የመቀሌው የእግር ኳስ ግጭት
ሰኞ፣ ግንቦት 7 2009ማስታወቂያ
ከትናንት በስትያ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ስቴዲየም ግጭት የተቀሰቀሰው ግጥሚያው በመካሄድ ላይ እያለ እንደነበር የአይን እማኞች ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል። የአይን እማኞቹ ግጭቱን ለማስቆም ጣልቃ የገባው ፖሊስ አስለቃሽ ጪስ መተኮሱን እና ተመልካቾችም መደብደባቸውን ገልጸውልናል። በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የቆሰሉ ሰዎችን የሚያሳዩ ምስሎች ይታያሉ።
ቅዳሜ ዕለት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ስቴዲየም ሥለተፈጠረዉ ግጭት የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽን ምላሽ እንዲሰጠን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር መንግሥት አረጋዊን በሥልክ ለማነጋገር ሞክረን ነበር። ኮማንደር አረጋዊ ግን ዶይቸ ቬለ «በሠላም ጊዜ አልመጣም» በማለት ሥለግጭቱ መናገር አልፈለጉም።
የግጭቱን መንስኤ ለማወቅ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባለሥልጣናትንም ለማነጋገር ሞክረናል። ይሁንና ፌዴሬሽኑ የቅዳሜውን ግጥሚያ አስመልክቶ ዝርዝር ዘገባ እየጠበቀ እንደሆነ ነው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ወንድምኩን አላየው የገለፁልን። እሳቸውም ጨዋታው ዛሬ ጠዋት በድጋሚ ይካሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም ሳይካሄድ መቅረቱን ገልጸውልናል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ