የመቐለ ከንቲባ ከሥልጣን መወገዳችዉ አዲስ ዉዝግብ አስከትሏል
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 19 2017የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የመቐለ ከተማ ከንቲባን ከስልጣናቸው አገዱደ። አሁን የታገዱት ከንቲባ፥ በቅርቡ የመቐለ ከተማ ምክርቤት የሰየማቸው ናቸው። የከተማዋ ምክርቤት ትላንት ባወጣው መግለጫየትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸዉ ረዳ ከንቲባውን ማገዳቸዉን ተቃውሟል። ትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች ምክር ቤቶች ከግዚያዊ አስተዳደሩ ጋር እየተወዛገቡ ነዉ።የመቀሌዉ ወኪላችን ሚሊዮን ኃይለ ሥላሴ ዝርዝር ዘገባ ልኮልናል
በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ተፈርሞ፥ በቅርቡ ለተሾሙት የመቐለ ከተማ ከንቲባ ተብሎ የተፃፈና በተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች የተሰራጨ ደብዳቤ እንደሚያሳየው፥ በቅርቡ በመቐለ ከተማ ምክርቤት የተሾሙት አዲስ ከንቲባ ሕገወጥ ስልጣን ይዘው የግዚያዊ አስተዳደሩ ስራ እያደናቀፉ እንዳለ ይገልፃል። በተለያየ ደረጃ የሚገኙ ምክርቤቶች ጉባኤ ባደረገው ህወሓት ተጠልፈው እና መጠቀሚያ ሆነው የግዚያዊ አስተዳደሩ ስራዎች በማደናቀፍ መጠመዳቸው የሚገልፀው የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር፥ በከተማዋ ምክርቤት የተሾሙት የመቐለ ከተማ ከንቲባም ሕገወጥ ስልጣን በመያዝ እና የግዚያዊ አስተዳደሩ ተግባራት በማሰናከል ከሷል። በመቐለ ምክርቤት በከንቲባነት ለተሾሙት ዶክተር ረዳኢ በርሃ በተፃፈ ደብዳቤም፥ ባለስልጣኑ በመቐለ ከንቲባነት ስም ማንኛውም ዓይነት ተግባር እንዳይፈፅሙ፣ ከስራቸው ያለው አመራር ደግሞ በእርሳቸው የሚተላለፍ ማንኛውም ትእዛዝ እንዳይቀበል ትእዛዝ ያስተላልፋል። የመቐለ ከተማ ምክርቤት በበኩሉ ትላንት ባሰራጨው መግለጫ የከተማውምክርቤት ከንቲባ የመሾም፣ በጀት የማፅደቅ እና ሌሎች ሐላፊነቶች እንዳሉት በመጥቀስ በሌላ ህዝባዊ ምርጫ ምክርቤቱ እስኪተካ ድረስ፥ በሐላፊነቱ እንደሚቀጥል እና ከንቲባ የመሾም ጨምሮ ሕግ የሚሰጠው ስልጣን እንደሚተገብር አመልክቷል። ምክርቤቱ እንዳለው የተሾሙት ከንቲባ ስራቸው እንዳይሰሩ ከትግራይ ክልል ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ የፃፉላቸው ደብዳቤ የምክርቤቱ ስልጣን የሚጋፋ በመሆኑ እንዲነሳ ጠይቋል።
በተመሳሳይ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች በወረዳ እና ቀበሌ ደረጃ የሚገኙ ምክርቤቶች፥ ግዚያዊ አስተዳደሩ በተፃረረ መልኩ የተለያየ ስልጣን የሚሰጡበት እንዲሁም የሚያግዱበት ሁኔታ ይስተዋላል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ሕጋዊ መሰረት እና ሐላፊነት በሚል መነሻ ዙርያ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተካሄደ መድረክ የጥናት ፅሑፋቸው ያቀረቡት የሕግ ምሁሩ አቶ ዳኒኤል ብርሃነ፥ በትግራይ በከተማ፣ ወረዳ እና ጣብያ ደረጃ ያሉ ምክርቤቶች የስልጣን ዘመናቸው የተጠናቀቀ እና በሂደት የነበሩ ለውጦች ግንዛቤ ውስጥ ያላስገቡ ይላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ግዚያዊ አስተዳደሩ ተልእኮዎቹ መፈፀም ከፈለገ እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ ማስተካከያዎች ማድረግ ይገባል ይላሉ።በዚህ የመቐለ ከተማ ምክርቤት እና የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ውዝግብ ዙርያ ማብራርያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የመቐለ ከተማ ምክርቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ራህማ ዓብደርቃድር ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር