የመቐለ ፍርድቤቶች የስራ ማቆም አድማ
ረቡዕ፣ ግንቦት 13 2017
የትግራይ ዳኞች ማሕበር በቅርቡ አውጥቶት በነበረ መግለጫ፥ በነፃነት ስራቸውን መከወን የሚገባቸው ዳኞች ላይ ጣልቃ ገብነት እና ጫና ማድረግ የቆየ እንኳን ቢሆን ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን የከፋ ሆንዋል ብሎ ነበር። በተለይም ፆታዊ ጥቃትን እና የግድያ ወንጀልን በሚመለከቱ ዳኞች በድህንነታቸው ላይ የተቃጡ ጥቃቶች እና ማስፈራርያዎች እየተበራከቱ መምጣቸውን አመልክቷል። መንግስት ለዚህ መፍትሔ ይስጥ በማለት ጥሪ ሲያቀርቡ የቆዩ ዳኞች፥ መንግስት መፍትሔ ባለማበጀቱ እንዲሁም በዳኞች ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ ማስፈራራት እና ጫና ተባብሶ በመቀጠሉ የመቐለ ማእከላይ ፍርድቤትን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኙ ሁሉም የክፍለከተማ ፍርድቤቶች ከትላንት ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓመተ ምህረት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ስራቸውን ማቆማቸው ተገልጿል። የትግራይ ዳኞች ማሕበር ፕሬዝደንት አቶ ዳዊት ኃይለሥላሴ እንዳሉት ፍርድቤቶችን እየረበሹ፣ ዳኞችን እያጠቁና እያስፈራሩ ያሉት ስልጣን ያላቸው አካላት ለተከሳሾች በመወገን ነው ይላሉ።
በመቐለ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደለችን ወጣት እንስት ጉዳይ ባለፈው ሳምንት ግንቦት 8 ቀን 2017 ዓመተምህረት ብይን ለመስጠት ተሰይሞ የነበረ የመቐለ ዞን ማእከላይ ፍርድቤት፥ ሁለት ተከሳሾችን ጥፋተኛ ካለ በኃላ የቅጣት ውሳኔ ወደማስተላለፍ ሲሸጋገር የተከሳሽ ቤተሰቦች እና ተከሳሾች ረብሻ በመፍጠር ችሎት እንዲቋረጥ አድርገዋል፣ በዳኞች ላይ አደጋ ፈጥረዋል ሲል የትግራይ ዳኞች ማሕበር ገልጿል። እነዚህ በዳኞች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መፍትሔ እስኪሰጣቸው ድረስ ፍርድቤቶች ተዘግተው እንደሚቆዩም የማሕበሩ ፕሬዝደንት አቶ ዳዊት ጨምረው ገልፀዋል።
በዚሁ ጉዳይ ዙርያ ትላንት መግለጫ ያወጣው የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ፅሕፈት ቤት፥ በፍርድቤቶች እና ዳኞች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በፍትህ ስርዓቱ ላይ የተጋረጡ ግልፅ ጥቃቶች ናቸው ብሎ የኮነነ ሲሆን፥ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድም አስታውቋል። ዛሬ በመቐለ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረን እንደታዘብነው፥ ፍርድቤቶች ተዘግተው ውለዋል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ