1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም የትኩረት በአፍሪካ ዝግጅት

ቅዳሜ፣ መስከረም 24 2018

በጆሴፍ ካቢላ ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ እንደሚፈጥር ግልጽ ነው » ብለዋል ። በተጨማሪም አገሪቱ ቀደም ሲል ወደነበረችበት የትርምስ አዙሪት ልትዘፍቅ እንደምትችልም ያስጠነቅቃሉ።

የማሳይ ጎሳ አባላት
የማሳይ ጎሳ አባላትምስል፦ Marco Simoncelli/DW

የመስከረም 24 ቀን 2018 ዓ.ም ትኩረት በአፍካ

This browser does not support the audio element.

የካቢላ የፍርድ ሂደትና መዘዙ

በአለፈው ማክሰኞ የኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ወታደራዊ ፍርድ ቤት የቀድሞው የሐገሪቱ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸውን በመግለፅ የሞት ፍርድ ውሳኔ አስተላልፏል። የቀድሞው ፕረዚደንት ጆሴፍ ካቢላ የተከሰሱት  በአገር ክህደት፣ ጳታዊ ጥቃት፣ ግርፋትና በጦር  ወንጀል በዋና ወንጀል ፈፃሚነት፤ በድርጊቱ በመተባበርና በመመሳጠር የሚል ዶሴ ተከፍቶባቸው ጉዳዩን በሌሉበት ሲመለከት የነበረው ወታደራዊ ፍርድቤት በሞት እንዲቀጡ ፈርዶባቸዋል።  ፍርድቤቱ ካቢላ ካሉበት ታድነው በእስር እንዲመጡና የሞት ፍርዱ እንዲፈጸምም ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በእንግሊዘኛ ምህጻሩ  PPRD የተባለው በጆሴፍ ካቢላ የተመሰረተው ፓርቲ የፍርድ ውሳኔውን ለመቃወም የቀደመው የለም። በፍርድቤቱ የተላላፈው ፍርድ «ፖለቲካዊ» ሲል አጣጥሎታል። በመሆኑም ይህ የፍርድ ውሳኔ በቋፍ ላይ ያለውን የኮንጎን አለመረጋጋት ያሰጋ ይሁን?
የካቢላ የሞት ፍርድ ውሳኔና ያሳደረው ስጋት
በቀድሞው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ  ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ላይ  የተላለፈው የሞት ፍርድ በአገሪቱ መረጋጋት ላይ ከፍተኛ ስጋትን አሳድሯል ። የሞት ፍርድ ውሳኔውን ተከትሎ አንዳንድ የቀድሞው ፕረዚደንት ጆሴፍ ካቢላ ደጋፊዎች ውሳኔውን  አሁን በስልጣን ላይ ያለው ገዢ ፓርቲ ባደረገው የፖለቲካ ግፊት እንደተወሰነና ሰላምን ለማስፈን የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረትን ሊያቀጭጨው እንደሚችል በአጽንኦት ይናገራሉ። 
የጆሴፍ ካቢላ ደጋፊ የሆኑት ፖለቲከኛ ሮጀር ሚዊኒሂየር ለዶይቸቨለ የእንግሊዝኛ ቋንቋ አገልግሎት በሰጡት ቃለ ምልልስ ወታደራዊ ፍርድቤቱ በጆሴፍ ካቢላ ላይ ያሳለፈው የሞት ፍርድ በጣም አሳስቦናል ብለዋል። 

«በጆሴፍ ካቢላ ላይ  በወታደራዊ ፍርድ ቤት የተላለፈባቸውን ብይን በከፍተኛ ስጋት እንመለከተዋለን። መንግስታችን በአሁኑ ጊዜ በኪንሻሳ እየተወሰዱ ያሉ ጠቃሚ ውሳኔዎች የሚያስከትለውን መዘዝ እያጤነ ባለመሆኑ አዝነናል። ይህ ለሀገሪቱ የፖለቲካ እና የጸጥታ ችግር ሰላማዊ መፍትሄ የማፈላለግ ሂደቱን ሊያቆም ይችላል።»
ሚዊኒሂየር አክለውም ውሳኔው በምሥራቅ ኮንጎ የተፈጠረውን ቀውስ ለመፍታት የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ያደናቅፋል ብለዋል ። በኪንሻሳ በአሁኑ ጊዜ እየተወሰዱ ያሉት ከባድ ውሳኔዎች የሚያስከትሉትን ውጤት መንግሥታችን እየመዘነ አለመሆኑ በጣም ያሳዝነናል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
ወታደራዊ ፍርድቤቱ በካቢላ ላይ ካስተለለፈው የሞት ፍርድ በተጨማሪ በመንግሥት እና  የሰሜን እና የደቡብ ኪቩ ግዛቶች ለደረሰው ጉዳት የ33 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፍሉ ወስኗል።
ፍርድቤቱ የኤም 23 ታጣቂዎችን በመደገፍም ወንጅሏል። የወቅቱ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ትሺሴኬዲ ካቢላን የታጣቂ ቡድኑን ዋና ደጋፊ ናቸው በማለት በይፋ ወቅሰዋቸው ነበረ። ፍርድቤቱ ያጸናውም ይህንኑ ወቀሳ ነው። ምንም እንኳን ጆሱፍ ካቢላ ውንጀላውን ባይቀበሉትም። 
የፖለቲካ ተሃድሶ
በእንግሊዘኛ ምህጻሩ  PPRD የተባለው በጆሴፍ ካቢላ የተመሰረተው ፓርቲ  ዋና ፀሐፊ ራማዛኒ ሻዳሪ መንግስትን ተወቃሽ ያደርጋሉ። የፍርድ ውሳኔውን «ፖለቲካዊ» ሲሉ አጣጥለውታል። በአምባገነን ገዢ የተካሄደ የይስሙላ ይፍርድ ሂደት መሆኑን በማከል።

የቀድሞው የዴሞክራቲክ ኮንጎ ፕረዚደንት ጆሴፍ ካቢላምስል፦ Jospin Mwisha/AFP

«ይህ ጀብደኛ የዳኝነት ውሳኔ ነው። ለዚህም ነው እና እንደ የፖለቲካ ጉዳይ አድርገን የገለፅነው።  ይህ በአምባገነን መንግስት ተቋማት የታወጀ የይስሙላ የፍርድ ሂደት ነው። በመሆኑም ይህ ለኛ  አያስደንቀንም፤ ምክንያቱም ሁሉም ነገር በፖለቲካ ተዋረድ ተወስኗል። ዛሬ በየይስሙላ የስልጣን ተዋረድ ውሳኔውን ወስኗል፣ ቀን፣ ቁጥር፣ ማህተም እና ፊርማም ጨምሯል።
ይህ አያስደንቀንም። ምንም ያልተለመደ ነገር አይደለም። ሁሉም ነገር አስቀድሞ የታቀደ ነበር።
ለኛ ይህ አምባገነን መንግስት፤ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ የሆነውን ጠቃሚ የፖለቲካ ተዋናይን ለማስወገድ እና ለማስወገድ ብቻ ያለው ግልጽ ፍላጎት ማሳያ ነው።»

ሻዳሪ አክለውም ፍርድ ቤቱ ውሳኔ  የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን በሰፊው የማጥቃት ዘመቻ  አንዱ ክፍል ነው ብለዋል። በዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ ከምንጊዜውም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን አንድ ወሳኝ የፖለቲካ ተዋናይ ለማስወገድ የተከናወነ አምባገነናዊ ድርጊት ነው ይላሉ።

ልተናል ጀነራል ሙቶምቦ ካታላይ የወታደራዊ ፍርድቤቱ ውሳኔ ሲያነቡምስል፦ Samy Ntumba Shambuyi/AP Photo/picture alliance


ተጠያቂነትን ለማምጣት የቀረበ ጥሪ

ይሁን እንጂ እንደ ሶዚ ኪሱኪ ያሉ አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የአገዛዙን ውሳኔ ይደግፋሉ። «እኛ የኮንጎ ተወላጆች የጋራ ምኞቻትችን ካቢላ ለፍርድ ቀርቦ ማየት ነው» ብለዋል። ምክንያቱም አሉ፤ ምክንያቱም ካቢላ ሰልችቶናል፤ ሰላማዊ ሰዎችን ጨፍጭፏል፤ የኤም 23 ታጣቂዎችንም ይደግፋል በማለትም ያክላሉ።
 «ለእኔ ይህ ክስተት ትክክለኛ ነገር ነው። ምክንያቱም የወቅቱ የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት እንኳን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ፍትህ የለም ብለው ተናግረዋል። ነገር ግን እንደ ኮንጎዎች የጋራ ምኞታችን ካቢላ ጥፋተኛ ነው ብለን እናስባለን።  ከ 2014 ጀምሮ  በሐገሪቱ  ውስጥ በሲቪሎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ ዋና መሪ ተዋናይ ነበር።  በአሁኑ ጊዜ በ M23 የዓመፅ ድርጊት ውስጥ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ ነው። እናም ይህ ጥፋተኛ ነው ብዬ ነው የማስበው»
ይሁንና ኪሱኪ የፍርድ ውሳኔው ተፈጻሚነትን አብዝተው ይጠራጠራሉ። በሐገሪቱ የፍትሕ ሥርዓቱ የተዳከመ እንደሆነ በመግለጽ። የፖለቲካ ተንታኝ ቦብ ካባምባም እንደ ኪሱኪ ሁላ የት እንዳሉ የማይታወቁት የቀድሞው የኮንጎ ፕረዚደንት ጆሴፍ ካቢላ ላይ  የተላለፈውየሞት ፍርድተፈጻሚ ሊሆን አይችልም ይላሉ።

« ጆሴፍ ካቢላ ካሉበት ታድነው እንዲታሰሩና የተፈረደባቸው የሞት ፍርድ ተፈጻሚ እንዲሆን ወታደራዊ ፍርድቤቱ ቢፈርድም በሌሎች የአፍሪካ አምባገነን መሪዎች እንደተስተዋለው ሁሉ ተፈጻሚ ይሆናል ብዬ አላምንም። »
ካቢላ ባለፈው ግንቦት ወር በምስራቃዊ ኮንጎ ውስጥ ሰላም ለማስፈን በተደረገ ስብሰባ  ለአጭር ጊዜ ታይተው ነበር። ከዛ ወዲህ ግን ያሉበት ቦታ በዕርግጠኝነት አይታወቅም። በመሆኑም ይህን የሞት ፍርድ ቅጣት ተፈጻሚነት በተመለከተ ብዙ ዎች ይጠራጠራሉ።     
ለረጅም ጊዜ የዘለቀው ንትርክ ውጤት
የስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል አባል የሆኑት ኤምቪምባ ፔዞ ዲዞል ለዶይቸቨለ  እንደገለጹት የፍርድ ሂደቱ  በካቢላና በወቅቱ ፕሬዚዳንት ትሺሴኬዲ መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ፉክክር ከፍተኛ  ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያመለክት ነው ብለዋል።  ፕሬዚዳንት ትሺሴኬዲ የኮንጎ መሪ ከሆኑበት ጊዜ ጀምሮ የተጀመረው ግጭት መቋጫ የሌለው ነው በማለትም አክለዋል። 
ዲዞለ  የፍርድ ሂደቱ ሰፋ ያለ አንድምታ እንዳለውም አስጠንቅቋል። «ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ  ለረጅም ጊዜ በሽግግር ላይ የነበረች አገር ነች ። የፍርድ ውሳኔው ለገዥው ፓርቲ ከፍተኛ መዘዝ አለው ። በጆሴፍ ካቢላ ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ  እንደሚፈጥር ግልጽ ነው » ብለዋል ። በተጨማሪም አገሪቱ ቀደም ሲል ወደነበረችበት የትርምስ አዙሪት ልትዘፍቅ እንደምትችልም ያስጠነቅቃሉ። 

የማሳይ ጎሳ አባላትምስል፦ Therin Weise/imageBROKER/picture alliance

የታንዛኒያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራና የማሳዮች ማፈናቀል

በደቡብ ኬንያና በሰሜናዊ ታንዛኒያ የሚገኙ የማሳይ ጎሳ አባላት ለረዥም ዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ የመጣው የአርብቶ አደርነት ተግባራት ያከናውናሉ። እነዚህ አርብቶ አደሮች ከቦታ ወደ ቦታ በመንቀሳቀስ ከብቶቻቸውን ሳር ያስግጣሉ። ይሁንና በየጊዜው ከአስፈጻሚ አካላት የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥማቸው ይናገራሉ። ከሚያጋጥሙአችው ችግሮች መካከል አስገዳጅ ሰፈራ፣ ለብሔራዊ ፓርክ ተብለው በተከለሉ አካቢዎች ከብቶቻቸውን ሳር ሲያስግጡ በሚገኙበት ጊዜ በተለይም በታንዛንያ የሚገኙ የማሳይ ጎሳ አባላት በሐገሪቱ የዱር እንስሳት አስተዳደር ባለስልጣን ከብቶቻቸውን መውረስ፣ ሕጋዊ ደረሰኝ የማይቆረጥለት የቅጣት ክፍያ ማስከፈልና ሌሎች ሕገወጥ ተግባራት እንደሚፈጸምባቸው ለማወቅ ተችሏል። 
በሰሜን ታንዛንያ የሚኖር የ37 ዓመቱ የማሳይ ጎሳ አባል የሆነው ናሲካር ዳኡዲ በመንግስት አካላት የሚፈጸምባቸውን በደል ያንገሸገሻቸው ይመስላል። ናሲካር ለዶይቸቨለ የእንግሊዝኛ አገልግሎት በሰጠው አስተያየት «ከብቶቻችን ይወርሱብናል፤ እናቶችና ሕጻናትን ያለወተት እንዲቀሩና እንዲራቡ እያደረጉ ነው» ሲሉ በምሬት ይገልጻሉ።
«ለእንስሶቻችን የሚግጡበት ቦታ አሳጥተውናል። በፓርኮች አካባቢ ሳር አስግጣችኋል በማለት ከብቶቻችንን ይወርሳሉ። በመሆኑም  ወተት ስለሌለን  እናቶችና ሕጻናት በረሃብ እተጠቁ ነው። ይህ መሬት ከብቶቻችን ሳር የሚግጡበት ነው።  ያለዚህ ምድር መኖር አንችልም። የምንጠይቀው በምድራችን ላይ በሰላም ለመኖር ብቻ ነው»
ሂዩማን ራይትስ ዎች እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2024  ባወጣው ሪፖርት የታንዛኒያ መንግስት በሰሜን የሐገሪቱ ክፍል  በሚገኘው የኔጎንጎሮ የአካባቢ ጥበቃ ሥፍራ፤ የማሳይ ጎሳ አርብቶ አደሮች  ከቅድመ አያቶቻቸው ጀምረው ይኖሩበት ከነበረው ወደ ሌላ ቦታ አዛውሮ ለማስፈር የያዘው  እቅድ ከባድ መዘዝ እንዳለው አሳስቦ ነበር።  
የታንዛንያ ባለስልጣናት በአካባቢው የሰፈሩት የማሳይ አርብቶ አደሮች እና የከብቶቻቸው ቁጥር እያደገ በመምጣቱ አካባቢው ለመራቆቱ በምክንያትነት ይጠቅሳሉ። የማሳይ ጎሳ አባላቱን ግን ይህን ውንጀላ « ሐሰት» ሲሉ ያጣጥሉታል። እንዲያም ሲል የአካባቢ ጥበቃን ሰበብ በማድረግ  በአካባቢው የእኛን ህልውና ለማጥፋት የተቀነባበረ ሴራ ነው በማለትም በመንግስት ባለስልጣናት የሚቀርብባቸውን ውንጀላ አይቀበሉም።

የማሳይ ጎሳ አባላት በባሕላዊ ጭፈራ ላይምስል፦ Luis Tato/AFP/Getty Images


በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ሰፈራ
በመቶዎች የሚቆጠሩ የማአሳይ አርብቶ አደሮች  በነጎሮጎሮ ከተማ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከነሐሴ ከ18, 2024 ጀምሮ ለሦስት ቀናት ተሰባስበው የመንግስትን ድርጊት በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውመዋል። 
«ይህች ምድር የእኛ ናት ። የመሬቱ የንብረት ባለቤትነት የተነጠቅነው ሕገወጥ በሆነ መንገድ ነው ።»  የሚሉት የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጆሴፍ ኦሌጋንጋይ ናቸው። የሰብአዊ መብት ተሟጓቹ በሺዎች ለሚቆጠሩ የማሳይ ጎሳ አባላድ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው። 

«ይህ መሬት የእኛ ነው። የመሬቱ የንብረት ባለቤትነት የተነጠቅነው ሕገወጥ በሆነ መንገድ ነው። ሕጋዊ አሰራርን ተከትሎ የተወሰደ አደለም። ተግባሩ አገር በቀል አደለም፤ ከሌላ አገር የተጫነን አሰራር ነው። ይህ በታንዛንያ ብቻ አደለም፤ በሌሎች የአፍሪካ ሐገሮችም ከቅኝ ግዛት ጊዜ ጀምሮ የሚያጋጥም ሕገወጥ ተግባር ነው። እርግጥ ነው የአካባቢ ጥበቃ ችግር አለብን፤ ይህ በጣም አሳሳቢ ነገር ነው። የአካባቢ ጥበቃ በጣም አስፈላጊ ነው። ሰዎችን በማፈናቀል መሆን የለበትም»  
ይህየታንዛንያ የማሳይ ጎሳ አባላት ያሉበት አካባቢ በቱሪዝም ዘርፍ ለረዥም ዘመናት በየአመቱ በአማካይ 1.85 ቢልዮን ዶላር ለአገሪቱ ገቢ እንደሚያስገኝ ከመንግስት የተገኘ መረጃ ያመላክታል። ይሁንና የሐገሪቱ ባለስልጣናት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር ከ2022 ጀምሮ «በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ» ያሉት ሰፈራ እያከናወኑ ነው። በዚሁም መሰረት 1,500 የሚሆኑ የማሳይ ጎሳ አርብቶ አደሮች ከአካባቢ ጥበቃ ስፍራው፤ ትምህርት ቤቶችና ክሊኒክ ወደተገነባባት እና 700 ኪሎምትር ርቃ ወደምትገኘው ሞሴመራ ወደተባለች  አካባቢ እንዲዛወሩ አድርጓል። መንግስት ይህን ድርጊት «በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ» ቢለውም  የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ግን ይህ የሰፈራ ፕሮግራም የማሳዮች የሰብአዊ መብትን ይጥሳል በማለት በጥብቅ ያወግዙታል። 
የማሕበረሰቡ አባላትም የሰፈራ ፕሮግራሙ አይደግፉትም። አዲስ የሰፈሩበት አካባቢ በቂ የግጦሽ መሬት ስለሌለው ከብቶቻችን እየተራቡብን ነው። ከሌሎች ጎሳዎች ጥቃት እየተፈጸመብን ስለሆነ የደህንነት ስጋት አለብን ሲሉ ያማርራሉ። አንዲት የማሕበረሰቡ አባል የሆኑት እናት  የአካባቢው ባለስልጣናት ወደ ሰፈራ እንድሄዱ ጠይቀዋቸው ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የመኖሪያ ጎጆአቸውን እንዳቃጠሉባቸው ለዶይቸቨለ ተናግረዋል። ሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ደግሞ አዲሱ የሰፈራ ቦታ ሰዎች የሌሉበት ነጻ ቦታ ነው ተብሎ ቢነገረንም በርካታ ቀደምት ነዋሪዎች ያሉበትና በቂ የግጦሽ መሬት የሌለው መሆኑን ገልጸዋል። 
የሰፈራ ፕሮግራሙ ሲጀመር የጸጥታ ሐይሎች መጥተው በሐይል ወደ አዲሱ የሰፈራ ቦታ በጉልበት እንደወሰዷቸውና በዚህ ጊዜ በተፈጠረ ግርግር 1 ሰው ሲሞት በርካቶች የደረሱበት እንዳልታወቀ መረጃዎች ያመለክታሉ። በመሆኑም የማሳይ ጎሳ አባላትን የአካባቢ ጥበቃን ሰበብ ተደርጎ የሚደረገውን አስገዳጅ ሰፈራ በሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞ እየደረሰበት ይገኛል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW