የመስከረም 12 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ መስከረም 12 2018
በጃፓን ቶኪዮ 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከ34 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ያለምንም የወርቅ ሜዳሊያ ተመልሳለች ። ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ዋነኛ ተፎካካሪዎቹ እነ አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ ነጥብ ሲጥሉ፤ ሊቨርፑልን ግን የሚያስቆመው አልተገኘም ። በአምስቱም ግጥሚያዎች አሸንፎ ዘንድሮም ብርታቱን ዐሳይቷል ። ሔሪ ኬን ሦስት ግቦችን ከመረብ አሳርፎ ሔትሪክ በሠራበት የጀርመን ቡንደስሊጋ ባዬርን ሙይንሽን በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው ።
ኢትዮጵያ በቶኪዮ የዓለም ውድድር ለምን ደካማ ውጤት አስመዘገበች?
ኬንያ ከአፍሪቃ አንደኛ ከዓለም ሁለተኛ ደረጃ ይዛ ባጠናቀቀችበት 20ኛው የቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር፦ ኢትዮጵያ ያለአንዳች ወርቅ ተመለሰች ። በማጣሪያ ውድድሩ ሳይቀር አትሌቶች ውድድራቸውን ማቋረጣቸውም ተስተውሏል ። ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ አንድም የወርቅ ሜዳሊያ ሳታገኝ በሁለት የብር እና በሁለት የነሐስ ሜዳሊያዎች ብቻ ተወስና ነው በ22ኛ ደረጃ ያጠናቀቀችው ። ከአፍሪቃ አገራት መካከል፦ ንዑሷ ቦትስዋና እንኳ በሁለት የወርቅ እና በአንድ የነሐስ ሜዳሊያ የአምስተኛ ደረጃ አግኝታለች ። ታንዛኒያ በበኩሏ በአንድ ብቸኛ የወርቅ ሜዳሊያ ከኢትዮጵያ በላይ 19ኛ ደረጃ ይዛ አጠናቅቃለች ።
ኢትዮጵያ ባልተለመደ መልኩ ከወርቅ ሜዳሊያም ከደረጃም ውጪ በመሆን ዝቅተኛ ደረጃ ይዛ ነው ከውድድሩ የተመለሰችው ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን በልዑክ ቡድኑ የሽኝት መርኃ ግብር ላይ ባሰሙት ንግግር፦ «በአጠቃላይ ለዚህ ውድድር 65 የልዑካን ቡድን ተመርጠው» መዘጋጀታቸውን ገልጠው ነበር ። «በተቻለ መጠን ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንሞክራለን» ሲሉም ተደምጠው ነበር ። ለ40 ቀናት ሆቴል ተቀምጦ ሲዘጋጅ የነበረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን እንዲህ ከደረጃ በታች የሆነ ውጤት ያመጣበት ምክንያቱ ምን ይሆን? በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት መርኃ ግብር ዋና አዘጋጅ ምስጋናው ታደሰ ።
«ብዙ የተዘጋጀ ግን ደግሞ የኢትዮጵያን ልዑክ የማይመጥን ቡድን ያየንበት ውድድር ነበር ከዝግጅታቸው ጀምሮ» ያለው ምስጋናው አትሌቶችወደ ሞቃት ቦታ እንሂድ አንሄድም በሚል ሲወዛገቡ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንደ አንድ መሪ ከውሳኔ ላይ አልደረሰም ብሏል ። ለውጤቱ መዳከም ዋነና ችግር የፌዴሬሽኑ ውሳኔ ሰጪነት ላይ ያሳየው መዳከም ነው ሲልም አክሏል ።
በአትሌቶች መካከል የብሔራዊ መንፈስ ያስፈልጋል
ለመሆኑ አፍሪቃዊ የዘር ሐረግ ያላቸው ሳይሆኑ ከዛው ከአውሮጳውያን ቤተሰቦች የተገኙ አውሮጳውያን አትሌቶች ከተለመደው ውጪ የበላይ የሆኑበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ቀጣዩ ጥያቄ ነበር ። «ይሄ ምንም ጥርጥር የለው የበላይነታችን ተነጥቆ ወደ አውሮጳ ተወስዷል» ያለው ምስጋናው ኬንያን ጨምሮ በተለይ በዘመናዊ የአሰለጣጠን መርኅ መመራታቸው እንዳስበለጠን ጠቅሷል ። የመስከረም 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በልዑክ ቡድኑ በአንዳንድ ግለሰቦች እና አትሌቶች መካከል ቅራኔ እና የከረረ ጠብ ተስተውሏል፤ የብሔራዊ ቡድን መንፈስ እንዳልነበረም ይነገራል ። ወደፊት ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ እንደቀድሞው ወኔ በተቀላቀለበት እና ብሔራዊ ስሜት በተንጸባረቀበት መልኩ ለአገር በወኔ ውጤት ለማስመዝገብ ምን ይደረግ ትላለህ?
«የብሔራዊ ቡድን መንፈስ እንዲኖር፦ «» መደረግ አለበት ብሏል፥ የኬንያን የርስ በርስ አለመግባባት ችግር ጠቅሷል ። ኬንያውያን ብሔራዊ እርቅ አድርገው ወደ ውድድር መግባታቸው ለውጤት አብቅቷቸዋል ብሏል ። ኢትዮፕያውያን አትሌcዕን በተመለከተ በውድድር ወቅት የታዘበውን ሲጠቅስም፦ «አንደኛዋ አትሌት ከግራ ወደ አን ስትሮጥ ሌላኛዋ ከቀን ወደ ግራ ትሮጥ ነበር» ትዝብቱን ገልጧል ። «አሰልጣኞች እርስ በእር ሲሰዳደቡ ተመልክቻለሁ፤ አትሌቶች አይነጋገሩም፤ ሁለት አሰልጣኞች ተንቀሳቃሽ ስልክ እስከመወራወር በደረሰ ጠብ ግብ ግብ መፍጠራቸውን ዐይተናል » ብሏል ። «አንቺ ባለሽበት ክፍል አልተኛም» ያለች አትሌት መኖሯንም ጠቅሷል። በአጠቃላይ የቡድን ሥራ መጥፋቱን ጠቅሷል ። «ብሔራዊ የሆነ መፍትኄ እና እርቅ ከሌለ ብሎም ፌዴሬሽኑ ጥርስ ያለው አንበሳ ካልሆነ በስተቀረ መፍትኄ የሚመጣ አይመስለኝም» ሲል አክሏል ።
በስምንት መቶ ሜትር የሴቶች የፍጻሜ ፉክክር ኬንያ ትናንት ተጨማሪ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች ። ኬንያ ወርቅ ያገኘችው በአትሌት ሊሊያን ዖዲራ ሲሆን፤ ውድድሩን ያጠናቀቀችበት ጊዜ (1:54.62)ሆኖ ተመዝግቧል ። በዚህ ውድድር ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ያገኙት የአውሮጳ ሯጮች ናቸው ። ጆርጂያ ሐንተር (1:54.90)እና ኬሊ ሆድግሰን (1:54.91) የብር እና የነሐስ ሜዳሊያዎቹን ወደ ብሪታንያ አስገብተዋል ።
ኬንያ ከዓለም ሁለተኛ ከአፍሪቃ አንደኛ ስትወጣት ኢትዮጵያ በ22ኛ አጠናቅቃለች
ኬንያ በአጠቃላይ 11 የሜዳሊያ ብዛት ከዩናይትድ ስቴትስ ቀጥላ ከዓለም የሁለተኛ ደረጃ አግኝታለች፥ ከአፍሪቃ ደግሞ የመጀመሪያ ደረጃ ተቀዳጅታለች ። ኬንያ የትናንቱን ወርቅ ጨምሮ 7 የወርቅ ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች፥ ቀሪዎቹ የኬንያ ሜዳሊያዎች ሁለት የብር እና ሁለት የነሐስ ናቸው ። የጳጉሜ 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ከአውሮጳ አገራት መካከል ጀርመን አምስት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ 12ኛ ደረጃ ይዛለች ። ለጀርመን ሦስቱ ሜዳሊያዎች የተገኙት የአፍሪቃዊ የዘር ሐረግ ባላቸው አትሌቶች ነው ። ለጀርመን የወርቅ ሜዳሊያ ያስገኘው ካሜሩናዊ አባት እና ጀርመናዊት እናት ያለው አትሌት ሌዎ ኖይጌበር በዴካትሎን ፉክክር ነው ። ከሌዎ ቀደም ብሎ በነበረ ፉክክር ትውልደ ኤርትራዊው ዓማናል ጴጥሮስ በማራቶን የነሐስ ሜዳሊያ ለጀርመን አስገኝቷል ። ጀርመናዊ እናት እና ዛንዚባራዊ አባት ያላት ማላይካ ምሐምቦ በርዝመት ዝላይ የብር ሜዳሊያ አጥልቃለች ። ጀርመናዊው ሜርሊን ሑመል በብረት ሉል ውርወራ የብር እንዲሁም በ4 ጊዜ 100 ሜትር የዱላ ቅብብል ፉክክር የነሐስ ሜዳሊያ ለጀርመን ተገኝቷል ። በዱላ ቅብብሉም የአፍሪቃዊ የደም ሐረግ ያላቸው አትሌቶች ተሳትፈዋል ።
በጃፓን ቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ዩናይትድ ስቴትስ 16 የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ በአንደኛ ደረጃ አጠናቅቃለች ። አምስት የብር እና አምስት የነሐስ ሜዳሊያዎችንም አግኝታለች ። ከኬንያ ቀጥላ በሦስኛ ደረጃ ያጠናቀቀችው ካናዳ ሦስት የወርቅ፤ አንድ የብር እና ሌላ አንድ የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች ።
እግር ኳስ
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች ዓለም ዋንጫ ማጣርያ የእግር ኳስ ግጥሚያ የኢትዮጵያ ቡድን ከኬንያ አቻው ጋር አንድ እኩል ተለያቷል ። ትናንት አዲስ አበባ ውስጥ በተከናወነው ሁለተኛ ዙር የመጀመርያ ጨዋታ ኬንያ ጨዋታው በተጀመረ አንድም ደቂቃ ሳይሞላ ነበር በሚሼል ሙታማ ያስቆጠረችው ። ግቡ በጨዋታ መጀመሪያው ጥቂት ሰከንዶች ውስጥ የተቆጠረው በተከላካዮች መናበብ ችግር እና በግብ ጠባቂ ኳሷን በአግባቡ ያለማጨናገፍ ወይንም አለመያዝ ችግር ነው ። ከረፍት መልስ በ66ኛው ደቂቃ ላይ እሙሽ ዳንኤ ባስቆጠረችው ግብ ኢትዮጵያ አቻ ወጥታለች ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሊቨርፑል ዘንድሮ አንድም ጊዜ ነጥብ ሳይጥል በመሪነቱ እየገሰገሰ ነው ። ቅዳሜ ዕለት እጅግ ሲጠበቅ በነበረው የአንድ ከተማ ቡድኖች ግጥሚያ ማለትም «ደርቢ» ኤቨርተንን 2 ለ1 አሸንፏል ። ሊቨርፑል በፕሬሚየር ሊጉ አጠቃላይ አምስት ግጥሚያዎች በማሸነፍ ዘንድሮም አይበገሬነቱን ዐሳይቷል ። የቅዳሜው ደርቢ ድል ባለፈው ረቡዕ በሻምፒዮንስ ሊግ አትሌቲኮ ማድሪድን 3 ለ 2 ካሸነፈ ጥቂት ቀናት በኋላ የተገኘ ነው ። ይህም የቡድኑ ተጨዋቾች በተደጋጋሚ ወሳኝ ግጥሚያዎች ድካም ሳይበግራቸው መዝለቅ እንደሚችሉ ያስመሰከሩበት ነው ።
ሊቨርፑል አትሌቲኮ ማድሪድን ድል ባደረገበት ቀን በባየርን ሙይንሽን የ3 ለ1 ሽንፈት ደርሶበት ወደ ፕሬሚየር ሊጉ የተመለሰው ቸልሲ ዳግም ሽንፈት አስተናግዷል ። በቅዳሜ ግጥሚያ ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ ሜዳ ኦልድትራፎርድ ያቀናው ቸልሲ ዳግም የ2 ለ1 ሽንፈት ደርሶበት ተመልሷል ። ለቡድኑ ተጨዋቾች እና ደጋፊዎች እጅግ የሚያበሳጭ አጋጣሚ ።
በሻምፒዮንስ ሊግ የቀናቸው ማንቸስተር ሲቲ እና አርሰናል ትናንት ያደረጉት ግጥሚያ በብዙዎች ዘንድ የሚጠበቅ ነበር ። አርሰናል አትሌቲክ ክለብን ማክሰኞ ዕለት በገዛ ሜዳው በሻምፒዮንስ ሊግ ግጥሚያ 2 ለ0 ድል አድርጎ ነበር የተመለሰው። ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ በኢትሐድ ስታዲየሙ ሊጋጠመው የመጣው ናፖሊን ሐሙስ ዕለት በሻምፒዮንስ ሊግ ያሸነፈው 2 ለ0 ነበር ። ማንቸስተር ሲቲ በፕሬሚየር ሊግ ትናንት በ9ኛው ደቂቃ በኧርሊንግ ኦላንድ ግብ አርሰናልን ሲመራ ቆይቶ ነበር ። የማታ ማታ ግን በ93ኛ ደቂቃ ላይ ጋብሪዬል ማርቲኔሊ ግብ በማስቆጠር አርሰናልን ከሽንፈት ታድጓል ።
ቡንደስሊጋ
በጀርመን ቡንደስሊጋ ሐምቡርግ ቅዳሜ ዕለት ታሪክ አስመዝግቧል ። ሐምቡርግ በቡንደስሊጋው ታሪክ ከ18 ዐመታት ወዲህ የመጀመሪያ ድሉን ተቀዳጅቷል ። ከስሩ አውግስቡርግ፤ ትናንት ከባዬር ሌቨርኩሰን ጋር አንድ እኩል የተለያየው ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን እና ሐይደንሐይምን አስከትሎ በ4 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በሐምቡርግ የሁለት ለአንድ ሽንፈት የደረሰበት ሐይደንሀይም የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ይገኛል ። ጊዜው ገና ቢሆንም፥ ወደመጣበት የታችኛው ቡንደስሊጋ ለመመለስ ዳር ዳርታ ።
መሪው ባዬርን ሙይንሽን ሆፈንሀይምን በሜዳው 4 ለ1 ጉድ ባደረገበት የቅዳሜው ግጥሚያ አጥቂው ሔሪ ኬን ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ሔትሪክ ሠርቷል፥ የመጨረሻዋ ግብ የሰርጌ ግናብሬ ናት ። ለሆፈንሀይም ቭላድሚር ኮውፋል ብቸኛውን ግብ አስቆጥሯል ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ትናንት ቮልፍስርግን 1 ለ0 አሸንፎ ነጥቡ 10 አድርሷል ። ከመሪው ባዬር ሙይንሽን የሚበለጠው በ2 ነጥብ ብቻ ነው ። ኮሎኝን 3 ለ1 ያሸነፈው ላይፕትሲሽ በዘጠኝ ነጥብ በሦስተኛነት ይከተላል ። ኮሎኝ በ7 ነጥብ በአራተኛ ደረጃ ላይ ሰፍሯል ። የሁለቱ ግጥሚያ የሦስተኛ ደረጃን ለመቆናጠጥ ብርቱ ፉክክር የታየበት ግጥሚያ በመሆኑ ጨዋታቸው በብዙዎች ዘንድ ሲጠበቅ ነበር ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ