1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 17 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ 

ሰኞ፣ መስከረም 17 2014

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ባልተጠበቀ ሁኔታ ቶትንሀም ሆትስፐርን ድል አድርጓል። መሪው ሊቨርፑል ከታችኛው ዲቪዚዮን በመጣ ቡድን ነጥብ ጥሏል። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ሔርታ ቤርሊን የግብ ጎተራ ሆኖ ተሸንፏል። ባየርን ሙይንሽን መሪነቱን እንደተቆናጠጠ ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቤርሊን ማራቶን በወንድም በሴትም ፉክክር ድል ቀንቷቸዋል።

Deutschland Berlin Marathon 2021  Gotytom Gebreslase
ምስል Annegret Hilse/REUTERS

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ አርሰናል ባልተጠበቀ ሁኔታ ቶትንሀም ሆትስፐርን ድል አድርጓል። መሪው ሊቨርፑል ከታችኛው ዲቪዚዮን በመጣ ቡድን ነጥብ ጥሏል። በጀርመን ቡንደስሊጋ፦ ሔርታ ቤርሊን የግብ ጎተራ ሆኖ ተሸንፏል። ባየርን ሙይንሽን መሪነቱን እንደተቆናጠጠ ነው። ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቤርሊን ማራቶን በወንድም በሴትም ፉክክር ድል ቀንቷቸዋል። በተለይ በሴቶች ፉክክር ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ደረጃን ጠቅልለው ወስደዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቀጣይ ግጥሚያው ልምምዱን ከወዲሁ ጀምሯል። አራት የጀርመን ቡድኖች ነገ እና ከነገ በስተያ ለሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ግጥሚያቸውን ያከናውናሉ። በከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያ አንቶኒ ጆሹዋ ያልጠበቀው ሽንፈት ገጥሞታል። አራት ቀበቶዎቹን ለዩክሬናዊው ባለድል አስረክቧል። በቁጭት ከመብሰክሰክ ግን ለዳግም ፍልሚያ ልምምዴን በፍጥነት እጀምራለሁ ሲልም ራሱን አጽናንቷል። በፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን 100ኛ ድልሉን አስመዝግቧል። 

አትሌቲክስ

በበርሊን ማራቶን ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በሴቶችም በወንዶችም አስደሳች ውጤት አስመዝግበዋል። ኢትዮጵያ በሴቶች ፉክክር ሙሉ ለሙሉ ድል ስትቀዳጅ፤ በወንዶች ፉክክር ደግሞ ኬንያዊ አትሌት በመሀል ጣልቃ በማስገባት ነበር አሸናፊነቱን የተቆጣጠረችው። ኢትዮጵያዊቷ ጎቲይቶም ገብረሥላሴ አንደኛ የወጣችው ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ09 ሰከንድ በማጠናቀቅ ነው። ሕይወት ገብረኪዳን በ2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ23 ሰከንድ ሁለተኛ ስትወጣ፤ ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሔለን ቶላ በ2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ የሦስተኛነት ደረጃውን ይዛለች። ኤዲዝ ቼሊሞን በመከተል ሹሬ ደምሴም የአምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቃለች።

ምስል ISSOUF SANOGO/AFP

በወንዶች ፉክክር ክብረወሰን ለመስበር ዓልሞ የነበረው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ሦስተኛ በወጣበት ውድድር የሀገሩ ልጅ አትሌት ጉያ አዶሎ አንደኛ ወጥቷል። ኬንያዊው ቤትዌል ዬጎን ሁለተኛ በመሆን አጠናቋል። ታዱ አባተ የ4ኛ ደረጃን ይዟል። በአጠቃላይ የትናንቱ የቤርሊን ማራቶን ኢትዮጵያውያን በወንድም በሴትም ኃያልነታቸውን ያስመሰከሩበት ፉክክር ነበር። በቶኪዮ ኦሎምፒክ ድል ርቆት ለነበረው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የትናንቱ ውጤት በርካቶችን ያስፈነደቀ ነበር።

እግር ኳስ

በሚቀጥለው ሳምንት ቅዳሜ ከደቡብ አፍሪቃ ቡድን ጋር የመልስ ጨዋታውን የሚያከናውነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ካለፈው ዐርብ ጀምሮ ለልምምድ ባሕር ዳር ይገኛል። ብሔራዊ ቡድኑ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ከመጋጠሙ ቀደም ብሎ አንድ የወዳጅነት ጨዋታ ሊያካሒድ ይችል እንደሆነም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ቀደም ሲል ለዶይቸ ቬለ የስፖርት ክፍል ተናግረዋል።  ቡድኑ አሁን የሚገኝበት ሁኔታ ጥሩ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምድቡ ውስጥ ከሚገኙት ጋና እና ዚምባብዌ ጋር ደግሞ የመልስ ጨዋታዎቹን ከአንድ ወር በኋላ ያከናውናል። ጋና እና ኢትዮጵያ ላለፉት ሦስት የአፍሪቃ እና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያዎች ባደረጓቸው ጨዋታዎች ሦስቱንም ያሸነፈው የጋና ብሔራዊ ቡድን ነው። በእርግጥ ቀደም ሲል 5 ለ0 ማሸነፍ ይችል የነበረው የጋና ቡድን ባለፈው የማጣሪያ ግጥሚያ ኢትዮጵያን ማሸነፍ የቻለው 1 ለ0 በሆነ ጠባብ ልዩነት ነው። የእግር ኳስ ውጤት በአንድ ጀንበር ሳይሆን በሒደት የሚገኝ መሆኑን የተናገሩት አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ሒደቱ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተውበታል።  

ምድቡን ደቡብ አፍሪቃ በ4 ነጥብ ይመራል። ተመሳሳይ 3 ነጥብ እና 1 የግብ ክፍያ ያላቸው የኢትዮጵያ እና የጋና ብሔራዊ ቡድኖች ይከተላሉ። 1 ነጥብ እና 1 የግብ እዳ ያለባት ዚምባብዌ የምድቡ መጨረሻ ላይ ትገኛለች። ዚምባብዌ የነገ ሁለት ሳምንት ጋናን በሜዳዋ ሐራሬ ብሔራዊ ስታዲየም ውስጥ ታስተናግዳለች።

ምስል AFP/Getty Images

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ክሪስታል ፓላስ ስድስተኛ ተስተካካይ ግጥሚያውን ዛሬ ማታ ከብራይተን ጋር ይጫወታል። ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ዎልቨርሐምፕተን ዋንደረርስ ሳውዝሐምተንን 1 ለ0 አሸንፏል። ቶትንሀም ሆትስፐር በአርሰናል የ3 ለ1 ሽንፈት ገጥሞታል። በዚህም መሰረት አርሰናል ከ13ኛ ወደ 10ኛ ከፍ ሲል ቶትንሀም ከ7ኛ ወደ 11ኛ ደረጃ አሽቆልቁሏል። በማንቸስተር ሲቲ የ1 ለ0 ሽንፈት የገጠመው ቸልሲ ከሊቨርፑል ጋር የነበረው ተመሳሳይ ነጥብ እና ግብ ክፍያ ተቀይሮ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። መሪነቱንም ሊቨርፑል በብቸንነት እንዲይዝ አስረክቧል። ሊቨርፑል በ14 ነጥብ መሪነቱን ቢይዝም ከታችኛው ዲቪዚዮን ከመጣው እና ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ብሬንትፎርድ ጋር ሦስት እኩል መውጣቱ ግን ደጋፊዎቹን አስደንግጧል። ምናልባትም ከተፎካካሪዎቹ በነጥብ በተወሰነ መራቅ የሚያስችለውን ዕድል አጥቷል። ሊቨርፑል ነገ ከፖርቹጋሉ ፖርቶ ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ ይጋጠማል።

ማንቸስተር ዩናይትድ እንደ ማንቸስተር ሲቲ፣እና ቸልሲ 13 ነጥብ ይዞ በግብ ክፍያ ልዩነት 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።  አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኤቨርተንም ነጥቡ 13 ነው። ማንቸስተር ዩናይትድ ከነገ በስትያ ከቪላሪያል ጋር ለሻምፒዮንስ ሊግ ይጋጠማል።

ቡንደስሊጋ

በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በተከናወኑ የቡንደስሊጋ ጨዋታዎች የላይፕትሲሽ እና ሔርታ ቤርሊን ግጥሚያ በርካታ ግቦች ተቆጥረውበታል። ላይፕትሲሽ ሔርታ ቤርሊንን 6 ለባዶ ነበር ያንኮታኮተው። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ የ1 ለ0 ሽንፈት ቀምሷል። ባየርን ሙይንሽን ከታችኛው ዲቪዚዮን ዘንድሮ ያደገው ግሮይተር ፊዩርትን 3 ለ0 አሸንፏል።  ትናንት በተደረጉ ጨዋታዎች ፍራይቡርግ አውግስቡርግን 3 ለ0 ሲያሸንፍ፤ ሽቱትጋርት እና ቦሁም ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ሆፈንሃይም ቮልፍስቡርግን 3 ለ1 አሸንፏል። ባየርን ሌቨርኩሰን ማይንስትን እንዲሁም ዑኒዮን ቤርሊን አርሜኒያ ቢሌፌልድን 1 ለ0 ድል አድርገዋል። ኮሎኝ ከፍራንክፉርት ጋር አንድ እኩል ነጥብ ተጋርተዋል።  

ምስል Heuberger/imago images

ሻምፒዮንስ ሊግ

አራት የጀርመን ቡድኖች ነገ እና ከነገ በስትያ የሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ሲግናል ኤዱና ፓርክ ስታዲየሙ ውስጥ ነገ ማታ የፖርቹጋሉ ስፖርቲንግ ሊዛቦንን ያስተናግዳል። በቀዳሚ ግጥሚያው ቦሩስያ ዶርትሙንድ የቱርኩ ቤሽክታሽ ኢስታንቡልን 2 ለ1 አሸንፏል።  ምድቡን የሆላንዱ አያክስ አምስተርዳም በግብ ልዩነት ይመራል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በግብ ክፍያ ተበልጦ የሁለተኛ ደጃን ይዟል። የመጀመሪያ ጨዋታውን የተሸነፈው ቤሽክታሽ ኢስታንቡል እና በአያክስ አምስተርዳም የ5 ለ1 አስደንጋጭ ሽንፈት የገጠመው ስፖርቲንግ ሊዛቦን ያለምንም ነጥብ በግብ እዳ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

ነገ ማታ በተመሳሳይ የጀርመኑ ላይፕትሲሽ ቡድን ሬድ ቡል አሬና ስታዲየሙ ውስጥ የቤልጂየሙ ክለብ ብሩዥን ይገጥማል። ከነገ በስትያ በሚደረጉ ሌሎች ጨዋታዎች ደግሞ የጀርመኑ ባየርን ሙይንሽን የዩክሬኑ ዲናሞ ኪዬቭን ይፋለማል። በመጀመሪያው ግጥሚያው ባየርን ሙይንሽን የስፔኑ ባርሴሎናን 3 ለ0 ድል አድርጎ ሦስት ነጥብ ማግኘት ችሏል። ረቡዕ ዕለት በሚከናወኑ የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ሌላኛው የጀርመን ቡድን ቮልፍስቡርግ ከስፔኑ ሴቪያ ጋር ይጫወታል።

ፎርሙላ አንድ

በሩስያ ግራንድ ፕሪ የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም ሌዊስ ሐሚልተን አሸናፊ ሆኗል። ዝናባማ በነበረው የሩስያ ፉክክር ያገነው ድሉም 100ኛ ሆኖ ተመዝግቦለታል። የሬድ ቡል አሽከርካሪው ማክስ ፈርሽታፐን በአለቀ ሰአት አጋጣሚ ቦርቋል። የሜርሴዲሱ አሽከርካሪ ሌዊስ ሐሚልተን አጀማመሩ ላይ ደካማ ነበር። ዘግየት ብሎ የተሽከርካሪዎቹን ጎማ በመቀየሩም አጋጣሚው ጠቅሞታል። የተሽከርካሪውን ሞተር ቀይሮ መጨረሻ ላይ ወደ ውድድሩ የገባው ማክስ ፈርሽታፐን ባለቀ ሰአት ሁለተኛ መውጣቱ እጅግ አስደስቶታል። በሩስያው ግራንድ ፕሪ ሽቅድምድም ከሌዊስ ሐሚልተን እና ማክስ ፈርሽታፐን ቀጥሎ የሦስተኛ ደረጃ የያዘው የፌራሪ አሽከርካሪው ካርሎስ ሳይንዝ ነው። እስካሁን በተደረጉ አጠቃላይ ውድድሮች፦ ሌዊስ ሐሚልተን 246.5 ነጥቦችን በመሰብሰብ ይመራል። ማክስ ፈርሽታፐን እጅግ በጠበበ የነጥብ ልዩነት በ244.5 ነጥብ ይከተላል።  ሌላኛው የመርሴዲስ አሽከርካሪ ቫለሪ ቦታስ 151 ነጥቦችን ሰብስቦ የሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የማክላረኑ ላንዶ ኖሪስ እና የሬድ ቡሉ ሠርጂዮ ፔሬስ በ139 እና 120 ነጥቦች የ4ኛ እና 5ኛ ደረጃን ይዘዋል።

ምስል ALEXANDER NEMENOV/AFP

ቡጢ

በዓለም የከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ዩክሬናዊው አሌክሳንደር ኡዚክ አንቶኒ ጆሹዋን ድል አድርጎ አራቱንም ቀበቶዎች ሰብስቦ ወስዷል። እንግሊዝ የቶትንሀም ሆትስፐር ስታዲየም ውስጥ 67ሺህ ታዳሚያን በተገኙበት ቅዳሜ ዕለት በተከናወነው ፍልሚያ ከ12 ዙር በኋላ ዩክሬናዊው አሸናፊ የሆነው በዳኞች ውሳኔ ነው። በዚህም መሠረት የዓለም ቡጢ ማኅበር (WBA) የዓለም አቀፍ ቡጢ ፌዴሬሽን (IBF) የዓለም ቡጢ ድርጅት (WBO) እንዲሁም የዓለም አቀፍ ቡጢ ድርጅት (IBO)ቀበቶዎችን አሸናፊ ኾኗል።

ቀድሞ የከባድ ቡጢ ፍልሚያው በአንቶኒ ጆሹዋ እና ታይሰን ፉሪ መካከል ይከናወናል በሚል ነበር ቀጠሮ የተያዘው። ሆኖም በከባድ ሚዛን ቡጢ ፍልሚያ ሽንፈት ገጥሞት የማያውቀው አሌክሳንደር ኡዚክ በዓለም ቡጢ ድርጅት (WBO)እንዲጫወት ግዴታ ስለተጣለበት የተደረገ ግጥሚያ ነበር። የ34 ዓመቱ ዩክሬናዊ በተለይ በውድድሩ የመጨረሻ 12ኛ ዙር ላይ አከታትሎ የሰነዘራቸው ምቶች አንቶኒ ጆሹዋ የቡጢ መድረኩ ተለጣጭ ገመዶችን ባይደገፍ ኖሮ በዝረራ ሊሸነፍም ይችል ነበር። አንቶኒ ጆሹዋ በተለይ ከ9ኝ ዙር በኋላ የቀኝ ዐይኑ ስር በደረሰበት እብጠት የተነሳ ማየት ከብዶት እንደነበረም ገልጧል።

ምስል Frank Augstein/AP/dpa/picture alliance

አሌክሳንደር ኡዚክ የቅዳሜ ምሽት የለንደን ድሉ ከ9 ዓመት በፊት ካገኘው የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ጋር የሚስተካከል አይደለም ብሏል። የ31 ዓመቱ እንግሊዛዊ ቡጢኛ አንቶኒ ጆሹዋ ሁለተኛ ሽንፈቱ ሆኖ በተመዘገበበት የቅዳሜው ግጥሚያ የአሌክሳንደር ኡዚክን ቡጢዎች መቋቋም ተስኖት ነበር።

ከአንቶኒ ጆሹዋ ጋር ለመጋጠም ቀደም ሲል ቀጠሮ ይዞ የነበረው ታይሰን ፉሪ በቅርቡ ከአሜሪካዊው የከባድ ሚዛን ቡጢኛ ዴዎንታይ ቪልደር ጋር ላስ ቬጋስ ሊጋጠም ቀጠሮ ተይዞለታል። ከዚያ ግጥሚያ በኋላ ከአንቶኒ ጆሹዋ ጋር ይኖረዋል ተብሎ የነበረው ፍልሚያ ግን በአንቶኒ ሽንፈት የተነሳ ተሰርዟል። አንቶኒ ጆሹዋ በአሌክሳንደር ኡዚክ በደረሰበት ሽንፈት እቤቱ ገብቶ እንደማይብሰከሰክ ይልቁንስ ልምምዱን በፍጥነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW