1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

የመስከረም 5 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ሰኞ፣ መስከረም 5 2018

በጃፓን ቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ፉክክር ትውልደ ኤርትራዊ አትሌት በማራቶን ለጀርመን የነሐስ ሜዳሊያ አስገኘ ። ሦስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድራቸውን አላጠናቀቁም ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል ትናንትም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ለድል በቅቷል ።

በቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን ጨምሮ
በቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ፉክክር ኢትዮጵያ በመካከለኛ እና ረዥም ርቀት ውጤት እየራቃት ነውምስል፦ Andrej Isakovic/AFP/Getty Images

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

This browser does not support the audio element.

በጃፓን ቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ፉክክር ትውልደ ኤርትራዊ አትሌት በማራቶን ለጀርመን የነሐስ ሜዳሊያ አስገኘ ።  በማራቶን ተሳታፊ የነበሩ ሦስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውድድራቸውን አላጠናቀቁም ።   የጀርመን ቡድን በአውሮጳ የቅርጫት ኳስ ፉክክርም ዋንጫ አግኝቷል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል ትናንትም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ለድል በቅቷል ። በማንቸስተር ደርቢ ማንቸስተር ዩናይትድ በማንቸስተር ሲቲ አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ተመልሷል ። በቡንደስሊጋ ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገ ቡድን ጋር የተጋጠመው ቦሩስያ ዶርትሙንድ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ደረጃውን አሻሽሏል ። 

አትሌቲክስ፦ ኢትዮጵያ በረዥም ርቀት የበላይነቷን እየተነጠቅ ነው

በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በሦስት ሜዳሊያዎች በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ። ኬንያ በ2 የወርቅ ሜዳሊያ ብቻ ዩናይትድ ስቴትስን ተከትላ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሰፍራለች ።

ኢትዮጵያ ሁለት የብር እና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ነው ያገኘችው ። የብር ሜዳሊያዎቹ የተገኙት በ10,000 ሜትር ፉክክር በዮሚፍ ቀጄልቻ እንዲሁም በሴቶች ማራቶን በአትሌት ትዕግስት አሰፋ (2:24:45 )ነው ። በሴቶች የ10,000 ሜትር ፉክክር 2:24:43 በመሮጥ አሸናፊ የሆነችው ኬኒያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ናት ። የዑራጋዩዋ ሯጭ ጁሊያ ፓቴርናን ውድድሯን በ2:27:23 በመግባት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች ።

አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ፦ የቶኪዮ ፉክክሩ የመጨረሻ የስታዲየም ውስጥ ፉክክሩ መሆኑ ተገለጠ 

ኢትዮጵያዊው አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ የብር ሜዳሊያ ያጠለቀው ርቀቱን የግሉ ምርጥ ተብሎ በተመዘገበለት የ28:55.83  በማጠናቀቅ ነው ። ፈረንሳዊው አትሌት ጂሚ ግሬሲርም የግል ምርጡ በተባለለት ሰአት ማለትም 28:55.77 በመሮጥ በአንደኛነት የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል ። የስዊድኑ ሯጭ አንድሪያስ አልግሬን 28:56.02 በመሮጥ የሦስተኛ ደረጃ አግኝቶ የነሐስ ሜዳሊያ አጥልቋል ።

ጉዳፍ ፀጋዬ በ10,000 ሜትር የሴቶች ውድድር ለኢትዮጵያ የነሐስ ሜዳሊያ አስገኝታለች ። በዚሁ ፉክክር፦ ኬኒያዊቷ ቢትሪስ ቼቤት 30:37.61 በሆነ ስዓት በመግባት ነው ለድል የበቃችው ። የሁለተኛ ደረጃ ደግሞ፦ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮጳዊት ተፎካካሪ ከምሥራቅ አፍሪቃ አትሌቶች ቀዳሚ በመሆን ለጣሊያናዊቷ አትሌት ተሰጥቷል ። አትሌት ናዲያ ባቶክሌቲ የብር ሜዳሊያ ያገኘችው 30:38.23 በመሮጥ ነው ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ በ30:39.65 በማጠናቀቅ በሦስተኛ ደረጃ የነሐስ ሜዳልያ ተሸልማለች ። በውድድሩ የተካፈሉት ኢትዮጵያውያቱ አትሌቶች እጅጋየሁ ታዬ 30:55.52 በመግባት 5ኛ ፤አትሌት ፎትየን ተሰፍይ 31:21.67 በመግባት 8ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቅቀዋል ።የጳጉሜ 3 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

ውድድሩ በሚካሄድበት ቶኪዮ ከተማ የሚገኘው የሐትሪክ ጋዜጣ እና የሐትሪክ ስፖርት ኦፊሺያል ድረገጽ ባለቤeት እና ዋና አዘጋጅ ይስሐቅ በላይ ውድድሮቹን ተከታትሏል ። በመካከለኛ እና በረዥም ርቀት ውድድሮች ምሥራቅ አውሮጳውያን አትሌቶች ወደ ሜዳሊያ ሰንጠረዥ ብቅ ያሉበት ምክንያን በማብራራት የምሥራቅ አፍሪቃ የበላይነት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብሏል ።  ስለውድድሮቹም ማብራሪያውን ሲሰጥ በማራቶን ውድድር ላይ ሦስቱም ተፎካካሪዎቻችን ውድድሩን አለማጠናቀቃቸውን «በጣም የሚያሳዝን» ብሏል ። በሴቶች ማራቶን የአትሌት ትእግስት አሰፋን ጥረት እና ውጤትም አድንቋል ።

በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው የታንዛኒያው አትሌት አልፎንስ ፌሊክስ ሲምቡ (2:09:48) በመሮጥ ነው ።   ትውልደ ኤርትራዊ አትሌት አማናል ጴጥሮስ ለጀርመን የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል ምስል፦ Jan Papenfuss/Eibner/IMAGO/Eibner

ኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን አትሌቶቿ ውድድሩን ለምን አላጠናቀቁም?

በማራቶን የወንዶች ፉክክርም፦ ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት አትሌት ደሬሳ ገለታ፣አትሌት ታደሰ ታከለ እና አትሌት ተስፋዬ ድሪባ ውድድሩን አለመጨረሳቸውን ዎርልድ አትሌቲክስ ሻምፒዮንሺፕ ዘግቧል ። ይልቁንም ለጀርመን የሚሮጠው ትውልደ ኤርትራዊ አትሌት ዓማናል ጴጥሮስ ለጀርመን የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል ። በወንዶች የማራቶን «ውድድር ማቋረጥ ማለት የመጨረሻ ደረጃ ላይ መገኘት ነውና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል» ብሏል። እጅግ አሳሳቢነቱም ጠቅሷል ። 

በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀው የታንዛኒያው አትሌት አልፎንስ ፌሊክስ ሲምቡ (2:09:48) በመሮጥ ነው ። አትሌት ኢሊያስ አውዋኒ (2:09:53) ሦስተኛ በመውጣት ለጣሊያን ነሐስ አስገኝቷል ።  ትውልደ ኤርትራዊ አትሌት አማናል ጴጥሮስ ለጀርመን የብር ሜዳሊያ አስገንቷል ። ቤተሰቦቹ በጦርነት ምክንያት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የተሰደዱበት ዓማናል፦ «ምኞቴ በማራቶን ውድድር ወቅት አንድ አን እናቴን ጀርመን መጋበዝ ነው» ብሏል ። በቶኪዮ ያገኘው የብር ሜዳሊያም «መታሰቢያነቱ ለእናቴ ነው» ብሏል ።

ዛሬ በተከናወነው የ3000 ሜትር መሰናክል ውድድር የብሪታንያው ሯጭ ጌኦርዲ ቤአሚሽ አንደኛ ወጥቶ የወርቅ ሜዳሊያ አጥልቋል ። ያሸንፋሉ ተብለው ከተጠበቁ አትሌቶች መካከል ደግሞ ሞሮኮዋዊው ሶፊያን ኤል ባካሊ ሁለተኛ ደረጃ አግኝቶ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ ሁኗል ። የሦስተኛ ደረጃውን አትሌት ኤድሙንድ ሴሬም ለኬንያ ነሐስ አስገኝቷል ። ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶች ብርቱ ፉክክር ቢያደርጉም ከሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውጪ ሁነዋል ። ሆኖም አትሌት ሣሙኤል ፍሬው በአራተኛ ደረጃ አጠናቅቋል ።  ሌላኛው ኢትዮፕያዊ አትሌት ለሜቻ ግርማ ከሞሮኮው አትሌት ሣላሀዲን ቤን ዛዚድ ቀጥሎ በሦስተኛነት አጠናቅቋል ። የነሐሴ 26 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ

በጃፓን ቶኪዮ ካሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ የጀመረው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር በሚቀጥለው እሁድ ይጠናቀቃል ።

የጀርመን የቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን የአውሮጳ ዋንጫን አነሳ  

የጀርመን የቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን በአውሮጳ የፍጻሜ ውድድር የዋንጫ ባለቤት ሆነ ። የጀርመን ቡድን ከሁለት ዓመት በፊትም የዋንጫ ባለቤት ነበር ። በፍጻሜው ውድድር የጀርመን ቡድን ያሸነፈው የቱርክ ብሔራዊ ቡድንን 88 ለ83 ድል በማድረግ ነው ። በቅርጫት ኳስ ታሪክ የዓለም ዋንጫን አንስቶ በአውሮጳ ውድድርም በፍጻሜው ለድል በመብቃት የጀርመን ቡድን በጣት ከሚቆጠሩ አገራት ተርታ ተሰልፏል ። 

የጀርመን የቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን በአውሮጳ የፍጻሜ ውድድር የዋንጫ ባለቤት ሆነ ። በፍጻሜው ውድድር የጀርመን ቡድን ያሸነፈው የቱርክ ብሔራዊ ቡድንን 88 ለ83 ነውምስል፦ sampics/picture alliance

ፕሬሚየር ሊግ፥ ሊቨርፑል የማታ ማታ ባገኘው ብቸኛ ግብ መሪነቱን አስጠብቋል

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ መሪው ሊቨርፑል የማታ ማታ ባገኛት ፍጹም ቅጣት ምት በዐሥር ተጨዋች የተወሰነው በርንሌይን 1 ለ0 አሸንፎ ነጥቡን 12 አድርሷል ። ፍጹም ቅጣት ምቱን ሞሐመድ ሣላኅ በድንቅ ሁኔታ ከመረብ አሳርፏል ። ቅዳሜ ዕለት ኖቲንግሀም ፎረስትን 3 ለ0 ያሸነፈው አርሰናል በ9 ነጥብ ይከተላል ። ቶትንሀም እና በርመስ እያንዳንዳቸው 9 ነጥብ ሰብስበው በግብ ክፍያ ልዩነት ከሦስተኛ እስከ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ ። የሐምሌ 28 ቀን 2017 ፤ የስፓርት ዘገባ

ትናንት ሲጠበቅ በነበረው የማንቸስተር ደርቢ፦ ማንቸስተር ሲቲ በኢትሀድ ሜዳው ሊገጥመው የመጣው ማንቸስተር ዩናይትድን 3 ለ0 ድል አድርጓል ። ኧርሊንግ ኦላንድ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፏል ። ቀዳሚዋ ግብ የፊል ፎደን ናት ።በደረጃውም ማንቸስተር ሲቲ በ6 ነጥብ ስምንተኛ ነው ። በአንጻሩ ማንቸስተር ዩናይትድ በአራት ጨዋታዎች በአራት ነጥብ ተወስኖ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። በስምንት ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቸልሲ ቅዳሜ ዕለት ከብሬንትፎርድ ጋር ኡለት እኩል ተለያይቷል ። ። ከስሩ ኤቨርተን በ7 ነጥብ ይከተለዋል ።

በጀርመን ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽን አሁንም ድል ቀንቶታል

ጀርመን  ቡንደስሊጋ መሪው ባዬርን ሙይንሽን ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ሐምቡርግን 5 ለ0 አንኮታኩቷል ። ። በሦስት ጨዋታዎች 9 ነጥብ አለው ። በ7 ነጥብ ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድም ቅዳሜ ዕለት ሐይደንሀይምን 2 ለ0 አሸንፏል ።  ቅዳሜ ዕለት ከቮልፍስቡርግ ጋር ሦስት እኩል የተለያየው ኮሎኝ በተመሳሳይ 7 ነጥብ ሦስተና ደረጃ ላይ ይገኛል ። ከታችኛው ዲቪዚዮን ያደገው ሳንክት ፓውሊም እንደ ኮሎኝ 7 ነጥብ ይዞ አራተኛ ደረጃ ላይይገኛል ። ትናንት አውግስቡርግን 2 ለ1 አሸንፏል ።  በትናንትናው ግጥሚያ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በገዛ ቦሩስያ ፓርክ ስታዲየሙ በደጋፊዎቹ ፊት በቬርደር ብሬመን የ4 ለ0 ሽንፈት አስተተናግዷል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ-እግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW