግጥም ከባድ ነው፡፡ በጋሞ ዞን  ጋጮ ባባ ወረዳ ማይዞ ዶይሳ ቀበሌ ግን  ይህ ሊሸሹት የማይችሉት አሳዛኝ ክስተት ሆኗል ፡፡ የማይዞ ዶይሳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ዳመነ ደበበ በቀበሌው መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓም በደርሰው የመሬት ናዳ  አራት የቤተሰብ አባሎቻቸውን ማጣታቸውን ይናገራሉ ፡፡

ሁሉም የመጀመሪያው አደጋ የደረሰበት ሥፍራ ተሯሩጦ መድረሱን የሚናገሩት ዳመነ “ እኔ ወደ ቤት ተመልሼ እሷ ግን አለመመለሷን ሳይ በናዳው እንደተበላች አወኩ ፡፡ ሌላኛዋም ልጄ ልጇን እንዳዘለች ሳትመለስ ቀርታለች ፡፡ በአደጋው አራት የቤተሰብ አባላቶቼን አጥቻለሁ “ ብለዋል ፡፡

አሁን ላይ አደጋውን ተከትሎ በመንግሥት ፣ በህብረተሰቡ እና በረድኤት ድርጅቶች አማካኝነት የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ ይገኛሉ  ፡፡ የአደጋው ተጎጂ አርሶአደር ዳመነ ደበበ አሁን ላይ ከጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጀምሮ የክልል ባለሥልጣናት ያሉበትን ሁኔታ መመልከታቸውን ተናግረዋል ፡፡ ይህን ተከትሎም ምግብና የተለያዩ ድጋፎች እየደረሳቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል ፡፡

አቶ ተስፋዬ ዱንዳ በሥፍራው የሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ናቸው ፡፡ ሰዎች የቤተሰብ አባሎቻቸውን በሙሉና በከፊል ያጡበት ከባድ አደጋ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተስፋዬ ማህበራቸው ከምግብ እና አልባሳት ድጋፍ በተጨማሪ በተጎጂዎች ሥነ ልቦና ላይ እየሠራ ይገኛል ብለዋል ፡፡

የናዳው ድግግሞሽ

በደቡብ ኢትዮጵያ እና በአጎራባች ክልሎች በተደጋጋሚ በሚከሰተው የመሬት ናዳ የበርካቶች ህይወት አልፏል ፡፡ በመጋቢት አንዱ የጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ የደረሰው የመሬት ናዳ የ125 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል  ፡፡ የጋጮ ባባ ወረዳ የመሬት ናዳ ክስተት በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ የመጀመሪያው አይደለም ፡፡ ባለፈው የ2017 ዓ.ም ብቻ በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ 229 ፣በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ 11 ሰዎች ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ኮንታ ዞን አመያ ዙሪያ ወረዳ  7 ሰዎች ፣ እንዲሁም በሲዳማ ክልል ወንሾ ወረዳ 6 ሰዎች በናዳ ምክንያት ህይወታቸው እንዳለፈ መረጃዎች ያሳያሉ ፡፡

በመጋቢት መጀመሪያ በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ የደረሰው የመሬት ናዳ የ125 ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል። ምስል፦ Gamo Zone Government Communication Affairs Department

ለመሆኑ የናዳ አደጋ በደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍል በሚገኙ ክልሎችለምን ይደጋገማል ?  ዶክተር ጌትነት መዋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዚክስ ፣ የጠፈር ሳይንስና ስነ-ክዋክብት ተቋም  ተመራማሪ ናቸው ፡፡ የመሬት መንሸራተት በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ በሚገኙ ክልሎች ሊደጋገም የቻለበት የመጀመሪያው መንስኤ ከመሬቱ ተዳፋትነት የተነሳ  ነው ይላሉ ፡፡

አሁን አደጋው የተከሰተባቸው ቦታዎችን ብንመለከት ወጣገባ የበዛበት ነው በማለት የጠቀሱት ዶክተር ጌትነት “ ይህንን ተከትሎ የህዝቡ አሠፋፈርና የመሬት አጠቃቀም ሁኔታው ለናዳው ተጨማሪ  ምክንያት ነው ፡፡ የመሬት ናዳ የሚከሰተው በአብዛኛው የክረምት የዝናብ ውሃን ተከትሎ ነው ፡፡ አደጋ የሚያስከትለውም የዝናብ አርጥበትን የያዘው ተዳፋታማ መሬት ሚዛኑን መጠበቅ ሲሳነው በሚፈጥረው እንቅስቃሴ የተነሳ ነው “ ብለዋል ፡፡

የሥምጥ ሸለቆ እንቅስቃሴ መላምቶች

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አብዛኞቹ ዞኖች የታላቁ ስምጥ ሸለቆ የሚያልፈባቸው አካባቢዎች ናቸው ፡፡በርካቶች የመሬት መንሸራተት ድግግሞሹ ከዚሁ የስምጥ ሸለቆ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል የሚል  መላምቶችን ያስቀምጣሉ ፡፡ ይህ ምን ያህል ሳይንሳዊ መሠረት አለው በሚል የተጠየቁት  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዝክስ የህዋ  ሳይንስና ሥነ ክዋክብት ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ተመራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር አታላይ አየለ የመሬት መንሸራተት ከሥምጥ ሸለቆ ተፈጥሮ ባህሪ ጋር የቀጥታ ግንኙነት የለውም ብለዋል ፡፡

እርግጥ ነው አካባቢው የሚታዩት ተራራዎችና ኮረብታዎች የተፈጠሩ ከመሬት በሥምጥ ሸለቆ የተፈጥሮ ሂደት ጋር የመጡ ናቸው በማለት የጠቀሱት ፕሮፌሰር አታላይ “ ነገር ግን የመሬት መንሸራተት አይነት አጫጭር ክስተቶች የሚመጡት ከሰዎች አኗኗርና ከመሬት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ እንጂ ከሥምጥ ሸለቆ እንቅስቃሴ ጋር የተገናኘ አይደለም “ ብለዋል ፡፡

በጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ ነዋሪዎች ርዳታ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነውምስል፦ Gamo Zone Government Communication Affairs Department

አደጋውን እንዴት መከላከል ይቻላል ?  

የጋሞ ዞን ጋጮ ባባ ወረዳ በደረሰው የናዳ አደጋ ተጎጂው ዳመነ ደበበ ሁኔታው አሁንም አስቸጋሪ እንደሆነ ይናገራሉ ፡፡ በመንደሩ በቀጣይ ተመሳሳይ አደጋ ሊከሰት ይችላል የሚለው ሥጋት እሳቸውን ጨምሮ የአብዛኛው ነዋሪ መሆኑን የጠቀሱት አርደሶአደሩ መንግሥት በሠፈራ መልክ ወደ ሌላ አካባቢ ቢያዛውራቸው የተሻለ እንደሆነ ይናገራሉ ፡፡
የመሬት ናዳ አደጋን አስቀድሞ ለመከላከል  ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው ሁለቱ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ ፡፡ ይሁንእንጂ ጉዳዩ አደጋው በተከሰተበት ወቅት ብቻ አጀንዳ ሆኖ ከማለፍ በስተቀር በጥናት ላይ የተመሠረተ መፍትሄ ከመስጠት አንጻር ተገቢውን ትኩረት አግኝቷል የሚል እምነት እንደሌላቸው ጠቅሰዋል ፡፡

በእርግጥ በደቡባዊው የኢትዮጵያ ክፍልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ከመሬት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን /  በሙሉ ማስቀረት እንደማይቻል አብዛኞች የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ ፡፡ ይሁንና የነዋሪውን አሠፋፈር በማስተካከልና የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረግ ጉዳቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደሚቻል የጠቀሱት ዶክተር ጌትነት “ የመኖሪያ ፣ የእርሻ  ፣ የደን መሬትን በመለየትና ተራራማና ተዳፋት የሆኑ  አካባቢዎችን ባለማረስ አደጋውን መቀነስ ይቻላል “ ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ  

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW