1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ፀሀይ ጫኔ
ዓርብ፣ ጥቅምት 15 2017

በአዲስ አበባ መርካቶ ሸማ ተራ የደረሰው የእሳት አደጋ፣ አስገድዶ መሰወር እና እገታን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ እንዲሁም ባለፉት 3 ወራት ለጎረቤት ሀገራት በተደረገ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ30 ሚሊየን ዶላር በላይ ተገኘ መባሉ በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ጉዳዮች ነበሩ።

Social Media App Symbolbild
ምስል Jonathan Raa/NurPhoto/picture alliance

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

This browser does not support the audio element.


 በዛሬው የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ፤ በአዲስ አበባ መርካቶ  ሸማ ተራ አካባቢ በደረሰው የእሳት አደጋ፣ አስገድዶ መሰወር እና እገታን በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ እንዲሁም ባለፉት 3 ወራት ለጎረቤት ሀገራት በተደረገ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ከ30 ሚሊየን ዶላር በላይ ተገኘ መባሉን በተመለከተ  የተሰጡ አስተያዮቶችን አሰባስበናል። አብራችሁን ቆዩ።

በመርካቶ ሸማ ተራ የደረሰ የእሳት ቃጠሎ

በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እጅግ መነጋገሪያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በአዲስ አበባበመርካቶየገበያ ቦታ በተለምዶ ሸማ ተራ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ የደረሰ የእሳት አደጋ ነበር። በሳምንቱ መጀመሪያ  ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017  ዓ.ም የተከሰተው ይህ የእሳት አደጋ በቁጥጥር ስር ሳይውል በመቅረቱ መጠኑ በይፋ ባይገለፅም በቃጠሎው በርካታ ንብረት መውደሙ እየተነገረ ነው። ምንም እንኳ ሥለቃጠሎዉ ያሰባሰበዉን መረጃ  የአካባቢዉ ባለሥልጣናት መሆናቸውን የገለፁ ሰዎች በሙሉ ቢሰርዙበትም፤ አካባቢውን  የተመለከተዉ የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ሥ ዩም ጌቱየእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች እሳቱን ለማጥፋት እስከ ረፋድ  ድረስ ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ መመልከቱን ገልጿል።
በወቅቱ የተከሰተውን ቃጠሎውን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት አደጋውን ቶሎ ለመቆጣጠር የተደረገውን ጥረት  አዳጋች ያደረገዉ የአካባቢው መንገድ ለእሳት አደጋ መኪና አስቸጋሪ በመሆኑ ነው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ በበኩሉ፤  በደረው የእሳት አደጋ የተሰማውን ሐዘን ገልፆ ስለአደጋው ወደፊት በምርመራ የደረሰበትን ውጤት ለህዝብ እንሚያሳውቅም ዐሳ ውቋል፡፡
ይህንን ተከትሎ ተስፋ ሰላም«ቦታው ለልማት ተፈልጎ እንዳይሆን»ሲሉ፤ጆኒ መላኩ ይህንኑ ሀሳብ በመደገፍ «ሆን ተብሎ አንዱን ነቅሎ አንዱን ለመትከል የተሰራ ሴራ ይመስላል።»ብለዋል። ያዳኖ ጉያቻ «የቆሞ-ቀር አስተሳሰብ!»ሲሉ ነቅፈዋል።«መቀማት ሲፈልጉ ቦታውን እሳት ይለቁበታል የሕዝቡን የስንት ዓ መት ልፋት መና አድርገው ኑሮውን ገሀነም ያደርጉታል።ፈጣሪ ለሁሉም ይከፍላል የጊዜ ጉዳይ ነው።»ያሉት መሳይ ዋቄ ናቸው።አሴ አሴሁሬ በሚል የፌስቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት«በኢህአዲግ ህወሀት ዘመንም ተመሳሳይ አደጋ ሲያጋጥም ሆን ብለው በስውር አቃጥለው ቦታውን ለባለ ሀብት ሊሸጡ ነው ስትሉ ነበር።አሁንም ሌሎችን ነቅለው ለመትከል ነው ከምትሉት ጭፍን ጥላቻ እና ፍረጃ ውጭ ፤ ከበቦታው ካሉት ነጋዴዎች መካከል አንድ ወይንም ሁሉት ወይንም የተወሰኑት በፈጠሩት የጥንቃቄ ጉድለት የተነሳ የተፈጠረ የቃጠሎ አደጋም ሊሆን አይችልም ?» ሲሉ ጠይቀዋል።ገነት ዋለልኝ«መረጃ እዲጠፋ ከተደረገ ነጋዴን ለመጎዳት ሆን ተብሎ የተፈፀመ ድርጊት ነዉ።ብለን ብንጠረጥር ምን ይፈረዳል።አላህ የተሻለዉን ይተካቸዉ።» ብለዋል።ናቲ ታሜ«የእሳት ቃጠሎ እንኳን መዘገብ የማይቻልበት ጊዜ ተደረሰ»ሲሉ፤ፋሲል ታዬ«ፈጣሪ ይድረስላችሁ ወገኖቼ ሴራውን ያጋልጥላችሁ።»ብለዋል።
«ምን እንላለን በእሳትም አንማርም ፣በጎርፍም አንማርም ፣ በዚህ አጋጣሚ ኮርደር ልማቱ ይሰራል አስፈላጊ መሆኑ ታይቷል።»ብለዋል ማርክነህ መኬቦ።ያሬድ ወንዴም«ስለኮሪደር ልማት  እውነታውን ለመቀበል ጊዜ ቢፈጅብንም ሀቁ ግን ይሄ ነው ሲሉ አስተያየቱን ደግፈዋል!» 
 «በስንት ውጣውረድ ለፍተው ያፈሩት ሀብት በአንድ ጀምበር አመድ ሲሆን ያሳዝናል።ከቃጠሎው መታደግ ባይችል እንኳ መንግስት በተቻለ መጠን ቢያቋቁማቸው ጥሩ ነው።»የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል ሙሄ ደጉ፤ የተጨቆኑ ግጥሞች «እርግጠኛ ነኝ ከወር በሗላ መርካቶ ለመንቀሳቀስ ምቹ አይደለችም ተብሎ በኮሪደር ልማት ሰበብ መፍረሷ አይቀርም። »ሲሉ የራሳቸውን ትንበያ አስቀምጠዋል።መጀመሪያ ተጎጂዎችን ማፅናናት፡ ማጠናከር፡ ከጎናቸው መሆን፡ እንጂ ለቃጠሎው ፖለቲካዊ  ሽፋን መስጠት  ፍፁም የተሳሳተና፡ ተጎጂዎችንም የማይጠቅም ነው» ያሉት ደግሞ  ፅናቱ ፅናቱ የተባሉ አስተያየት ሰጪ ናቸው። ክቤ የአዱገነቷ በሚል የፌስ ቡክ ስም «እሳት አደጋው ከባድ ነበር ከፍተኛ ውድመት ድርሷል ኮሪደር ልማት ለጊዜው ቆሞ እነዚህን ከፍተኛ ግብር ከፋፋዮች ማቋቋም ይገባል»የሚል ሀሳብ አስፍረዋል።

የእሳት አደጋው በቁጥጥር ስር ሳይውል በመቅረቱ መጠኑ በይፋ ባይገለፅም በቃጠሎው በርካታ ንብረት መውደሙ እየተነገረ ነው። ምስል Yared Shumete

በአስገድዶ መሰወር እና እገታ ላይ የኢሰመኮ መግለጫ

ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አነጋጋሪ ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ መደበኛ ባልሆነ ማቆያ ቦታ ተይዘው ለሚቆዩ፣ ያሉበት ሳይገለጽ እንዲቆዩ ለሚደረጉ እና አስገድዶ መሰወር ለሚፈፀምባቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች እና ቤተሰቦቻቸው ፍትሕ እንዲሰጥ፣ ተጠያቂነትም እንዲሰፍን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መጠየቁ  ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዚህ ሳምንት ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በአዲስ አበባ፣ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ ከ52 በላይ ሰዎችን አቤቱታዎች መመርመሩን አስታውቋል።ተጎጂዎች በአብዛኛው ሰሌዳ በሌላቸው ተሽከርካሪዎችና በታጠቁ ሲቪል ወይም የደንብ ልብስ በለበሱ የፀጥታ አካላት «በግዳጅ የተያዙ መሆናቸውን» ያስታወቀው ኮሚሽኑ የፀጥታ አካላት ከተያዙ ሰዎች ቤተሰቦች ጋር ድርድር በማድረግ ሁኔታውን የገንዘብ ማግኛ ምንጭ የማድረግ ሕገ ወጥ ድርጊት መታየቱንም አመልክቷል።
ተሰማ ብርሃኑ«መንግስት ሽፍታ የሆነባት ሀገር አይ ኢትዮጵያ» ሲሉ፤ኖህ ሔኖክ«ከፍለው የሚወጡ ታሳሪዎች ብዙ ናቸው!!! ማለት ምን ማለት ነው።»ብለዋል።ድንቁ ዓለሙ«የመረጃው ትክክለኝነት ከተጋች እና ከታጋች ቤተሰብ ከሆነ ሚዛን አይደፋም»ሲሉ፤ ቤካ በቀለ«ኢሠመኮ የተቋቋመው የመንግስትን ፀጥታ ሀይል ስም ለማጥቆር ብቻ ነው እንዴ?»ብለዋል።ማኔ ኢትዮጵያ «ወዴት እየሄድን ነው ለማለት ዘግይተናል። ግን ከሄድንበት ኢ-ሰዋዊነት መቼ ነው የምንመለሰው?»ብለዋል።ደበበ አራዳው «ፍትህ ለተጎዳው ህዝብ»ብለዋል።ዳዊት ታደሰ «ለምን ይሆን  ይህንን የሰብአዊ መብት ጥሰት ለተባበሩት መንግስታት ለአውሮፓ ህብረት ማጋለጥ ያልተቻለው።» ብለዋል።አብቧል ያምራልl«ችግሩን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ ከአጋቾቹ መካከል የመንግስት የፀጥታ አካላት  መኖራቸው ነው፡፡»ሲሉ፤ ምናለ ሀገሬ «ከመንግስትም ከሀገርም ሸሽተን የት እንድረስ»ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተወስደው ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የቆዩ ከ52 በላይ ሰዎችን አቤቱታዎች መመርመሩን አስታውቋል።ምስል Solomon Muche/DW

ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ

ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ተገኘ መባሉ ሌላው በዚህ ሳምንት በማኅበራዊ መገኛኛ ዘዴዎች መነጋገሪያ የነበረ ጉዳይ ነው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን ጠቅሰው የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃ ን እንደዘገቡት በበጀት ዓመቱ ባለፉት ሦስት ወራት 6 ሺህ 456 ጊጋ ዋት ሠዓት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለጎረቤት ሀገራት ማቅረብ የተቻለ ሲሆን፤ ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። ገቢው የተገኘውም ለጅቡቲ፣ ሱዳን እና ኬኒያ 497 ነጥብ 8 ጊጋ ዋት  የኤሌክትሪክ ኃይል በመሸጥ መሆኑም ተመልክቷል፡፡በቀጣይ ለታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መሆኑም ተመልክቷል።
ይህንን ተከትሎ ሂወት ጌታቸው በፌስቡክ «እኮ የኛን እያጠፋቹ»ሲሉ፤ ጌጡ ቤስት«ጥሩ ነው ግን ይሄን ዜና ስንሰማ እኛ ሰፈር ደግሞ መብራት የለም የጉድ ሀገር።»ብለዋል። ማሜ ቡን ከይር ደግሞ «የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች አሉ።ለመሆኑ ሱዳን የተጠቀመችውን እዳ ከፍላለች ?»ሲሉ ጠይቀዋል።ስሓቅ ብታራ እያ፤ «ቀልዳቹ እኮ አይጠገብም »ብለዋል። ሆፕ ሆፕ በሚል የፌስቡክ ስም ደግሞ «ለካ መብራት ሚሄደው ዶላር ሊያመጣ ነው» ሲሉ ቀልደዋል።ሀይሚ ሃይሚ« ለግድቡ ያወጣነውን ብር መልሱልን ሻማ እንግዛበታለን።»በማለት ፅፈዋል።«

የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ምስል Tim Wegner/epd-bild/picture alliance

ይህ አስደሳች ዜና ነው።31 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ከኤለክትሪክ ሽያጭማግኜት የሚያሳየው ሀገሪቱ በሀይል አቅርቦት ዘርፍ ያላትን አቅም ነው።ወደ ሱዳን እና ታንዛኒያ ማስፋፋቱ ኢኮኖሚን ማሳደግ ብቻ ሳይሆን  ቀጠናዊ ትስስርንም ያጠናክራል።»በማለት በእንግሊዝኛ። የፃፉት ተስፋዬ ዘላለም ናቸው።እድላዊት የአባቷ ልጅ ደግሞ «የደላው ሙቅ ያኝካል» ብለዋል።ደብሊው ኤች አባተ «ለውጭ አልጋ ለውስጥ ቀጋ።»ሲሉ፣«ዘንድሮ እኮ ጎረቤት ብንሆን ይሻለን ነበር ጎበዝ።»ብለዋል ዳዊት ገብረማርያም። ሰኒ ግርማ«አባይ ሲገደብ ለ ኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም መስሎኝ ነበር ጭራሽ መብራት እና ውሃ ታሪፍ ጨመረ ጌታ ሆይ ደጉን ቀን አምጣልን» ሲሉ ተመኝተዋል።በእርሱ ፈቃድ ይሁን«የኛ ሀገር ማለት የለኝም ብሎ ለቤቱ ሽሮ እየሸመተ ለውጪ ሰው ቁርጥ የሚጋብዝ አይነት አባት ነው ።»ብለዋል።
ሳም ታምሩ «ቢያንስ አንዳንድ መረጃዎች ለህዝብ  ባይወጡ እና እዛው በሚመለከታቸው መ/ቤቶቾ ውስጥ ተቀምጠው በውስጥ ለውስጥ ማስታወሻ መልክ መረጃውን ቢቀያየሩት ንዴታችንን ይቀንሱታል ። ምንም ስለማንሰማ ለመልስ ምት እና ለትዝብትም አይዳርጉንም ።በዚህ ብቻ ተባበሩን ።»
ባሮክ አባተ «ለውጪ አልጋ ለቤት ቀጋ ይልሃል እንደዚህ ነው። እኛ ከተማ ውስጥ እየኖርን በቅጡ መብራት አናገኝም እናንተ ከተሸጠ የተገኘ ገቢ ትላላቹ ።መሸጡን ገቢ ማግኘቱ ጥሩ ነው። ግን መጀመሪያ ያማረራችሁትን  ህዝብ በቅጡ አገልግሉት።»ብለዋል።
ማየ ዮርዳኖስ ዘብሔረ አግኣዚ ደግሞ«47% የኤሌክትሪክ ሽፋን ያላት ሀገራችን 87% የኤሌክትሪክ ሽፋን ላላት ኬንያ ኀይል እየሸጠች ነው። ግሩም ነው።»ሲሉ፤እስማኤል አባ ጀበል «ህይወት ሚዛናዊ አይደለችም።»በማለት መንግስትን ሳይሆን ህይወትን ኮንነዋል።

ፀሐይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW