1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 20 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 20 2017

በዛሬው የስፖርት መሰናዶዋችን በተለይ ኢትዮጵያውያን አመርቂ ውጤት ስላስመዘገቡበት የቤርሊን የማራቶን የሩጫ ፉክክር ቃለ መጠይቅ ይኖረናል ። የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ እንዲሁም የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ቅኝትም አካተናል ።

Deutschland | Berliner Marathon 2024 | Milkesa Mengesha
ምስል Ebrahim Noroozi/AP/picture alliance

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በዛሬው የስፖርት መሰናዶዋችን በተለይ ኢትዮጵያውያን አመርቂ ውጤት ስላስመዘገቡበት የቤርሊን የማራቶን የሩጫ ፉክክር ቃለ መጠይቅ ይኖረናል የእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ እንዲሁም የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ቅኝትም አካተናል

አትሌቲክስ

በቤርሊን ማራቶን የ50ኛ ዐመት ልዩ የሩጫ ፉክክር  ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ተቀዳጅተዋል ። እሁድ መስከረም 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በተከናወነው የቤርሊን ማራቶን ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ተከታትለው በመግባት መድረኩን ተቆጣጥረዋል ። አትሌት ትዕግስት ከተማ አሸናፊ በሆነችበት ውድድር፦ አትሌት መስተዋት ፍቅር፤ ቦሰና ሙላቴ እና አበሩ አያና ተከታትለው በመግባት ዓለምን አስደምመዋል ።  በወንዶች ፉክክርም አትሌት ሚልኬሳ መንገሻ ሲያሸንፍ፤ ሃይማኖት ዓለውም የሦስተኛ ደረጃ አግኝቷል። 

የአየር ጠባዩ እና የመሮጫ መንገዱ ተስማሚ መሆኑ ቀድሞ ቢታወቅም፤ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በቤርሊን ማራቶን እንዲህ ያለ እጅግ አስደሳች ውጤት ያስመዘግባሉ ተብሎ ግን ተጠብቆ ይሆን? የኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 የኢትዮ ስፖርት ዋና አዘጋጅ እና አቅራቢ ምሥግናው ታደሰ፦ በተለይ በብሔራዊ ቡድን ያልታፉ አዳዲስ ተወዳዳሪዎች ያሳዩት ትጋት ነው ብሏል ።

በኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያ አጠቃላይ የአትሌቲክስ ውጤቶቿ ከዓመታት ወዲህ ዝቅ ቢልም፦ በማራቶን ውድድሮች ግን ዳግም ብቅ ብላለች ። በፓሪስ ኦሎምፒክ በሴቶች ፉክክር የአንደኛነቱ ደረጃ ወደ ኢትዮጵያ ባይመጣም፤ በወንዶች የማራቶን ፉክክር ግን በአትሌት ታምራት ቶላ የ2:06:26 ጊዜ አዲስ ክብረ ወሰን ኢትዮጵያ ድል አድርጋለች ። ቀደም ብሎ በነበረው የቶኪዮ ኦሎምፒክ በወንዶች ጭራሽ ከቁጥር ሳንገባ በሴቶች ማራቶን በአትሌት ሮዛ ደረጀ ቢያንስ የአራተኛ ደረጃ አግኝተን ነበር ።

የበርሊንን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች በሚደረጉ የማራቶን ሩጫ ፉክክሮች ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መድረኩን ስትቆጣጠር በኦሎምፒክ አስቸጋሪ የሆነው ለምንድን ነው? ምሥጋናው፦ ዋነኛ ችግሩ ለወጣቶች እና አዳዲስ አትሌቶች ዕድል አለመሰጠቱ፤ የቡድን እና የትውቅ ሥራ መኖሩ፤ አትሌቶች ውድድሩ እስኪቃረብ ድረስ በተለያዩ አሰልጣኞች መሰልጠናቸው እና በአንድ አሰልጣኝ እንደ ቀድሞው ተሰባስበው አለመሰልጠናቸው ከችግሮቹ መካከልዋነኞቹ ናቸው ብሏል ። የመስከረም 13 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሻምፒዮንስ ሊግ

የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስተያ ይኖራሉ ። በነገው ዕለት የጀርመኖቹ ቦሩስያ ዶርትሙንድ፣ ባዬር ሌቨርኩሰን እና ሽቱትጋር ይፋለማሉ ። ከዋነኞቹ ቡድኖች መካከልም፦ ማንቸስተር ሲቲ፤ አርሰናል፤ ፓሪ ሳንጃርሞ፤ ኤሲ ሚላን፤ ኢንተር ሚላን፤  ቦሩስያ ዶርትሙንድ እንዲሁም ባርሴሎና የሚጫወቱት በነገው ዕለት ነው ። 

የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ፦ ዘንድሮ ማን ይወስደው ይሆን?ምስል Gregorio Borgia/AP/picture-alliance

በበነጋታው ረቡዕ ከሚፋለሙት ዋነኞቹ ቡድኖች መካከል ደግሞ፦ እነ ሊቨርፑል፤ ጁቬንቱስ፤ ላይፕትሲ፤ ሪያል ማድሪድ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ባዬርን ሙይንሽን ይገኙበታል ።

የአውሮጳ ሊግ ሁለተኛ ዙር 18 ጨዋታዎች ደግሞ ሐሙስ ዕለት ይከናወናሉ ። ማንቸስተር ዩናይትድ ከፖርቶ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ይጠበቃል ። የመጀመሪያው ዙር ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እና ሐሙስ ተከናውነዋል ።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ መጨረሻ ግጥሚያዎች፦ ማንቸስተር ዩናይትድ ትናንት በሜዳው ዖልድ ትራፎርድ ስታዲየም በደጋፊዎቹ ፊት በቶትንሀም የ3 ለ0 ሽንፈት አስተናግዷል ። 42ኛው ደቂቃ ላይ የብሩኖ ፈርንናንዴሽ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበት በእርግጥም ቡድኑን እጅግ ነው የጎዳው ። አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሐግ ከቡድኑ ጋር ያላቸው የወደፊት ዕጣ ሰሞኑን እጅግ መነጋገሪያ ሁኗል ። የማንቸስተር ዩናይትድ ምንጮች ግን ለዜና አውታሮች እንደተናገሩት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ቡድኑ ዋነኛ ትኩረቱ ሐሙስ ዕለት በአውሮጳ ሊግ ከፖርቶ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ ነው ብለዋል ።  ማንቸስተር ዩናይትድ ሐሙስ በኤስታዲዮ ዶ ድራጋዎ ስታዲየም ፖርቶን ይገጥማል ። በፕሬሚየር ሊግ ተደጋጋሚ ሽንፈት በ7 ነጥብ ብቻ ተወስኖ 12ኛ ደረጃ ላይ ለሚገኘው ማንቸስተር ዩናይትድ በእርግጥም የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያዎቹ ወሳኝ ናቸው ። 

ባለፈው የፕሬሚየr eሊግ ዋንጫ ባለድሉ ማንቸስተር ሲቲ ፦ ዘንድሮስ ይሳካለት ይሆን?ምስል Molly Darlington/REUTERS

ቅዳሜ ዕለት አርሰናል ሁለት እኩል ከነበረበት ሁኔታ ባለቀ ሰአትም ያደረገው ፍልሚያ ማንነቱን ያሳየበት ነው ሲሉ አሰልጣኙ ተናግረዋል።  ከላይስተር ሲቲ ጋር በነበረው ግጥሚያ አርሰናል መደበኛው ዘጠና ደቂቃ ተጠናቆ በባከነ ጭማሪው አራተኛ እና ዘጠነኛ ደቂቃዎች ላይ በተከታታይ ባስቆጠራቸው ሁለት ተጨማሪ ግቦች 4 ለ2 ማሸነፍ ችሏል ። አርሰናል  በሻምፒዮንስ ሊግ ከፈረንሳዩ ፓሪ ሳንጃርሞ ጋር ነገ ለሚኖረው ግጥሚያም በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ተናግረዋል። የጳጉሜ 4 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ዎልቭስን በሜዳው 2 ለ1 አሸንፎ የተመለሰው ሊቨርፑል የደረጃ ሰንጠረዡ መሪነትን ከማንቸስተር ሲቲ ተረክቧል ። ማንቸስተር ሲቲ ኒውካስልን ሊገጥም ሄዶ በአንድ እኩል ውጤት ነጥብ ተጋርቷል ። ከመሪው ሊቨርፑልም በአንድ ነጥብ ተበልጦ እንደተከታዩ አርሰናል 14 ነጥብ ሰብስቧል ። ስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም ውስጥ ብራይተንን 4 ለ2 ድል ያደረገው ቸልሲ በ13 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።

ሊቨርፑል እና አርሰናል በካራባዎ ዋንጫ ግጥሚያ ረቡዕ ዕለት ተጋጣሚዎቻቸውን በተመሳሳይ 5 ለ1 አሰናብተዋል።   ዛሬ ማታ በርመስ ከሳውዝሐምፕተን ጋር ተስተካካይ ስድስተኛ ጨዋታውን ያደርጋል። 

የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያ በከፊል፦ ሳንክት ፓውሊ እና ፍራይቡርግምስል Alex Grimm/Getty Images

ቡንደስ ሊጋ

ትናንት እና ከትናንት በስትያ በነበሩ የቡንደስ ሊጋ ግጥሚያዎች፦ በ13 ነጥብ  የደረጃ ሰንጠረዡን የሚመራው ባየር ሙይንሽን በ10 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው ባዬር ሌቨርኩሰን ጋር አንድ እኩል ተለያይቷል ። 12 ነጥብ ሰብስቦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሰፈረው አይንትራኅት ፍራንክፉርት ሆልሽታይን ኪዬልን በገዛ ሜዳው 4 ለ2 ጉድ አድርጓል ።  ላይፕትሲሽ አውግስቡርግን ቅዳሜ ዕለት 4 ለ0 ድባቅ መትቶ ነጥቡን 11 በማድረስ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ።  ቦሩስያ ዶርትሙንድ 10 ነጥብ አለው ። ቦሁምን ዐርብ ዕለት 4 ለ2 አሸንፏል ። 

ሆፈንሀይም በ3፤ ቦሁም እና ሆልሽታይን ኪዬል በአንድ አንድ ነጥብ ከ16ኛ እስከ 18ኛ ወራጅ ቃጣና ውስጥ ሰፍረዋል ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW