የመስቀል በዓል አከባበር በትግራይ
ቅዳሜ፣ መስከረም 17 2018
በየዓመቱ በክርስትያኖች ዘንድ በድምቀት የሚከበር የመስቀል በዓል ዘንድሮም በትግራይ በባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ስነስርዓት እየተከበረ ይገኛል። በዛሬው ዕለት በመቐለ እና ዓዲግራት ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ደማቅ የመስቀል በዓል አከባበር ስነስርዓቶች እየተደረጉ ያለ ሲሆን በተለይም በዓዲግራት በርካታ ከሀገር ውስጥ እና ውጭ የመጡ እንግዶች በበዓሉ ታድመዋል። በትግራይ ምስራቃዊ ዞን የሚገኙ የኢሮብ ማሕበረሰብ አባላት የመስቀል በዓል በተለየ የሚያከብሩ ሲሆን፥ ግዕዝም እና ጥሕሎ የመሳሰሉ ልዩ የበዓል ምግቦች በዋነኝነት ለበዓሉ ይቀርባሉ።
በትግራዩ ጦርነት ምክንያት በኢሮብ ጨምሮ በአጠቃላይ ትግራይ የመስቀል በዓል አከባበር ተቀዛቅዞ የቆየ ሲሆን፥ አንፃራዊ ሰላም ተከትሎ ዘንድሮ በተለይም በድንበር ከተማዋ ዓዲግራት የመስቀል በዓል ደምቋል። ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች እንዲሁም ከተለያዩ ሀገራት የተጓዙ የአካባቢው ተወላጆች እና ሌሎች እንግዶች መስቀል በዓዲግራት ታድመዋል። ተቀዛቅዛ የቆየቸው ዓዲግራት ከተማም ደምቃለች።
ከዚህ በተጨማሪ በመቐለ ጮምዓ ተራራ የመስቀል ደመራ በዓል በትላንትናው ዕለት በድምቀት የተከበረ ሲሆን፥ የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና የክልሉ ባለስልጣናት ወደተራራው በመውጣት በዚሁ ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ታድመዋል። በጮምዓ ተራራ አናት ላይ 54 ሜትር የሚገመት በብረት የተሰራ መስቀል ያለ ሲሆን፥ ይህንኑ ግዙፍ መስቀል በመብራት እና ችቦ አጊጦ ለከተማዋ ድምቀት ሆንዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሽረ፣ ማይጨው እና ሌሎች ከተሞችም የመስቀል በዓል በሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክንዋኔዎች እየተከበረ ይገኛል።
ሙሉ ቃለምልልሱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ሚሊዮን ኀይለስላሴ
ፀሀይ ጫኔ