1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመቀሌው ዝርፊያ፤የመንግሥት መግለጫና የህወሓት መልስ

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 10 2015

የመከላከያ ሠራዊት ባልደረሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች በተለይም በመቀሌ ከተማ በመንግስትና በንግድ ተቋማት ላይ በፓትሮል የታገዘ የተደራጁ ከፍተኛ ዝርፊያዎች መኖራቸውን መንግሥት ተናግሯል። አቶ ጌታቸው ረዳ "እኛ ልንፈታው የማንችለው፣ ሕዝባችን ሊፈታው የማይችለው ማንኛውም አይነት የደህንነት ሥጋት ማንም ሊፈታው አይችልም" ሲሉ በትዊተር ጽፈዋል።

Kenia I Friedensabkommen von Pretoria
ምስል Yasuyoshi Chiba/AFP/Getty Images

የመቀሌውዝርፊያ የመንግሥት መግለጫና የህወሓት መልስ

This browser does not support the audio element.

የፌዴራል መንግሥት "የመከላከያ ሠራዊት ባልደረሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች በተለይም በመቀሌ ከተማ በፓትሮል ጭምር የታገዘ ከፍተኛ ዝርፊያ መኖሩን አስታውቋል። መንግሥት « ለሕዝብ እና ለሀገር ሰላም ሲባል በሰላም ስምምነቱ የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድር በመተግበር ላይ መሆኑን በቅርቡ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።  የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የሰላም ስምምነቱን አተገባበር በተመለከተ ከመንግሥት የሚጠበቀው ተግባር እየተፈፀመ አይደለም ማለታቸው ተሰምቷል። ዶቼቬለ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የሕግ ባለሙያ  ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመው ጉዳዩ በአጭሩ የማይቋጭ ከሆነ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊሄድ ስለሚችል ሁለቱም ወገኖች በገቡት ግዴታ መሰረት ስምምነቱ መፈፀም አለባቸው" በማለት አሳስበዋል።ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዘገባ አለው።
የፌዴራል መንግሥት "የመቀሌ ሕዝብ ደኅንነት ሊጠበቅ ይገባዋል" ሲል ባወጣው መግለጫ መንግሥት ለሕዝብ እና ለሀገር ሰላም ሲባል በሰላም ስምምነቱ የገባውን ቃል ሳይውል ሳያድርና ሳያንጠባጥብ በመፈጸም ላይ መሆኑን ይሁንና የመከላከያ ሠራዊት ባልደረሰባቸው የትግራይ አካባቢዎች በተለይም በመቀሌ ከተማ በመንግስትና በንግድ ተቋማት ላይ በፓትሮል የታገዘ የተደራጁ ከፍተኛ ዝርፊያዎች መኖራቸውን ተናግሯል። ለዚህ የመንግሥት መግለጫ ቀጥተኛ መልስ የሰጡት የሕወሓት ዋነኛ ተደራዳሪ ከነበሩት አንዱ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ "እኛ ልንፈታው የማንችለው፣ ሕዝባችን ሊፈታው የማይችለው ማንኛውም አይነት የደህንነት ሥጋት ማንም ሊፈታው አይችልም" በማለት ትዊተር ላይ ጽፈዋል። 
ይህንን በተመለከተ ጥያቄ ያቀረብንላቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ዶክተር ዮናስ ቢርመታ የሰላም ስምምነቱ "አተረጓጎም ፈር እንዲስት የማድረግ አዝማሚያ እየተስተዋለ" ነው ብለዋል። "የስምምነት አተረጓጎም በቅን ልቦና ላይ የተመረኮዘ መሆን ይገባዋል። የሕግ ባለሙያው እንደሚሉት "ጉዳዩ የሚያሳስብ" ነው። ተጨባጭ ሁኔታውን የመለወጥ እና አዲስ እውነታ የመፍጠር አዝማሚያ ማስተዋላቸውንም ገልፀዋል። የሕወሓት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል የፌዴራል መንግሥት ስምምነቱን በማስፈፀም ረገድ የሚጠበቅበትን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እያደረገ አለመሆኑን በመግለጽ በተለይ የኤርትራ ሠራዊት እና የአማራ ኃይሎች ከክልሉ እንዲወጡ አልተደረገም ማለታቸው ተሰምቷል። 
የኤርትራ ሠራዊትን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት በጋዜጠኞች የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስታር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር መለስ አለም "የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዴት እንደሚወጡ በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ በግልጽ የተቀመጠ ነው። የናይሮቢው ውልም እንደዚሁ ያስቀመጠው ስለሆነ በዚያ ደረጃ የሚሄድ ነው" የሚል ምላሽ ሰጥተው ነበር። 
የሕግ መምህሩ ዶክተር ዮናስ ቢርመታ እንደሚሉት ከሰላም ስምምነቱ በኋላ እየታየ ያለው አዝማሚያ በአጭሩ የማይቋጭ ከሆነ እና ስምምነቱ በጊዜው ካልተተገበረ ሁኔታው ወዳልተፈለገ አቅጣጫ ሊሆድ ይችላል። 
በውል ቁጥሩ ያልተገለፀ ሰው ያለቀበትን ፣ መጠነ ሰፊ የስነ ልቦና ጠባሳ የጣለውን እና ግዙፍ ምጣኔ ሀብታዊ ድቀት ያስከተለውን የሁለት ዓመታት ጦርነት ሁለቱ አካላት በሰላም ለመቋጨት መስማማታቸው ትልቅ ተስፋ እና ምስጋና ያስገኘ እርምጃ ነው። 


ሰሎሞን ሙጬ
ኂሩት መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW