1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመቐለ ድባብ በስምምነቱ ማግስት

ዓርብ፣ ኅዳር 2 2015

ከሳምንት በፊት እስከ 14 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረ የአንዱ ኩንታል ጤፍ ዋጋ አሁን በየደረጃው ከ7 ሺህ እስከ 9 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል። የአምስት ሊትር የምግብ ዘይት ዋጋ ከ2 ሺህ ብር አካባቢ ወደ 1200 ብር፣ የፍርኖ ዱቄት ዋጋ በኩንታል ከ13 ሺህ ብር አሁን ላይ ወደ 8 ሺህ ብር ቀንሷል።

Äthiopien Tigray-Provinz Mekele
ምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

መቀሌ፣ ከስምምነቱ በኋላ የሸቀጥ ዋጋ ቀነሰ፣ የሕዝብ እንቅስቃሴ ጨመረ

This browser does not support the audio element.

                               
የኢትዮጵያ ፈደራዊ መንግሥትና ህወሓት ባለፈዉ ሳምንት  የሰላም ስምምነት መፈራረማቸዉን አብዛኛዉ የመቀሌና ያካባቢዉ ነዋሪዎች በደስታ ተቀብለዉታል።የተለያዩ የኃይማኖት ተቋማትን ስምምነቱ እንደሚደግፉ እያስታወቁ ነዉ።ሁለቱ ወገኖች ሰላም ለማዉረድ ከተስማሙ በኋላ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች የአዉሮፕላን ጥቃት ይደርሳል የሚለዉ ሥጋት እንደቀነሰላቸዉ ይናገራሉ።በትግራይ ርዕሰ ከተማ አንዣብቦ የነበረዉ የጦርነት ድባብ እየገፈፈ፣ ህዝብና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እየጨመረ፣ የሸቀጦች ዋጋ ባንፃሩ እየቀነሰ ነዉ።የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች በሰላም ስምምነቱ ተስፋ እንደሰነቁ ይናገራሉ። ላለፊት 16 ወራት ያለምንም ደሞዝ፣ ያለሌላ ገቢ ከቤተሰባቸው ጋር አስከፊ ኑሮ መግፊታቸው የሚናገሩት መንግስት ሰራተኛው አቶ ሰለሙን ፅጌ፣ በሰላም ስምምነቱ ተስፋ ካደረባቸው የመቐለ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አንዱ ናቸው። አቶ ሰለሙን እንደሚሉት የጦርነቱ ወቅት ለሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው እና አጠቃላይ የትግራይ ህዝብ ፈታኝ ሆኖ መቆየቱ የሚገልፁ ሲሆን፥ የተጀመረው የሰላም ሂደት "ከባዱን ግዜ እንዲያበቃ ዕድል ይፈጥራል" ይላሉ። 
የሰላም ስምምነቱ ዜና ከተሰማ ወዲህ ባለው ግዜ በመቐለ በተለይም በገበያዎች የዋጋ ቅናሽ መታየት ጀምሯል። ካለፈው ሳምንት እና ከዛበፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በተለይም የምግብና ምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ በመቐለ ቅናሽ ይታይበታል። በገበያዎች ተዘዋውረን እንዳረጋገጥነው፥ ከሳምንት በፊት እስከ 14 ሺህ ብር ይሸጥ የነበረ የአንዱ ኩንታል ጤፍ ዋጋ አሁን በየደረጃው ከ7 ሺህ እስከ 9 ሺህ ብር እየተሸጠ ይገኛል። የአምስት ሊትር የምግብ ዘይት ዋጋ ከ2 ሺህ ብር አካባቢ ወደ 1200 ብር፣ የፍርኖ ዱቄት ዋጋ በኩንታል ከ13 ሺህ ብር አሁን ላይ ወደ 8 ሺህ ብር ቀንሷል። የዋጋ ቅናሽ ቢኖርም አሁንም በትግራይ የፋይናንስ ተቋማት ዝግ ሆነው በመቀጠላቸው እና የጥሬ ገንዘብ እጥረት በመኖሩ ግብይቱ ውሱን ሆኖ እንዳለ ተገበያዪች ገልፀዋል። የድሮን ጥቃት በመቀሌ ከተማ
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰላም ስምምነቱ ከብዙሃን ድጋፍ እየተቸረው ነው። የተለያዩ በትግራይ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች የተፈረመው የሰላም ስምምነት በደስታ እንደሚቀበሉት አስታውቀዋል። የትግራይ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በሰጠው መግለጫ "ጦርነት አይደለም የመጀመርያ፡ የመጨረሻ አማራጭም መሆን የለበትም" ብሏል።  አሁንም በትግራይ ያለው የኤርትራ ጦር እንዲወጣ፣ የጥላቻ ንግግር እንዲወገዱ፣ ለትግራይ ህዝብ ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ፣ መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎቶች በአስቸኳይ እንዲጀምሩ የጠየቀው የትግራይ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፥ ይህ ማድረግ ለዘላቂ ሰላም አጋዥ ነው ብሎታል። ከህወሓት የሰላም ጥሪ በኋላ የተከሰተው የአየር ድብደባ
የሰላም ስምምነቱ በብዙሀን ዘንድ ታላቅ ተስፋ የፈጠረ ቢሆንም፥ ግዜ በማይሰጥ ረሀብ፣ የመድሃኒት እጦት እና ሌሎች ችግሮች ላይ ላለው የትግራይ ህዝብ ከስምምነቱ 8 ቀናት በኃላም ቢሆን እስካሁን ወደ ትግራይ የገባ ህይወት አድን ሰብአዊ እርዳታ ይሁን መድሃኒት፣ የተጀመረ የትኛውም አይነት የህዝብ አገልግሎት የለም።

የመቀሌ የጉሊት ገበያ (ከክምችታችን)ምስል Million Haileselassie/DW
የመቀሌ የጉሊት ገበያ (ከክምችታችን)ምስል Million Haileselassie/DW

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ነጋሽ መሐመድ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW