የመቀሌው ሽምግልና፣የህዳሴው ግድብ ውዝግብ፣የወላይታ ከምክር ቤት መውጣት
ዓርብ፣ ሰኔ 12 2012
አንዳች መነጋገሪያ የማያጡት የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በዚህ ሳምንትም በኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግስት መካከል ያለውን ውዝግብ ለመሸምገል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የሀገር ሽማግሌዎች ወደ መቀሌ ማምራት፣በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የኢትዮጵያና የግብፅ ውዝግብ እንዲሁም የወላይታ ተወካዮች ከደቡብ ክልል ምክር ቤት ለቆ መውጣት በዚህ ሳምንት ብዙ አነጋግሯል።
ከ50 በላይ ዓባላትን የያዘው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤና የሀገር ሽማግሌዎች በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልላዊ መንግስት መካከል ያለውን መቃቃር ለመሸምገልና በንግግር እንዲፈታ ለማድረግ « ሰኔ 9 ቀን 2012 ዓ/ም ወደ መቀሌ ሊጓዝ ነው» የሚለው ዜና ከተሰማ ጀምሮ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ትልቅ መነጋገሪያ ሆኖ ነው የሰነበተው።ሽምግልናውን አንዳንዶች መልካም ነው ብለው ሲያወድሱት፤ አንዳንዶች ደግሞ ነቅፈውታል።
ላወይ አካላት « ሽምግልና በጣም ጥሩ ነው ነገር ግን የጠቡ መንስኤ ይወስነዋል»ሲሉ አቢ አለማየሁ ደግሞ «ሀገር በህገመንግስት እንጂ በሽማግልና አትመራም።»ብለዋል።ማቲዎስ ሽመልስ በበኩላቸው «ዕርቅን የሚጠላ ሠይጣን ብቻ ነው።ጥሩ ሃሳብ ነው።ከኔ በላይ ላሳርና እብሪት መጨረሻው ውድቀት ነው ።»የሚል አስተያየት አቅርበዋል።አምላክ ያውቃል የተባሉ የፌስ ቡክ ተከታታይ ደግሞ «ወዳጄ ሽምግልና እኮ ሽማግሌ የሚያከብር ሲኖር ነው።ምን ዋጋ አለው ሞራላችን ከላሸቀ ቆዬ እኮ።»ሲሉ ፅፈዋል።
«ደስ የሚል ነገር ነው ወለጋ እና ጉጂም ወታደር ከማዝመት ሽማግሌ ቢላክ ጥሩ ነው!»ያሉት ሙባረክ ሱልጣን ናቸው።ፍላወር ነኝ በሚል የፌስ ቡክ ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ«ልዝረፍና ልግደል የሚልን ሀይል በምን ትሸመግለዋለህ?»ይላል።ጋሻው ዋስነህ ደግሞ«እነኝህ ሽማግሌዎች ግን ትግራይ ላይ ሁለት አመት መንገድ ሲዘጋ የትነበሩ?»በማለት ጠይቀዋል።ያሬዲና ፍስሀ ደግሞ«የሀይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ያደረጉት ነገር ደስ የሚልና የሚበረታታ ነው። በአንድ ጊዜ ውጤት የሚያመጣ ባይሆንም ሳይሰለቹ መስራት አለባቸው።የጥላቻና የቂም በቀል ፖለቲካ ይብቃን።»ብለዋል።አላምር ጆኒ ነኝ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ ደግሞ «እኔ የምለው የፌደራል መንግስቱ ግን ከስንቱ ጋር ተሸማግሎ ይችለዋል። ቆፍጠን ያለ አመራር ሰጥቶ ሀገርን ከውድቀት መታደግ አይሻልም? አንተም ተው አንችም ተይ የሚባለው ነገር ለባልና ለሚስትም ብቻ ነው።»ሲሉ ፤ዳግም ስለሺ ደግሞ «የሀገር ሽማግሌዎቹ በድል ይወጣሉ የሚል ሙሉ እምነት አለኝ።ፅንፍ የረገጠ እና የከረረ መጠላለፍ ለየትኛውም ወገን አይጠቅምም።አሁን ግብፅን በጋራ የምንመክትበት እና ኢትዮጵያዊ ወንድማማችነታችንን የምናሳይበት ጊዜ ነው።»ብለዋል።ቤዛ ተስፋይ«ደስ ይላል ደግሞም የትግራይ ህዝብ ሽማግሌና የሐይማኖት አባቶችን የሚያከብር ህዝብ ነው። ስለዚህ ጥሩ ስምምነት ላይ እንደሚደረስ እምነቴ ነው» ብለዋል።አብዱላህ አቦዬ የሚከተለውን ሃሳብ ፅፈዋል።«ያላስማማንን ጉዳይ በአስታራቂ ሽማግሌዎች መፍትሄ መስጠት ነባሩ የኢትዮጵያውያን ባህል ነው፣ለዘመናት የነበሩ ችግሮቻችንን በዚሁ መልኩ እየፈታን አብረን ኖረናል፣ስለዚህም ተነጋግሮ ችግርን ለመፍታት ዝግጁ ያልሆነ ሁሉ መጀመሪያ ከእራሱ ጋር ይስማማ»ብለዋል።ጀስቲስ አፈንጉስ ነሲቡ «በፖለቲካ ጥቅም እንጂ ፍቅርም፣ጠብም የለም። በብልፅግናና በሕወሓት መካከል ከፍተኛ የፖለቲካ ልዮነት አለ። እነዚህ የማይታረቁ የፖለቲካ ልዩነቶች በእግዚኦታ፣ በዱኣ እና በልመና አይቃለልም።» ሲሉ፤በሌላ በኩል ኤሚ ፍቅር የተባሉ አስተያየት ሰጪ «የፖለቲካ ልዩነት እኮ ያለና የነበረ ወደፊትም የሚኖር ነው ሽምግልናው መሆን ያለበት ልዩነትን በሰላማዊና በሰለጠነ መንገድ እንዲያራምዱ ነው።»ብለዋል።
የኢትዮጵያና የግብፅ ውዝግብ
ሌላዉ በዚህ ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን ያነጋገረው ጉዳይ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያና ግብፅ የገቡበት ውዝግብ ነው። ኢትዮጵያ ግብፅና ሱዳን በግድቡ ላይ ሰሞኑን ባደረጉት ውይይትና ድርድር ግብፅ የግድቡን ውሃ አሞላል በተመለከተ ኢትዮጵያ የያዘችው ግትር አቋም ለድርድሩ እንቅፋት ሆኗል ስትል።የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ምንስቴር በበኩሉ እኔ ብቻ ልጠቀም የሚለው የግብጽ አቋም፣ ለድርድሩ እንቅፋት መሆኑን ገልጿል።
ይህንን ተከትሎ ሚሚሻ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ «የታሪክ ተወቃሽ እንዳትሆኑ ተወያዮቹ በአቋሟቹ መፅናት አለባቹ ጀግኖቻችን በእናንተ ሙሉ እምነት አለን ግድባችን ይገደባል ኢትዮጵያችንም ትበለፅጋለች»ሲሉ፤ ዴብ አርሴዶ ደግሞ«ሀገራችንን በድህነት ጥለን ከምናልፍ ለሀገራችን እድገት ስንሰራ አይሆንም የሚሉንን መክተን መሞቱ የተሻለ ነው።»ብለዋል።
ልዑል ሰይፉ «ግድቡ ይሞላል እግዚአብሄርም ይረዳናል።ምክንያቱም እኛ ግድቡን ለቅንጦት አይደለም የምንፈልገው።»ሲሉ ፅፈዋል።ኢንድሪስ ሁሴን ደግሞ ።«በዚህ ወቅት ሁሉም የሀገር ልጅ በአንድነት በመቆም አባይን በተመለከተ እየተደረገ ላለው ድርድር ሀይልና ብርታት መሆን አለበት።ብለዋል።በጣም የሚገርመው ሁሉም የግብፅ ፓርቲዎች አባይን በተመለከተ የአልሲሲ መንግስት ለሚወስደው አቋምና እርምጃ ሙሉ ድጋፍ ሰጥተዋል።ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጊዚያዊ ልዩነትን በመተው፤በሀገር ጉዳይ በአንድነት በመቆም ከታሪክ ተወቃሽነት መዳን አለበት።»ሲሉ፤አሰፋ ብርሃኑ ደግሞ «አባይ ፖርቲ አይደለም አባይ ወደስልጣን የምትወጣበት ወይም ከስልጣን የምትወርድበት መሰላልም አይደለም።አባይን ለፖለቲካ መጠቀም ታሪካዊ ስህተት ነው።»ብለዋል።ሀብታሙ ግዛውም «ሞት ምንግዜም የማይቀር እዳ ነው። ጎረቤትህ አንጡራ ሀብትህን እየቀማህ በረሀብ መሞት ደግሞ የሞት ሞት ነው።»የሚል ሃሳብ አንስተዋል።
ከዚሁ ከግድቡ ውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በአሜሪካው ፕሬዝደንት ፅ/ቤት ስር ያለው ብሄራዊ የደህንነት ምክርቤትየበቲዩተር ገፁ ያሰፈረው ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙርያ ስምምነት ላይ ሳይደርስ ሙሌት እንዳትጀምር የሚያሳስብ አስተያየትም ብዙ አነጋግሯል።
ጋዜጠኛ ኤሊያስ መሰረት«ሳንሰማ አሜሪካ የአባይ ተፋሰስ ሀገር ሆነች እንዴ?«»በማለት በቲዩተር ገፁ ፅፏል።ሳሚ ቢራራ ደግሞ «ግድቡ መሞላቱ አይቀርም ግን ወዳጅ ጠላታችንን የምንለይበት ጊዜ ነው።»የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል።«ልክ እንደ ጆርጅ ፍሎይድ የ110 ሚሊየን ህዝብ አንገትን በጉልበታቸው ረግጠው ሊገድሉ የተዘጋጁ መሰለኝ !!!ቀጣይ ዘመቻችን ጉልበታችሁን አንሱልን ቢሆንስ....ጎበዝ ?»ያሉት ደግሞ ሰላም ሙሉጌታ ናቸው።አለም ህሉፍ «ማንም ምንም ይበል የግድቡ ሙሌት መጀመር አለበት።»ሲሉ፤ማሊን ሀሰን በበኩላቸው «አሜሪካ የፈለገችውን ትበል እኛ ግን ብሄራዊ ጥቅማችንን ለማስከበር በአንድነት ልንቆም ይገባል።»ብለዋል።
የወላይታ ተወካዮች ከደቡብ ክልል ምክር ቤት መዉጣት
በደቡብ ክልል ምክር ቤት የሚገኙ የዎላይታ ሕዝብ ተወካዮች እራሳቸውን ከምክር ቤት አባልነት አግለሉ መባሉ ሌላው በዚህ ሳምንት ያነጋገረ ጉዳይ ነው።ተወካዮቹ ራሳቸውን ያገለሉት የወላይታ ብሔር በክልል የመደራጀት ጥያቄ ምላሽ አላገኜም በሚል መሆኑን የዞን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ገልፀዋል።
ረጃ አብዱ የተባሉ የፌስቡክ ተከታታይ «የወሰኑት ዉሳኔ ትክክል ነዉ ምክንያቱም በክልሉ ምክርቤት በአብላጫ ድምፅ ይሸነፋና የክልልነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት አይኖረውም።» ሲሉ የበረሃው ዳኛ በበኩላቸው «የወላይታ ህዝብ ተወካዮች ትክክል አይደሉም ክልል ካልሆንን ብሎ መሸሽ ብስለት የጎደለው ውሳኔ ነው። ውጤት ለማምጣት ቦታው ላይ ሆኖ መታገል ነበረባቸው።ያለትግል ድል የለም።» ብለዋል።ዘበነ ሀይሉ ደግሞ «መንግሥት ጆሮ ዳባ ሢል ምን ይደረግ !ለማጨብጨብ ብቻ ም/ቤት መቀመጥ ምን ይጠቅማል እንደውም ዘግይተዋል»ሲሉ ፅፈዋል።
የንስር ዓይን በሚል ስም የሰፈረው አስተያየት ደግሞ «የወላይታ የክልነት ጥያቄ ሲመለስ የጉራጌው ይቀጥላል የጉራጌው ሲመለስ የስልጤው ይቀጥላል ይህ ነገር ማቆሚያው የት ነው? ስህተቱ በዚህ ድብልቅልቁ በወጣ ወቅት የሲዳማ ክልል መሆን ያመጣው ነው።አሁንም በጊዜ መላ ካልተባለ ችግሩ ማቆሚያ ያለው አይመስልም።»ይላል።ቡሽራ ባሌማ «ለሲዳማ ከተፈቀደ እነሱም መጠየቅ ህገ መንግስታዊ መብታቸው ነው »ሲሉ፤ዓለምናት ሁንዴ ደግሞ«ጎበዝ በዚህ አካሄድ በቅርቡ ከ50 በላይ ክልል ያላት ብቸኛ ሀገር ልንሆን ነው።»በማለት ፅፈዋል።በቀለ ሌዳ «ወዳጄ ሰላማዊ ጥያቄ ያለምንም ኮሽታ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መጠየቅ ሊበረታታ እንጂ ሊንኳሰስ አይገባውም።»ሲሉ፤ ዋቢ አያና ደግሞ«የኮሮና ወረርርሽኝ፣ ድህነትና ስራ አጥነት ህዝቡን ሰንጎ በያዘበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እንዲህ አይነቱ ጥያቄ መጠየቅ ነበረበት?»ሲሉ ጠይቀዋል. ።
ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ ሙሀመድ