1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 28 ቀን 2016 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

ሰኞ፣ መስከረም 28 2016

ትናንት እሁድ የአሜሪካዋ ቺካጎ ያስተናገደችው የማራቶን የሩጫ ውድድር በወንዶች አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ተመዝግቦበታል። በሴቶች ምድብ በተካሄደው ውድድር የተመዘገበው ሰዓትም የምንጊዜም ሁለተኛ ፈጣን ፣ የቦታው እና የአውሮጳ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። በእግር ኳስ የአምና ሻምፒዮኑ ማንችስተር ሲቲ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ሽንፈት ደርሶበታል

USA Chigaco | Marathon - Weltrekord - Gewinner - Kelvin Kiptum
ምስል KAMIL KRZACZYNSKI/AFP/Getty Images

የሰኞ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት

This browser does not support the audio element.


ትናንት እሁድ የአሜሪካዋ ቺካጎ ያስተናገደችው የማራቶን የሩጫ ውድድር በወንዶች አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን ተመዝግቦበታል። በሴቶች ምድብ በተካሄደው ውድድር የተመዘገበው ሰዓትም  የምንጊዜም ሁለተኛ ፈጣን ፣ የቦታው እና የአውሮጳ ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል።  በእግር ኳስ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ የአምና ሻምፒዮኑ ማንችስተር ሲቲ ለሁለተኛ ተከታታይ ጊዜ ሽንፈት ደርሶበታል፤ አርሰናል ከአምስት ተከታታይ ዓመታት በኋላ በሲቲ የመሸነፍ ሞራው ተገፎለታል። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ባየር ሌቨርኩሰን የሊጉን መሪነት ያጠናከረበትን ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አጣጥሟል። ዘጠነኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው የስፔይን ላሊጋ ሪያል ማድሪድ በተመሳሳይ ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን በማስመዝገብ በ24 ነጥቦች ሊጉን ይመራል። የ 7 ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው እና የ2022 የዓለም ዋንጫ ኮከቡ ሊዮኔል ሜሲ ከፍተኛ ዝና እና ክብር ወዳስገኘለት የቀድሞ ክለቡ ባርሴሎና በውሰት ዳግም ሊመለስ ይችላል  መባሉ አነጋጋሪ ሆኗል። እውነት ሜሲ ወደ ባርሴሎና ይመለስ ይሆን የዕለቱ ዝግጅታችን ይጠይቃል።የመስከረም 14 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
በአትሌቲክስ መረጃዎች ስንጀምር ትናንት የአሜሪካዋ ቺካጎ ባስተናገደችው  የ2023 የማራቶን የሩጫ ውድድር ኬንያዊው አትሌት ኬቪን ኪፕቱም አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ አሸንፏል። ኩቪን ውድድሩን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት ከ35 ሰከንድ የወሰደበት ሲሆን ከሁለት ሰዓት ከ1 ደቂቃ በታች በመሮጥም በዓለማችን ታሪክ የመጀመሪያ ሰው መሆን መቻሉን ዓለማቀፉ የአትሌቲክ ማህበር ገልጿል። በነፋሻማ የአየር ሁኔታ ውስጥ በአስደናቂ ብቃት አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ ያሸነፈው ኪፕቱም ስለውድድሩ ተጠይቆ በሰጠው ምላሽ « ለዚህ አልተዘጋጀሁም ነበር ፤ በጣም ደስተኛ ነኝ» ብሏል። በማራቶን ውድድሮች ሲሳተፍ ይህ ለሶስተኛ ጊዜው እንደሆነ የተነገረለት አትሌቱ ምናልባትም የራሱን ክብረ ወሰን ሊያሻሽል የሚችልበት ዕድል እንዳለው ተተንብዮለታል።   ቀደም ሲል የወንዶች የማራቶን ክብረ ወሰን በኬንያዊው ኤልውድ ኪፕቾጌ እጅ የነበረ ሲሆን በጎርጎርሳውያኑ 2022 በርሊን ውስጥ በተደረገው ውድድር 2 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ09 ሰከንድ በመግባት የራሱን ክብረ ወሰን በማሻሻል ማሸነፉ አይዘነጋም። 
በትናንቱ ውድድር ሌላኛው ኬንያዊ ቤንሰን ኪፕሩቶ ሁለተኛ ሲሆን ትውልደ ሶማሊያዊ ቤልጅየማዊ በሽር አብዲ ሶስተኛ በመሆን አጠናቋል። 
በሴቶች ምድብ የተደረገውን የትናንቱን የቺካጎ የማራቶን ውድድር ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኒዘርላንዳዊት ሲፈን ሀሰን የስፍራውን ክብረ ወሰን እና የዓመቱን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፋለች። ሲፈን ውድድሩን ለመጨረስ 2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ ወስዶባታል። ሲፈንም እንደ ኪፕቱም ሁሉ በማራቶን ስትወዳደር ገና ሶስተኛዋ እንደ መሆኑ የርቀቱን ክብረ ወሰን የራሷ ለማድረግ ብርቱ ተፋላሚ ልትሆን እንደምትችል ከወዲሁ ቅድመ ግምት እየተሰጣት ነው። ኢትዮጵያውያን እና ኬንያውያን የነገሱበት ማራቶንአትሌቷ በተለይ ከምትታወቅባቸው እና ድንቅ ብቃቷን ካስመሰከረችባቸው የመካከለኛው እና የረዥም የትራክ ላይ ሩጫዎች በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማራቶንም በተመሳሳይ ድንቅ ብቃት ማሳየቷ ከአትሌቲክሱ ማህበረሰብ አድናቆትን አትርፋለች። ሲፈን በቅርቡ ቡዳፔስት ሃንጋሪ ባስተናገደችው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአስር ሺ ሜትር ውድድር በመጨረሻ ወድቃ ከሜዳሊያ ውጭ ስትሆን  በአምስት ሺ ሜትር ውድድር የብር እንዲሆም በ1500 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፏ አይረሳም። ሲፈን ትናንት በቺካጎ ያስመዘገበችው ሰዓት የአውሮጳም ክብረ ወሰን ጭምር ሆኖ ተመዝግቦላታል። በውድድሩ ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች ሁለተኛ ስትወጣ ኢትዮጵያዊቷ መገርቱ ዓለሙ ሶስተኛ በመሆን አጠናቃለች። 
በሌላ የአትሌቲክ ዜና የቱርኳ አንካራ ትናንት ባስተናገደችው የግማሽ ማራቶን የሩጫ ውድድር በሁለቱም ጾታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አሸናፊ ሆነዋል። ቀደም ብሎ በተከናወነው የወንዶቹ ውድድር አትሌት ሲሳይ ለማ አሸናፊ ሲሆን የገባበትም ሰዓት 1 ሰዓት ከ1 ደቂቃ ከ09 ሰከንድ ሆኗል። በውድድሩ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ጪምዴሳ ደበሌ 2ኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆን ችሏል። በሴቶች ምድብ የተደረገውን ውድድር ደግሞ አትሌት ዘውዲቱ አደራው ስታሸንፍ ፤ ውድድሩን ለማጠናቀቅ የወሰደባት ጊዜም አንድ ሰዓት ከ8 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ሆኗል። 
ወደ እግር ኳስ መረጃዎች ስንሸጋገር በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት በብዙዎች ዘንድ ተጠባቂ የነበሩ የአውሮጳ ሊጎች ውጤቶች እንዳስሳለን ። ቀዳሚ የምናደርገው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ይሆናል። በሊጉ እጅግ ተጠባቂ ከነበሩት ውስጥ ትናንት አርሴናል ማንችስተር ሲቲን ያስተናገደበት ጫወታ አንደኛው ነበር።ኢትዮጵያውያን የደመቁበት የኦሪጎን አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሁለቱን ቡድኖች ጫወታ ተጠባቂ ያደረገው ያለፉትን 12 የሊጉ ጫወታዎች አርሴናል በሜዳውም ሆነ ከሜዳው ውጭ ማንችስተር ሲቲን አሸንፎ አለማወቁ እንዲሁም ሁለቱ ክለቦች ያለፈውን የውድድር ዘመን አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ማጠናቀቃቸው ለውድድሩ የተለያየ ቅድመ ግምት እንዲሰጠውም አድርጎ ነበር። የማታ ማታ አርሴናል በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ተቀይረው በገቡ ሶስት ተቻዋቾች የጫወታውን ሚዛን በመቀየር በ85 ደቂቃ ብራዚላዊው  ማርቲኔሊ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል የሚፈልጋትን ሶስት ነጥቦች ይዞ መውጣት ችሏል። ማንችስተር ሲቲ ደግሞ ከረዥም ጊዜ በኋላ የሊጉን ተከታታይ ሽንፈት ለማስተናገድ ተገዷል። አርሰናል የትናንቱን ግጥሚያ በማሸነፉ ነጥቡን 20 በማድረስ ብዙ ጎሎች ባስቆጠረ በሌላኛው የሰሜን ለንደን ክለብ ተበልጦ  ሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ትናንት በተከናወኑ ሌሎች ጫወታዎች በአቻ ውጤት የተጠናቀቁ ሲሆን ፤ ወልቨርአምፕተን ከአስቶን ቪላ አንድ አቻ ፤ ውስትሃም ኒውካስልን ዩናይትድን አስተናግዶ  ሁለት አቻ እንዲሁም ሊቨርፑልን በሜዳው ያስተናገደው ብራይተን ሁለት አቻ በሆነ ውጤት አጠናቀዋል። 
ባለፈው ቅዳሜ በተከናወኑ ተመሳሳይ የሊጉ የስምንተኛ ሳምንት ጫወታዎች ማንችስተር ዩናይትድ ድራማዊ በሆነ መልኩ ወደ ማሸነፍ የተመለሰበትን ድል ተቀዳጅቷል። በኦልትራፎርድ በወቅቱ በጠንካራ አቋም ላይ የሚገኘውን ብሬንትፎርድን ያስተናገደው ማንችስተር የመደበኛ የጫወታ ጊዜ እንሲኪጠናቀቅ 1 ለ 0 ሲመራ ቆይቶ  ተቀይሮ የገባው ስኮት ማክቶሚናይ በ93 ኛው እና 97ኛው ደቂቃዎች ላይ አከታትሎ ባስቆጠራቸው 2 ጎሎች ንጹህ 3 ነጥቦች ሰብስቦ መውጣት ችሏል። ውጤቱ ለአሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ እፎይታን የሰጠ ሲሆን ክለቡን ከተቀላቀለበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ያልሆነ ጊዜ እያሳለፈ ለሚገኘው በረኛው ኦናናም እንዲሁ እረፍት ሆኖለታል። ውጤቱን ተከትሎ ማንችስትር ዩናይትድ 10ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። በሌሎች የቅዳሜ ጫወታዎች የሊጉ መሪ ቶተንሃም ሆትስፐር አዲስ መጪውን ሉቶን ታወን ገጥሞ ፣ 1 ተጫዋች በቀይ ካርድ ጭምር አጥቶ 1 ለ 0 አሸንፎ መመለስ ችሏል። ወደ በርንሌይ የተጓዘው ቼልሲ ከረዥም ጊዜ በኋላ በርካታ ጎሎችን አስቆጥሮ 4 ለ 1 አሸንፎ መመለስ የቻለ ሲሆን ፤ ኤቨርተን ደግሞ በሜዳው በርንማውዝን አስተናግዶ እንዲሁ 3 ለምንም አሸንፏል። የፉልሃም እና ሼፊልድ ዩናይትድ ጫወታ በፉልሃም አሸናፊነት 3 ለ 1 ተጠናቋል። ሊጉን ቶተንሃም ብዙ ባገባ አርሰናልን ቀድሞ በ20 ነጥቦች ሲመራ አርሰናል በተመሳሳይ 20 ነጥቦች ሁለተኛ እንዲሁም ማንችስተር ሲቲ በ18 ነጥቦች ሶስተኛ ፣ ሊቨርፑል በ17 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።  በርካታ ጎሎች በማስቆጠር የማንችስተር ሲቲው ሄሪሊንግ ሃላንድ በ8 ጎሎች ሲመራ የኒውካስሉ አጥቂ አሌክሳንደር ኢሳክ እና የቶተንሃሙ ሶን ሁውንግ ሚን በስድስት ጎሎች ይከተላሉ ። ሊጉ ቀጣይ ሳምንት በዓለማቀፍ ውድድሮች ምክንያት አይኖርም። 
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የ9ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጫወታዎች ተስተናግደዋል። መሪው ባየር ሊቨርኩሰን ኮለንን ትናንት እሁድ ባስተናገደበት ጫወታ 3 ለ 0 በማሸነፍ በ19 ነጥቦች መሪነቱን ማጠናከር ችሏል። ትናንት በተደረጉ ሌሎች ጫወታዎች ባየር ሙንሽን ፍራይቡርግን 3 ለ 0 ፤ እንዲሁም ኤንትራህት ፍራንክፈርት ሃይደንሃይምን አስተናግዶ 2 ለ ለባዶ አሸንፈዋል። ቅዳሜ ዕለት በተደረጉ የሳምንቱ መርሃግብር ጫወታዎች ሆፈንሃይም ቨርደር ብሬመንን ገጥሞ 3 ለ2 ፣ ዳርምሽታት ወደ አውስበርግ ተጉዞ አውስበርግን 2 ለ 1 ፣ ዶርትሙንድ ዩንየን በርሊንን አስተናግዶ 4 ለ 2 እንዲሁም ዎልፍስበርግን ያስተናገደው ሽቱትጋርት 3 ለ 1 ሲያሸንፉ ሞንቼ ግላድባህ ከማየንዝ ፣ እና ላይፕሲሽ ከቦሁም ያደረጓቸው ጫወታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ሊጉን ሌቨርኩሰን በ19 ነጥብ ሲመራ ስቱትጋርት እና ባየር ሙንሽን በ18 እና 17 ነጥቦች ይከተላሉ ።
ሊጉን በርካታ ጎሎች በማስቆጠር የሽቱትጋርቱ ሴሮሁ ጉይራሲ በ13 ጎሎች ሲመራ ፤ ከቶተንሃም ባየርሙንሽንን የተቀላቀለው ሃሪኬን በ8 ጎሎች ይከተላል። 
ላሊጋ የመስከረም 21 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
 በውድድር ዘመኑ ከጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ላሊጋንን የተቀላቀለው ዩዴ ቤሊንግሃም ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኝበት ክለቡ ሪያል ማድሪድ ባለፈው ቅዳሜ ኦሳሱናን ባስተናገደበት ጫወታ 4 ለ 0 በማሸነፍ ሊጉን በ24 ነጥቦች ይመራል። ከዶርትሙንድ ማድሪድን የተቀላቀለው ቤልንግሃም ሮናልልዶ ክለቡን ሲቀላቀል ያስመዘገበውን በ10 ጫወታዎች 10 ጎል የማስቆጠር ብቃት መጋራት ችሏል። በሊጉ የ9ኛ ሳምንት መርሃ ግብር የትናንት ጫወታዎች የዓምናው ሻምፒዮና ባርሴሎና ወደ ግራናዳ ተጉዞ 2 አቻ በመውጣቱ 2 ነጥብ ጥሎ ለመመለስ ተገዷል። ሴልታ ቪጎ ከጌታፌ 2 አቻ፣ አላቬስ ከሬያል ቤትስ 1 አቻ ሲወጡ ወደ ቪያሪያል የተጓዘው ላስፓልማስ 2 ለ1 አሸንፎ ተመልሷል። አትሌቲክ ክለብ ደግሞ አልሜራን 3 ለምንም አሸንፏል። ሊጉን ከሪያል ማድሪድ በመቀጠል ጊሮና እና ባርሴሎና በ22 እና 21 ነጥቦች  ሁለተኛ እና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ ፤ አትሌቲኮ ማድሪድ በ17 ነጥቦች አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ሊጉን የሪያል ማድሪዱ ዩዴ ቤሊንግሃም በ8 ጎሎች ሲመራ ፣ የአትሌቲኮ ማድሪዱ አልቫሮ ሞራታ በ5 ጎሎች ይከተላል።
የ7 ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው እና የ2022 የዓለም ዋንጫ ሻምፒናው አርጀንቲናዊ ሊዮኔል ሜሲ በቅርቡ በውሰት ወደ ላሊጋ ሊመለስ ይችላል የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ የመገናኛ ብዙኃን ርዕሰ ወሬ መሆን ችሏል። የሜሲ ወዳደገበት እና ዓለማቀፍ ስም ዝና እና ክብር ወደተጎናጸፈበት ባርሴሎና ይመጣል የሚለው ዜና የተሰማው የአሜሪካ ሊግ ለእረፍት መዘጋቱ በምክንያትነት መቅረቡ ነበር። ነገር ግን የኢንተር ማያሚው ክለብ አሰልጣኝ ታታ ማርቲኖ «ከሜሲ ጋር ተያይዞ ስለሚወራው ወሬ የማውቀው ነገር የለም » ማለታቸው ተዘግቧል። ሊዮኔል ሜሲም ቢሆን በግሉ በውሰት ይመጣል ስለተባለው ነገር እንስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም። የአሜሪካ ሊግ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ ለእረፍት ዝግ ይሆናል ።  
ታምራት ዲንሳ

የ7 ጊዜ የባላንዶር አሸናፊው እና የ2022 የዓለም ዋንጫ ሻምፒናው አርጀንቲናዊ ሊዮኔል ሜሲ በቅርቡ በውሰት ወደ ላሊጋ ሊመለስ ይችላል የሚሉ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ የመገናኛ ብዙኃን ርዕሰ ወሬ መሆን ችሏል። ምስል Lynne Sladky/AP Photo/picture alliance
በውድድር ዘመኑ ከጀርመኑ ቡንደስ ሊጋ ላሊጋንን የተቀላቀለው ዩዴ ቤሊንግሃም ድንቅ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኝበት ክለቡ ሪያል ማድሪድ ባለፈው ቅዳሜ ኦሳሱናን ባስተናገደበት ጫወታ 4 ለ 0 በማሸነፍ ሊጉን በ24 ነጥቦች ይመራል። ምስል Tim Warner/Getty Images
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት የ9ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ጫወታዎች ተስተናግደዋል። መሪው ባየር ሊቨርኩሰን ኮለንን ትናንት እሁድ ባስተናገደበት ጫወታ 3 ለ 0 በማሸነፍ በ19 ነጥቦች መሪነቱን ማጠናከር ችሏል።ምስል Marius Becker/dpa/picture alliance
ማንችስተር ሲቲ ደግሞ ከረዥም ጊዜ በኋላ የሊጉን ተከታታይ ሽንፈት ለማስተናገድ ተገዷል። ምስል MIke Egerton/PA Wire/picture alliance
በርካታ ጎሎች በማስቆጠር የማንችስተር ሲቲው ሄሪሊንግ ሃላንድ በ8 ጎሎች ይመራል። ምስል ARIS MESSINIS/AFP
አርሴናል በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ተቀይረው በገቡ ሶስት ተቻዋቾች የጫወታውን ሚዛን በመቀየር በ85 ደቂቃ ብራዚላዊው  ማርቲኔሊ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል የሚፈልጋትን ሶስት ነጥቦች ይዞ መውጣት ችሏል። ምስል John Walton/empics/picture alliance
የቺካጎ የማራቶን ውድድር ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኒዘርላንዳዊት ሲፈን ሀሰን የስፍራውን ክብረ ወሰን እና የዓመቱን ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፋለች። ምስል Matthias Schrader/picture-alliance/dpa
የአሜሪካዋ ቺካጎ ባስተናገደችው  የ2023 የማራቶን የሩጫ ውድድር ኬንያዊው አትሌት ኬቪን ኪፕቱም አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በማስመዝገብ አሸንፏል።ምስል KAMIL KRZACZYNSKI/AFP/Getty Images

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW