የመቋጫ ያጣዉ የኪረሙ ወረዳና የአከባቢው ፀጥታ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 24 2017
መቋጫ ያጣዉ የምስራቅ ወለጋዋ ኪረሙ ወረዳና የአከባቢው ፀጥታ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ የመረጋጋት ተስፋ አሳይቶ የቆየው የአከባቢው ፀጥታ ዳግም ስጋት እየወለደ መሆኑ ተነገረ። አካባቢዉ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ለዶይቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት የወረዳው ነዋሪዎች በአባይ ሸሎቆ ኦሮሚያ እና አማራ ክልሎችን በምታዋስነው በዚህች ወረዳ የታጠቁ አካላት ስጋት መሆናቸው አልተገታም ብለዋል። አንገብጋቢ በሆነዉ በዚህ የአዝመራ ወቅት በፀጥታ ችግር ምክንያት ገበሬዎች እንዳያፈናቀሉ ሲሉ ነዋሪዎች የመንግስትን ጥብቅ ክትትል ጠይቀዋል፡፡በምስራቅ ወለጋ ስጋትን አስከትሏል የተባለው የትጥቅ ማስፈታት ዉሳኔ
ለደህንነታቸው ሲባል አስተያየታቸውን እንጂ ስማቸውን እና ማንነታቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት የኪረሙ ወረዳ ኪረሙ ከተማ ነዋሪ በአከባቢው የሚፈጸም ተደጋጋሚ ግድያ እና የታጣቂዎች ጥቃት ህብረተሰቡን መረጋጋት ነስቷል፡፡ “ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጠዋት ከጊዳ ወደዚህ ባለው ኤጄረ በምትባል ቀበሌ የኦነግ ወታደሮች ከመንግስት ወታደሮች ጋር ተተኳኩሰው ሦስት ሰዎች ሞተዋል፤ በዚሁ ኪረሙ ወረዳ ቆቆሬ በምትባል ቀበሌም አንድ ሚሊሻ ተገድሏል እና ስጋት አለ” ሲሉ ጸጥታውን የሚያደፈርሱ ያልዋቸዉን ጠቃቅሰዋል፡፡ ስሬዶሮ በተባለች የኪረሙ ወረዳ ከተማ ላይም ገደፋ ቦንጋሴ የሚባሉ የቀበሌው ባለስልጣን “በታጣቂዎች ተገድለዋል፤ መሳሪያቸው ተወስዷል” ያሉት አስተያየት ሰጪ በሳምንት ግድያ ሳይሰማ አይታለፍም ሲሉ በአከባቢው ስላንዣበበው የፀጥታ ስጋት አስረድተውናል፡፡በኪረሙ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት 15 ሰዎች ተገደሉ
በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ከጊዳ ወደ ጉቲን እና ነቀምት የሚጓጓዘውን የህዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪን አጅበው በሚሄዱ የመንግስት ፀጥታ ሃይሎች ላይ ታጣቂዎች በወሰዱት የደፈጣ ጥቃት ሰባት ሰዎች ወዲያዉ መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡ “ኪረሙ ከተማና አከባቢው ላይ ካሉት አንድ ሁለት ሦስት ቀበሌዎች በስተቀር በሌሎቹ የወረዳዎች የፀጥታ ስጋቱ ይነስም ይብዛም አለ” የሚሉት አስተያየት ሰጪው ነዋሪዎች ከፀጥታ ስጋቱ የተነሳ በአንዳንድ ቀበሌዎች መፈናቀላቸዉን ተናግረዋል፡፡
አስተያየት ሰጪው አካባቢዉ ላይ በሚገኙት ታጣቂዎች የተነሳ የፀጥታ ችግሩ ዳግም በማገርሸቱ አርሶ አደሮች በስፋት እየተፈናቀሉ መሆናቸዉን አክለዋል።“ወደ በረሃ አቅራቢያ ባሉ ቀበሌዎች በፊትም ቢሆን አርሶአደሩ ብዙም አልገባም ነበር፤ የገባዉ ግን ተመልሶ እየተፈናቀለ ነዉ፡፡
ሌላም የአከባቢው ነዋሪ በአስተያየታቸው “በኪረሙ አከባቢ ከፍተኛ ስጋት አለ” ሲሉ ወቅታዊ ያሉትን ያልተረጋጋ የአከባቢውን ፀጥታ እና የነዋሪዉን ስጋት ጠቁመዋል፡፡
ዶቼ ቬለ ስለነዋሪዎቹ ስጋትና እየተሰነዘረ ነው ስለተባለው የታጣቂዎች ጥቃት አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ለኪረሙ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብርሃኑ ፍቃዱ ስልክ ቢደዉልም “መንገድ ላይ ነኝ“ ሲሉ ለዛሬ አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡ የወረዳው ጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኦላኒ ዲንሳ እንዲሁም የጊዳ አያና ጸጥታ አስተዳዳሪ አቶ ሳቀታ እንዲሁም የምስራቅ ወለጋ ዞን ባለስልጣናት ጋርም ደውለን ስልካቸውን ባለማንሳታቸዉ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቸቻለም፡፡ከምስራቅ ወለጋ ዞን ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎች እየተመለሱ ነው
የኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች በምስራቅ ወለጋ ዞን የሚገኙና ከአማራ ክልል ጋር የሚዋሰኑ አሊያም በቅርበት የሚጎራበቱ ሲሆን በሁለቱ ክልሎች አከባቢ ላለፉት ዓመታት በታጣቂዎች የተወሳሰበው የፀጥታ ስጋቱ ሰለባ ሆነው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ