1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 18 ቀን፣ 2013 ዓ.ም ስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 18 2013

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለብሔራዊ ቡድኑ አዲስ አሰልጣኝ መሰየሙን ዛሬ ይፋ አድርጓል።  በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያል የሚባሉት ቡድኖች ያልተጠበቀ ሽንፈት አስተናግደዋል። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ሲቲ ከባድ ሽንፈት ገጥሞታል። ዛሬ ማታ በወሳኝ ግጥሚያው ሊቨርፑል ከአርሰናል ጋር ይፋለማል።

Äthiopien: Trainer der Fußballnationalmannschaft I Wubetu Abate
ምስል Omna Taddele/DW

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

አሰልጣኝ አብርሃም በብሔራዊ ቡድን ቆይታቸው መገባደዱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ በዶይቼ ቬሌ (DW) ተጠይቀው አሁን ምላሽ መስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው አስረድተዋል። የአሰልጣኝነት ውላቸው በወርሃ ሐምሌ 2012 ዓ.ም እንደተጠናቀቀ እና በዋሊያዎቹ አሰልጣኝነታቸው መቀጠል እንዳልቻሉም ቀደም ሲል ተገጧል።  

አዲሱ ተሿሚ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ብሔራዊ ቡድኑን ለአፍሪቃ ዋንጫ የማሳለፍ እና በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ረጅም ርቀት የመጓዝ ኃላፊነት ውላቸው ላይ ተቀምጧል። በወር ከታክስ የተጣራ 125,000 ብር እንደሚያገኙ የተገለፀው አሰልጣኙ ከሰበታ ከተማ ጋር ያላቸውን የአንድ ዓመት ቀሪ ውል በስምምነት ማፍረሳቸውን ገልፀዋል።

ዖምና ታደለ ዛሬ ያነጋገራቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የልጅነት ሕልማቸው በመሳካቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልጠው ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መኾናቸውን ዐሳውቀዋል።

«በቅድሚያ ለዚህ ታላቅ ኃላፊነት በመታጨቴ እና እንደማንኛውም አሰልጣኝ ከልጅነት ጅምሮ ስፈልገው ወደነበረው ቦታ ምንም እንኳን ባልፈለኩት እና ባልጠበቁት ሰዓት ቢሆንም ኃላፊነቱን የተረከብኩት ኃላፊነቱ ስለተሰጠኝ በጣም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል። የምችለውን ነገር በቆይታዬ የራሴን የሆነ አሻራ ለማሳረፍ ጥረት አደርጋለው።"

ኢትዮጵያ ቡናን ከ10 ዓመት በፊት የፕሪምየር ሊጉ አሸናፊ ያደረጉት አሰልጣኝ ውበቱ በአዳማ ከተማ፣ ደደቢት፣ ንግድ ባንክ፣ ሃዋሳ ከተማ እና ፋሲል ከነማ ክለቦችን አሰልጥነዋል። ድንበር ተሻግረውም የሱዳኑን አል አሃሊ ሸንዲ ክለብ ለተወሰኑ ግዜያት ማሰልጠን ችለዋል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪቃ ዋንጫ ማጣሪያ ኒጀርን በደርሶ መልስ የሚቀጥለው ወር የሚገጥም ይሆናል።

ምስል Omna Taddele/DW

በሌላ ተጨማሪ ዜና፦ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር እና የስፔን ላሊጋ የትብብር ስምምንተ መፈራረማቸውን ዐስታውቀዋል። ለኹለት ዓመት ይቆያል የተባለው ስምምነት በሰባት አበይት ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራት ያቀደ መኾኑ ተጠቊሟል። በስምምነቱ መሰረት ላሊጋ ለፕሪምየር ሊጉ በተቋማዊ አሠራር መዘምን፣ በታዳጊዎች ስልጠና፣ በአሰልጣኞች ስልጠና፣ የምስል እና ድምጽ ቅጂ መብት ሽያጭ እና የተቋማዊ መለያ (ብራንድ) እድገት ላይ እንዲሁም የቡድኖች ፕሮፌሽናል መኾን ላይ እገዛ ያደርጋል ተብሏል። ላሊጋ ምንም ዓይነት የገንዘብ ርዳታ ለፕሪምየር ሊጉ እንደማያቀርብ የታወቀ ሲሆን የማኅበራዊ ኃላፊነት መወጣት ላይ የሚሠሰሩ ሥራዎች በጋር እንደሚተገብሩ መታወቊን ኦምና የላከው አጠር ያለ ዘገባ ይጠቊማል።

የጀርመን ቡንደስሊጋ የኹለተኛ ዙር ግጥሚያ አስገራሚ ውጤቶችን አስተናግዷል። ቦሩስያ ዶርትሙንድ ያልተጠበቀ ሽንፈት ገጥሞታል። ባየር ሙይንሽን ከበርካታ ወራት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸንፏል፤ ለዚያውም በሰፋ የግብ ልዩነት።

ባለፈው የጨዋታ ዘመን እና ካቻምና እጅግ ደካማ ውጤት አስመዝግቦ ያጠናቀቀው አውግስቡርግ በቡንደስሊጋው የባየር ሙይንሽን ዋነኛ ተፎካካሪ የኾነው ቦሩስያ ዶርትሙንድ ጉድ አድርጎታል። 6,000 የአውግስቡርግ ደጋፊዎች በተገኙበት በተደረገው ግጥሚያ አውስቡርግ አመርቂ ድል አስመዝግቦ ደጋፊዎቹን አስፈንድቋል።

አውግስቡርግ ባለፉት ኹለት ጨዋታ ዘመኖችን ከመውረድ የተረፈው ለጥቂት ነበር። በኹለቱም ዓመት 32 እና 36 ነጥብ ይዞ በተመሳሳይ 15ኛ ኾኖ ነበር የጨረሰው። በዘንድሮ ውድድር ኹለቱንም ግጥሚያዎቹን አሸንፎ ለጊዜውም ቢኾን በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ ለመኾን በቅቶ ነበር። ይኼም በቡድኑ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ተብሎ ተመዝግቦለታል።

በቅዳሜው ግጥሚያ የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ኧርሊን ሃላንድ ጥሩ አቋም ላይ አልነበረም። የመጀመሪያ የግብ ሙከራውን እንኳን ያገኘው 90ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። እሱንም ቢኾን በአግባቡ አልተጠቀመበትም። የኧርሊንግ ሃላንድ ቀን አልነበረም ማለት ይቻላል። እንደውም በ31ኛው ደቂቃ ላይ ቢጫ ካርድ ዐይቶም ነበር።  ወጣቶቹ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ተጨዋቾች፦ እነ ሣንቾ፣ ጂዮቫኒ ሬይና እና ጁዴ ቤሊንግሃም ቡድናቸውን በዜሮ ከመውጣት መታደግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ማርኮ ሮይስ፣ ዩሊያን ብራንድትም ኾነ ራይነር የቀየሩት ነገር አልነበረም።

ምስል Eduard Martin/Jan Huebner/lmago lmages

ሌላኛው በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ከተደረጉ ግጥሚያዎች በርካቶችን ያስደመመው የባየር ሙይንሽን በሆፈንሃይም 4 ለ1 መሸነፉ ነበር። ቀደም ሲል የመጀመሪያ ዙር ግጥሚያውን ከኮልን ጋር ተጋጥሞ 3 ለ2 ያሸነፈው ሆፈንሃይም የባየር ሙይንሽን በተደጋጋሚ ጨዋታዎች ተዳክሞ ወደ ሜዳ መግባቱን በሚገባ ተጠቅሞበታል። ለዲተር ሐንሲ ፍሊክ በአጠቃላይ ሦስተኛ በዚህ የጨዋታ ዘመን ደግሞ አንደኛ ሽንፈታቸው ነው። ሆፈንሃይም ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎቹ ባይከሽፉበት ኖሮ ሽንፈቱ ከዚህም በላይ በሰፋ የግብ ልዩነት ይኾን ነበር።

ሽፒገል የተባለው ድረ-ገጽ ጋዜጣ የሆፈንሃይም አሰልጣኝ ሰባስቲያን ሆኔስን ዐወድሶ ጽፏል፦ «ሆኔስ ባየርን እንዴት ማናደድ እንደሚቻል ዐሳይተዋል» ሲል አስነብቧል። ሙይንሽኖች ሆፈንሃይም ውስጥ ሽንፈት ቀመሱም ሲል ርእሱን ጎላ አድርጎ ጽፏል።

አሰልጣኝ ሰባስቲያን ሆኔስ ባለፈው ዓመት ከ23 ዓመት በታች ካቻምና ደግሞ ከ19 ዓመት በታች የባየር ሙይንሽን ተጨዋቾችን አሰልጥነው ለውጤት አብቅተዋል። አምና ወደ ሦስተኛ ዲቪዚዮን ያደገውን የባየር ሙይንሽን ኹለተኛ ቡድን በጨዋታ ዘመኑ አንደኛ ኾኖ እንዲያጠናቅቅ አስችለዋል።

በእርግጥም የትናንቱ ግጥሚያ የሆፈንሃይሙ ወጣት አሰልጣኝ ባየር ሙይንሽንን ጠንቅቀው እንደሚያውቊት አመላካች ነበር። የባየር ሙይንሽንን ድክመት እንዴት መጠቀም እንደሚችሉም ዐሳይተዋል። በተለይ አማካዩን ጠበብ አድርጎ በመጫወት፤ ተጋጣሚያቸውን እያስጨነቊ (Gegen-Pressing) የባላጋራቸው ተጨዋቾች ኳስ እንዲያበላሹ ማድረግ ተሳክቶላቸዋል። በፈጣን አጨዋወትም ቡድናቸው የባየር ሙይንሽን የተከላካይ ክልል ላይ እንዲመላለሱ አድርገዋል። በርካታ ግብ ሊኾኑ የሚችሉ ሙከራዎችንም ማድረግ ተሳክቶላቸዋል።

ኹለት ግቦችን ያስቆጠረው የሆፈንሃይሙ አጥቂ አንድሬ ክራማሪች በባየር ሙይንሽን የግብ ክልል ላይ እንዳሻው ተምነሽንሿል። 2 ለ0 ሲመራ የነበረው ባየር ሙይንሽን ረፍት የወጣው በዮሹዋ ኪሚሽ ብቸኛ ግብ 2 ለ1 በመኾን ነበር። አንድሬ ክራማሪች በ5 ግብ ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ነው። የቬርደር ብሬመኑ ኒክላስ ፉይልክሩግ እና የባየር ሙይንሽኑ ሠርጌ ግናብሬ 3 ግብ በማስቆጠር የኹለተኛ ደረጃ ይዘዋል። 4ኛ አይንትራኅት ፍራንክፉርቱ አንድሬ ሲልቫ እና የላይፕሲሹ ኤሚል ፎርስቤርግ ናቸው፤ 2 ግብ አላቸው።

ምስል Marvin Ibo Güngör/GES/picture-alliance

ባየር ሙይንሽን ሳያርፍ ተደጋጋሚ ጨዋታዎችን ማድረጉ ጎድቶታል። የፊታችን ረቡዕ ምሽት ገና የጀርመን ሱፐር ካፕ የዋንጫ ግጥሚያ ይጠብቀዋል።  ለዋንጫ የሚፋለመውም ደግሞ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ነው።

ዙይድዶይቸ ሳይቱንግ ጋዜጣ ባየር ሙይንሽን በሚታወቅበት «Mia san Mia» ማለትም «እኛ እኛ ነን» በተሰኘው የአሸናፊነት መፈክሩ ላይ በመሳለቅ «Mia san müd» ብሎታል። «እኛ በድካም ተዳቀናል» እንደማለት ነው።  «ባየር ሙይንሽን ከሱፐር ካፕ ድሉ ሦስት ቀናት በኋላ ብቻ ሆፈናይም ውስጥ በ4 ለ1 አስደናቂ ሽንፈት ስቃይ ገጥሞታል» ሲል ጽፏል።

አማካዩ ኮረንቲን ቶሊሶ መሬት ላይ ወድቆ ከድካሙ ተመልሶ የሚነሳም አይመስልም ነበር። የቶሊሶን ቦታ ሌዮን ጎሬትስካ ሊሸፍነው ይችል ነበር። ግን በተለየ መልኩ እንዲያርፍ ተብሎ ተቀያሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ ነበር። አማካዩ ላይ ከወደኋላ ሊሰለፍ የሚችል ሌላ የባየር ሙይንሽን ተጨዋች መጥቀስ ይቻል ይኾን? አዎ፤ ቲያጎ አልካንትራን። ግን እሱም ቢኾን አሁን ለሊቨርፑል ነው የሚጫወተው። ምናልባት የባየር ሙይንሽን ደጋፊዎች ዛሬ ማታ ሊቨርፑል ከአርሰናል ጋር ሲጋጠም የቀድሞ አማካያቸው ቲያጎ አልካንትራን እያዩት በትዝታ ይብሰለሰሉም ይኾናል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ግጥሚያ የሊቨርፑል እና አርሰናል የዛሬ ጨዋታ በጉጉት ይጠበቃል።  የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ፦ አርሰናል ቡድናቸው ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል አስቀድመው ተናግረዋል። ሊቨርፑል አንፊልድ ሜዳው ላይ አርሰናልን በአንድ ሳምንት ለኹለት ጊዜያት ያስተናግዳል። የመጀመሪያው ግጥሚያ ለፕሬሚየር ሊግ ሲኾን፤ ኹለተኛው የሊግ ዋንጫ አራተኛ ዙር ፍልሚያ ነው። ውድድሩም ሐሙስ ዕለት ይደረጋል። የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ሊቨርፑል ከ30 ዓመታት ቆይታ በኋላ ዋንጫ በወሰደበት የባለፈው የጨዋታ ዘመን ሦስተኛ ሽንፈቱን እንዲቀምስ ማድረግ የቻለ ነው።  

ምስል picture-alliance/P. Noble

ላይስተር ሲቲ በትናንቱ ግጥሚያ ማንቸስተር ሲቲን እንዳይኾን አድርጎ 5 ለ2 አንኮታኲቷል። የላይስተር ሲቲው የቊርጥ ቀን ልጅ ጃሚ ቫርዲ ድንቅ ብቃቱን ዐሳይቷል። የ33 ዓመቱ እንግሊዛዊ አጥቂ ለላይስተር ሲቲ ኹለት ኳሶችን በፍጹም ቅጥት ምት አንድ በጨዋታ አስቆጥሯል። በዚህም የዛሬ አራት ዓመት የፕሬሚየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ የነበረው ላይስተር ሲቲ በታሩኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በሦስት ግጥሚያዎች ከፍተኛውን ነጥብ ማስመዝገብ ችለዋል።

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በአሰልጣኝነታቸው ዘመን ካደረጓቸው 686 ግጥሚያዎች አምስት ግብ ሲቆጠርባቸው የመጀመሪያው ኾኖ ተመዝግቧል። የቀድሞው የሴልቲክ እና ሊቨርፑል የአኹኑ የላይስተር ሲቲ አሰልጣኝ ብሬንዳን ሮጀርስ የቫርዲን አጠቃላይ ብቃት አድንቀዋል። ቡድናቸው መቶ በመቶ አቅሙን ማሳየቱንም ተናግረዋል። በሚኬል አርቴታ ቡድን እንደሚደመሙ የተናገሩት ጀርመናዊው የሊቨርፑል አሰልጣኝ ዬርገን ክሎፕ፦ «በተከላካዩ እና አጥቂው ክፍል ያለውን መመጣጠን መመልከት ትችላለህ። በጣም ጥሩ ነው። እውነቱን ለመናገር አርቴታ ወደ ቡንዱ ከመጡ ወዲህ አስደናቂ ሥራዎችን ሠርቷል» ብለዋል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዖምና ታደለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW