የመሰረተልማት ውድመት በቤኒሻንጉል
ዓርብ፣ ሐምሌ 29 2014
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ባለፉት ዓመታት በነበረው የጸጥታ ችግር ወደ 80 ቢሊዩን ብር የሚገመት ንብረት መውደሙን የክልሉ መንግስት አስታወቀ፡፡ በክልሉ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለመለየት እስካሁን በተደረገው የመጀመሪያው ምዕራፍ ጥናት 189 የጤና ተቋማት፣42000 የግለሰብ ቤቶች እና 211 ትምህርት ቤቶች መውደማቸው የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኃለፊ አቶ ታቀረኝ ታሲሳ ተናግረዋል፡፡ የወደመውብረት 79.4 ቢሊዩን ይገመታል ተብሏል።
ከጥቅምት 2013 ዓ.ም አንስቶ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር የደረሰውን ጉዳት መጠን ለመለየት ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ 39 የሚደረሱ ባለሙያዎች በጥናት ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኙ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ይፋ አድርጓል፡፡ እስካሁን በተደረገው ጥናት መሠረት በክልሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ሙሉ በሙሉ መልሶ ለማቋቋም ከ2 እስከ አምስት ዓመት እንደሚፈጅ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በነበሩት የሰላም መናጋት ለማህበረሰቡ አገልግሎት በሚሰጡ የግብርና፣የጤና እና ሌሎችም ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን አቶ ታረቀኝ አስረድተዋል፡፡ የወደመውን ንብረት መልሶ ለመገንባትና መደበኛ አገልግሎት ለማስጀመርም ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚጠይቅ አክለዋል፡፡ በተወሰኑ አካባቢዎች ዜጎች ሸሽተው ከነበሩበት ስፍራ በየወረዳው በተዘጋጀው መጠለያ ጣቢያ እየተመሰሉ እንደሚገኙም ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
ሐምሌ 22/2014 ዓ.ም በተካሄደው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን የጠላት ተልዕኮን ለማስፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር ያሏቸው ሀይሎች በክልሉ ካማሺና መተከል በትምህርት ቤቶች እና ጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሳቸውን አብራርተዋል፡፡
ከከልሉ በርካታ ተፈናቃይ የሚገኙው በመተከል ዞን ሲሆን በዞኑ ጉባ ወረዳ 3 ሺ የሚደርሱ ዜጎች ወደ ቀያአቸው መመለሳቸውን እና በአካባቢው ተቋርጦ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ዳግም መጀመሩ ተገልጸዋል፡፡ የቤኒሻንል ጉሙዝ ብልጽግና ፓርቲ ከዚህ ቀደም በዞኑ በነበረው የጸጥታ ችግር ውስጥ እጃቸው አለበት ያላቸውን አመራሮች ከወረዳ እስከ ዞን ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ አድርጓል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ካልሚ ሀሚድ የጸጥታ ችግር በሚስተዋልባቸው የክልሉ አካባቢዎች የዕርቀ ሰላም ጉባኤዎችን በማካሄድ፣ በአስቼኳይ ጊዜ አስተዳደር ወይም ኮማንድ ፖስት ደግሞ የተለያዩ አሰሳዎችን በማድረግ በተገኘው ሰላም የተሳካ ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እና ተፈናቃዩችን ለማቋቋም ያስችላል የተባለውን ጥናት አሶሳ ዩኒቨርሰቲ በበላይነት የሚያስተባብር ሲሆን ከ475ሺ በላይ ተፈናቃዩች እንደሚገኙም በጥናቱ ይፋ ተደርገዋል፡፡ የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ እስካሁን 42ሺ የሚደርሱ ሰዎች ተመዝግቦ እንደሚገኙ ገልጾ በጥናቱ የተገለጹት ከክልሉ ወደ ሌላ ስፋራ የተፈናቀሉትን እንደሚጨምር ጠቁሟል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር
ኂሩት መለሰ